Saturday, July 4, 2015

ወረኛዉ ዝም ይበል!! በጂቱ ለሚ


barruuቃሊቲ እስር ቤት ፣ ዞን ሦስት 2006:- አንድ ካኪ ሱሪና እጀ-ጉርድ ሸሚዝ መልበስ የሚያዘወትሩ አዛዉንት እንደአሸን ከሚተራመሰዉ እስረኛ መሃል መታየት ከጀመሩ ሰንብቷል። ተክለ-ሰዉነታቸዉ ቀጥ ያለ ሲሆን የራስ ጸጉረቸዉ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወደ ነጭ ተለዉጧል። በባሕሪያቸዉ ቁጥብ ይመስላሉ።   በሰዉነታቸዉ ላይ መጠነኛ መጎሳቆል ቢታይም ያሉበትን ሁኔታ ለመጋፈጥ ግን አሁንም ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸዉ ያስታዉቃል። ቀን ቀን ብቻቸዉን ነጠል ብለዉ ግቢ ዉስጥ ከሚያደርጉት የእግር እንቅስቃሴ ይልቅ ሌሊት ሌሊት  በተሰጠቻቸዉ የማረፊያ ቦታ ላይ ነጭ ጋቢያቸዉን አፍንጫቸዉ ድረስ ተከናንበዉ ኩርምት ብለዉ የምያሳልፉት ምሽት ይበልጥ ስለሳቸዉ የቀደመ ማንነት እንዳሰላስል ያደርገኝ ነበር። ለዓመታት ሲታሰሩበት ከነበረዉ በተለምዶ የቀይ-ሽብር ቀጠና ከሚባለዉ ዞን በምን ምክንያት ወደዚህ እንደተዛወሩ አይታወቅም። አሁን ከምን ጊዜም በላይ እጅግ ፈታኝ ሁኔታ ዉስጥ ሳይገቡ አልቀረም። አጫዋች ጓደኛ የላቸዉም።  ለማረፊያ የተሰጣቸዉ ቦታ የኣእምሮ ሕሙማንና በተለያዩ ምክንያቶች ከሌሎች ታሳሪዎች እንዲገለሉ የተደረጉ እስረኞች የሚቆለሉበት ስለሆነ አስከፊነቱ ከቃላት በላይ ነዉ። ሽታዉ አይጣል፤ ተባዩም የከፋ!። ይበልጥ የሚገርመዉ ደግሞ አንዳንድ ግዴለሽ ወጣቶች ከመጸዳጃ ክፍል ሲመለሱ እግራቸዉን በእሳቸዉ ፍራሽ ላይ እየጠራረጉ እንደዋዛ ተረማምደዉበት ያልፋሉ። እኚህ በሰዉ እግር ስር የተጣሉት ሰዉ በዘመነ-ደርግ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር የነበሩ – ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ናቸዉ!
ይህችን አጭር ትዝብቴን ያስቀደምኳት “የጨቋኞች መዉደቂያ በተጨቋኙ ሕዝብ እግር ስር ነዉ!” የሚለዉን ፅንሰ-ሀሳብ ለማጉላት እንጂ ለጊዜዉ ስለ ሰዉዬዉ የማነሳው ጉዳይ ኖሮኝ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። እርግጥ ነዉ ጨቋኝ ገዢዎች ሥልጣናቸዉን ዘልዓለማዊ አድርገዉ ያስቡታል። ጊዜም የማይቀየር፣ ዘመንም የማይሻር ይመስላቸዋል። ያ ግን ፍፁም ስህተት ነዉ። ካሰጠማቸዉ ቅዠት ሲነቁ ራሳቸዉን እንኳን ለማስተካከል ጊዜ ሳያገኙ ነገሮች ይቀየሩና በሰሩት ወኅኒ ይጣላሉ። በዘመናቸዉ ግፍና መከራን ዘርተዋልና ከምቾት ሰገነት ቁልቁል ይፈጠፈጣሉ። የጭንቅና የመከራ ጉድጓድ ማረፊያቸዉ ይሆናል። ይህንን ሀሳብ በጽሁፌ ማጠቃለያ ላይ እመለስበታለሁ። አሁን ባሩድ ባሩድ ሸቶኛልና ወደዚያዉ ልገስግስ!

No comments:

Post a Comment