አቶ በቀለ ገርባ
የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት
በይርጋ አበበ
ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ነው። ከ40 እስከ 50 ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎችን ሳላስተምር አልቀረሁም የሚሉት የዛሬ እንግዳችን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሲሆኑ በሙያቸው ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የውጭ ቋንቋዎች አስተማሪ ናቸው። በ1997 ዓ.ም 19 መምህርንን በጅምላ ያባረረው የአዳማ መምህራን ኮሌጅ አስተማሪ የነበሩት አቶ በቀለ ገርባ በወቅቱ ከመምህራን ኮሌጁ ከተሰናበቱት መምህራን መካከልም አንዱ ነበሩ። አቶ በቀለ ገርባ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ስለ ፖለቲካ ተሳትፏቸው ጅማሮ፣ ለእስር ስላደረጋቸው የፖለቲካ አቋማቸው፣ ስለ 2002 ምርጫ እና ሰሞኑን በስፋት እያወዛገበ ስላለው የአዲስ አበባ መሪ እቅድ (ማስተር ፕላን) ጉዳይ አነጋግረናቸው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተውናል። የቃለ ምልልሳችንን ሙሉ ኀሳብ ከዚህ በታች አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ።
ሰንደቅ:- የአቶ በቀላ ገርባ የፖለቲካ ተሳትፎ መቼ ጀመረ? ወደ ፓርቲ አባልነት የተቀላቀሉትስ መቼ ነው?
አቶ በቀለ:- ወደ ፖለቲካው ዓለም የገባሁትና ለመጀመሪያ ጊዜ የአንድ ፓርቲ አባል ሆኜ የተመዘገብኩት በቅርቡ ማለትም በ2002 ዓ.ም ነው። ከዚያ በፊት የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊ ልሆን እችላለሁ እንጂ አባል አልነበርኩም። ምክንያቱም እኔ አስተማሪ በመሆኔ በሙያዬ ጠንክሬ ከሰራሁ ለውጥ ማምጣት እችላለሁ ወይም አስተዋጽኦ ማበርከት የምችለው በራሴ ሙያ ነው ብዬ ነበር የማስበው። ሁሉም ሰው የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን አለበት የሚል እምነት አልነበረኝም። እኔ የተወለድኩበት ማህበረሰብ (የኦሮሞ ብሔር) በአንዳንድ ሁኔታዎች በምመለከትበት ጊዜ በደል ውስጥ ያለ ወይም ተጽእኖ ውስጥ ያለ መስሎ እየታየኝ መጣ። ስለዚህ ይህንን ነገር ደግሞ አቅሜ በሚፈቅደው መሰረት በምርጫ ተወዳድረው ወደ ስልጣን መጥተው አገሪቱ በሰላማዊ መንገድ ስልጣን እየተቀባበሉ የሚሄዱበት ስርዓት ውስጥ እንድትገባ በሚደረገው ጥረት የበኩሌን ማድረግ እችል እንደሆነ እያልኩ እያሰብኩ ሳለ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ጥሪ አደረገልኝ። በዚያ መሰረት ፓርቲውን ተቀላቀልኩ። ብዙም ሳልቆይ ወደ አመራር አመጡኝ። በምርጫ ተወዳድሬም በወቅቱ በነበረው ሁኔታ ተሸንፈሃል ተባልኩኝ። ውጤቱንም በጸጋ ተቀብዬ በፖለቲካ ተሳትፎዬ ቀጥዬ ትክክል ነው ብዬ የማምነውን እየጻፍኩ በስውር ሳይሆን በግልጽ እና በይፋ ተከትዬ ሳለ ነሀሴ 21 ቀን 2003 ዓ.ም ለእስር ተዳረኩኝ።
ሰንደቅ:- ወደ ፖለቲካ ተሳትፎው የመጡት በኦፌዴን (የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል። ከዛ በፊት ደግሞ በእነ ዶክተር መረራ የሚመራው ኦብኮ (የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ) ፓርቲ ነበረ። አሁን ሁለቱም ተጣምረዋል። የፓርቲዎቹ የጣምራነት ትግል ምን ይመስላል?
አቶ በቀለ:- ድርጅቶቹን በቅርብ ሆኜ ባልከታተልም ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር የሚያደርጉትን ጥረት በርቀትም ቢሆን እከታተል ነበር። በዚህ የተነሳም ከየትኛው ድርጅት ብሳተፍ ይሻላል ብዬ በማስብበት ጊዜ ከኦፌዴን ጥሪ ስለቀረበልኝ ኦፌዴንን ተቀላቀልኩ እንጂ የተለየ መስፈርት አውጥቼ አልነበረም። ፓርቲውን ከመቀላቀሌ በፊት የፓርቲውን ትግል በተመለከተ የምለው የለኝም። ነገር ግን ከገባሁ በኋላ ከኦፌዴን አመራሮች የተመለከትኩት የነበረው ፍጹም የሆነ የመቆጨት ስሜት እና ተፈጥሯዊ እና ትክክል (Geniune) የሆነ የፖለቲካ ስርዓት የማራመድ ዝንባሌ በመሆኑ እጅግ በጣም ነበር የወደድኩት። አቅም፣ እውቀት፣ የፖለቲካ ተሞክሮ እና የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ በጥላቻ ወይም እንደሚባለው በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ተቃውሞ ሳይሆን በትክክል ይህ ህዝብ ከሌላው ተለይቶ ተበድሏል የሚል ተቆርቋሪነት ስላላቸው ከሌላው እኩል መታየት አለበት የሚል ቅን የሆነ አስተሳሰብ እንዳላቸው ስለተመለከትኩ ፓርቲውን በመቀላቀሌ በጣም ነው ደስ ያለኝ።
ከተዋሃዱ በኋላ በአንድ ላይ እያደረጉ ስላለው ትግል ደግሞ ሁለቱም ፓርቲዎች በኦሮሞ ህዝብ ተቀባይነት ስላላቸው ለምን አትዋሃዱም? የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ ይቀርብልን ነበር። እኔ እስር ቤት በነበርኩበት ጊዜም ውህደቱ ተካሂዶ በሌለሁበት የአዲሱ ፓርቲ (የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አድርገው መርጠው ጠበቁኝ። ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላም ጊዜ ሳላጠፋ በቀጥታ ያመራሁት ፓርቲዬ በሚያደርገው ትግል ወደ ማገዙ ነው። በምርጫ ተወዳዳሪ ባልሆንም በምርጫ ቅስቀሳውና ፓርቲውን በማንኛውም መልክ በማገዝ በኩል ድጋፍ ማድረግ ችያለሁ። አሁን እያደረግን ያለነው ትግልም ይህን ይመስላል።
ሰንደቅ:- ከሶስት ዓመታት በላይ ለቆዬ እስር ተዳርገው በቅርቡ ተለቀዋል፡፡ በምን ምክንያት ታሰሩ? ከእስር ከተፈቱ በኋላ በቀድሞ ስራዎ ላይ ይገኛሉ። ሁኔታውን በዝርዝር ቢገልጽልን?
አቶ በቀለ:- ልክ ነህ እንዳልከው ከእስር የተፈታሁት ባለፈው ዓመት መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ነው። የታሰርኩበት ምክንያት እንደሚታወቀው በፖለቲካ አመለካከቴ ብቻ ነው። የተያዝኩት ነሐሴ 21 ቀን 2003 ዓ.ም ሲሆን እንዴት እንደታሰርኩ ደግሞ፤ በወቅቱ አንድ የደህንነት አባል ከምሰራበት ዩኒቨርስቲ ይመጣና ሻይ እንጠጣ ብሎ ይዞኝ ይወጣል። ሰውዬውን ቀደም ብሎ አውቀው ነበር። በተደጋጋሚ ጊዜ በፖለቲካ አመለካከቴ ዙሪያ ውይይት አድርገናል። ያኔም ሻይ እንጠጣ ብሎ ሲጠራኝ እንዲሁ እንደባለፈው ለውይይት ነበር የመሰለኝ። ነገር ግን ከተባለው ቦታ ስንደርስ ያገኘኋቸው ፖሊሶች ነበሩ። ፖሊሶቹ ወደ ማዕከላዊ ይዘውኝ ሄዱ። በሁለተኛው ቀን ፍርድ ቤት ቀረብኩ፤ ከወር በኋላ የስምንት ዓመት እስር ተፈረደብኝ። ከዚያም ወደ ዝዋይ ተወሰድኩና በተለምዶ ጨለማ ቤት በሚባል ክፍል እንድገባ ተደረገ። ከእስር ከተፈታሁ በኋላ ወደ ቀድሞ ስራዬ የገባሁት ለዩኒቨርስቲው ወደ ስራዬ እንዲመልሱኝ ስላመለከትኩ ነው። ዲፓርትመንቱም ሆነ የትምህርት ክፍሉ (ፋካልቲው) ወስኖ ወደ ስራ እንድመለስ ተደረገ።
ሰንደቅ:- በእስር ላይ በነበሩበት ጊዜ የሚደረግልዎትን ጥበቃ እና ክትትል እንዲሁም አያያዝን በተመለከተ የፓርቲዎ አመራሮች ቅሬታ ሲያቀርቡ ነበር። በእስር ወቅት አያይዝዎ ምን ይመስል ነበር?
አቶ በቀለ:- በመጀመሪያ ወደ ቃሊቲ እንደወረድኩ የገባሁት በጣም ጠባብ የሆነች ክፍል ሲሆን በጊዜው ከእኔ በተጨማሪ አንዷለም አራጌ፣ አንድ ዶክተር እና ሁለት መምህራን ነበሩ። ከዚያ ሆኜ ለአንድ ዓመት ከሁለት ወራት የፍርድ ሂደቴን ከተከታተልኩ በኋላ ሲፈረድብኝ ወደ ዝዋይ ነው የሄድኩት። ዝዋይ ስንሄድ አሳምነው ጽጌ (ኮሎኔል)፣ ተፈራ ማሞ (ጄኔራል) እና ሌሎቹም ነበሩ። በዚያም የተመደብነው በተለምዶ ጨለማ ቤት ተብሎ በሚጠራው ክፍል ነው። ዝዋይ ለአንድ ዓመት ከቆየሁ በኋላ ስለታመምኩ ወደ አቃቂ (ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት) ተዘዋወርኩ። በዚያም ዞን ሁለት በሚባል ስፍራ ነው ያስገቡኝ።
በማረሚያ ቤት የነበረኝ ቆይታ በተለይ መጀመሪያ የነበርኩበት ጨለማ ቤት እጅግ በጣም አደገኛ ተብለው የተፈረጁ ከባድ ወንጀል የፈጸሙ ወይም ደግሞ ተመልሰው የገቡ ወንጀለኞች ያሉበት ቦታ በመሆኑ በጣም አደገኛ ነው። ለደህንነትም በጣም አስጊ ነው፡፡ ምክንያቱም በታራሚዎቹም መደብደብ አለ። ለምሳሌ አንዷለም አራጌ ላይ ከባድ ድብደባ ደርሶበታል። እንደገና አልባና ሌሊሳ ላይም ድብደባ ተፈጽሞበታል። ለአእምሮም ለመኖርም በጣም ከባድ የሆነ ስፍራ ነው።
ዝዋይ የነበርኩበት ቦታ ትልልቅ ሰዎች የነበሩበት ቦታ ነው፡፡ እንደነገርኩህ የቀድሞ የአየር ኃይል አብራሪዎች፣ ሁለት ብርጋዴር ጄኔራሎች፣ ሌፍተናንት ኮሎኔሎች እና ሌሎችም በኢህአዴግ ሰራዊት ያገለገሉ እና በተለያዩ ምክንያቶች የታሰሩ ሰዎች ያሉበት ቦታ ነው። በዚያ ቦታ ከሌሎች የተገለልን ቢሆንም በጸጥታ በኩል ጥሩ የነበረ ስፍራ ነው ብዬ ነው የማስበው። የማረሚያ ቤቱ አያያዝ ግን እኛ ከሌሎቹ ተለይተን ስለምንያዝ በጣም ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግብን ነበር፡፡ ከሌሎቹ ጋር መገናኘት አንችልም፡፡ ፍርድ ቤትም ሆነ ህክምና ቦታ ስንሄድ እጃችን በካቴና ታስሮ ነበር የምንሄደው። በእስር ላይ በቆየሁባቸው ጊዜያት እጄን ሳልታሰር ሀኪም ቤትም ሆነ ፍርድ ቤት ሂጄ አላውቅም።
ሰንደቅ:- እናንተ የታሰራችሁት በፖለቲካ አመለካከታችሁ እንደሆነ ተናግረዋል። ወደ ፍርድ ቤትም ሆነ ወደ ህክምና ስትወሰዱ የምትንቀሳቀሱት እንደ ከባድ ወንጄለኛ እጃችሁን በካቴና ታስራችሁ እንደሆነም እየገለጹልን ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በከባድ ሙስና ተከሰው የታሰሩ ሰዎች በእስር ቤት ያላቸው የእስር አያያዝ የተንደላቀቀ የሚባል አይነት ነው እየተባለ ይነገራል። የህዝብን ንብረት ዘርፎ የታሰረ ሰው በነጻነት ሲንቀሳቀስ “የፖለቲካ እስረኛ” በዚህ መልኩ መያዙ ለምን ይመስልዎታል?
አቶ በቀለ:- ትክክል ነህ። የእኔ እስር ትንሽ የሚባል የእስር አይነት ነው። በመጀመሪያ ስምንት ዓመት የተፈረደብኝ ቢሆንም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቴ ወደ ሶስት ዓመት ከሰባት ወር እንዲቀነስልኝ ተደርጓል። ይህ ማለት ቀላል ፍርድ የሚባል አይነት ነው። የታሰርኩት ግን እጅግ በጣም አደገኛ ወንጀል ከፈጸሙ እና እድሜ ልክ እና ሞት ከተፈረደባቸው ወንጀለኞች ጋር ነበር። እንዳልከው በሙስና የታሰሩ እስረኞች የተያዙበት መንገድ እጅግ በጣም ምቹ በሚባል ሁኔታ ነው። ፍርድ ቤት እንኳን የሚሄዱት እጃቸውን በካቴና ሳይታሰሩ ነው። በእኛ ላይ ያለው የፖሊስ ወከባ በእነሱ ላይ አይፈጸምም። ማረሚያ ቤቱ የሚጠቀምባቸው የስራ ዘርፎች ላይ በሙያቸው አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል። ለምሳሌ ሀኪሙ ያክማል፣ አስተማሪው ያስተምራል፣ ሌሎቹም በሱቅ ስራ ላይ እንዲሰሩ ይደረጋል። እኛ የፖለቲካ እስረኞች ግን በሙያችን እንድንሰራ ይህ እድል አይፈጠርልንም። አስተማሪውም ማስተማር አይችልም፡፡ ሀኪሙም በህክምናው አገልግሎት መስጠት አይችልም። በአጠቃላይ ከህዝብ ጋር እንድንገናኝ አይደረግም ነበር።
ሰንደቅ:- እንደዚህ አይነት የታራሚ አያያዝ ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ በቀለ:- መንግስት አውቆ ይህንን አድርጎ ይሁን ወይም የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ራሳቸው ያድርጉት የማውቀው ነገር የለም። ነገር ግን አሁን እንዳልኩህ ዝዋይ አብሮኝ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ቀድሞ ከነበረበት ቦታ ወጥቶ በጣም ተራ ወንጀለኞች ካሉበት ቦታ ነው የተወሰደው። እስካሁንም እዛ ያለ ነው የሚመስለኝ። ይህ የሚያሳየው የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ራሳቸው በዘፈቀደ የሚያደርጉት ይመስለኛል። መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን ለብቻ አሰቃዩአቸው የሚል ትዕዛዝ የሚሰጥ አይመስለኝም። ምክንያቱም እነዚህ የፖለቲካ እስረኞች ነገ አገሪቱ ውስጥ አንድ ነገር ቢፈጠር የአገሪቱን መጥፋት የማይፈልጉ ናቸው። የተሻለ አስተዳደር እናሰፍናለን፣ የተሻለ አመለካከት አለን፣ ለህዝቡም የተሻለ ተቆርቋሪነት አለን የሚሉ ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች መንግስት ከሚከተለው አቅጣጫ በተለየ መንገድ መሆኑን ቢያውቅም በዚህ ደረጃ እንዲሰቃዩ ይፈልጋል የሚል እምነት የለኝም።
ነገር ግን ሙስናን በተመለከተ ዛሬ ገንዘብ የማይሰራው ስራ ስለሌለ እዛው ማረሚያ ቤት አካባቢ ያሉ ኃላፊዎች እነሱ የሚያደርጉት ነው የሚመስለኝ። ከፖለቲካ እስረኞች ጋር በተመለከተ ስንመለከተው ግን የመንግስት ትዕዛዝ ወይም የማረሚያ ቤቶቹ አሰራር ይሁን አላውቅም።
ሰንደቅ:- ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ የዘመናት ጥያቄ መመለስ ችያለሁ ብሎ ቢናገርም በርካቶች ግን በዚህ ሀሳብ አይስማሙም። እንዲያውም አንዳንዶች የኦሮሞ ህዝብ የወቅቱ ችግር ራሱ ኦህዴድ ነው ይላሉ። ኦህዴድ ለኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት ያልቻለውም የፓርቲ ነጻነት ስለሌለው ነው ይላሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ የእርሰዎ አስተያየት ምንድን ነው?
አቶ በቀለ:- ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ መልሷል፤ ፍላጎቱንም አሟልቷል ብሎ የሚያስብ ኦሮሞም ሆነ ከኦሮሞ ውጭ ያለ ሰው እንደማይኖር ይታወቃል። ይህንን ለምንድን ነው ማድረግ ያልቻለው ብዬ ሳስብ ኦህዴድ የኦሮሞ ድርጅት ባለመሆኑ ወይም ማድረግ ባለመፈለጉ ሳይሆን ስለማይችል ነው። እንዳይችል ያደረገው ደግሞ ከአመሰራረቱ ጀምሮ ባለው ችግር ነው። እንደሚታወቀው ኦህዴድ የተመሰረተው በትጥቅ ትግል ወቅት ሲሆን ህወሓት ለረጅም ጊዜ ከታገለ በኋላ ኢህዴንም ከታገለ በኋላ የደርግ መውደቂያ በተቃረበበት ወቅት ወደ ኦሮሚያ ምድር ለመግባት የግድ የኦሮሞ ተወካይ ፓርቲ ስለሚያስፈልግ ነው የተመሰረተው ብዬ ነው የማስበው። በትጥቅ ትግሉ ውስጥ በነበራቸው አስተዋጽኦ መሰረት ነው የድርጅቶቹ (የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች) አቅም የተመሰረተው። ኦህዴድ ወደ በኋላ ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ ከኢህዴንም ሆነ ከህወሓት ጋር በእኩልነት የተመሰረተ አቅም ፈጥረው ነው የመሰረቱት ብዬ አላስብም።
በዚህም ምክንያት የኦህዴድ የፓርቲ ነጻነትም ሆነ የኢኮኖሚ አቅም ከሁለቱ ያነሰ ነው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ ኦህዴድ ለኦሮሞ ህዝብ ማድረግ ቢፈልግ እንኳ አቅሙ የለውም። ያደርጋል ተብሎም አይጠበቅም። በህዝቡ ዘንድም ተቀባይነት የለውም። ወጣቶች ፓርቲውን ሲቀላቀሉ የፓርቲውን ውስጣዊ ይዘት እየቀየሩት እና ምናልባትም እየተፈታተኑት (ለኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ መልስ እንዲሰጥ ግፊት ማድረግ) ይሄዳሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ነገር ግን ወደ ኃላፊነት የሚደረሰው በፓርቲ ታማኝነት እንጂ በብቃት ባለመሆኑ ይህ ነገር አልተሳካም።
በአጠቃላይ ድርጅቱ ከዚህም ከዚያም (ከኢህአዴግም ሆነ ከኦሮሞ ህዝብ) ያልሆነ ፓርቲ ነው። እኔ እንደ አንድ ኦሮሞ ሳስበው ድርጅቱም ሆነ የድርጅቱ አባላት ያሳዝኑኛል፡፡
ሰንደቅ:- በአሜሪካ የሚገኘው የኦሮሞ ጥናት ማህበር የሚባል ማህበር ባደረገልዎት ጥሪ ወደ ስፍራው አቅንተው ነበር። በውጭ አገር የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች በኦሮሚያ ክልል ጥያቄ ዙሪያ የተለያየ አቋም አላቸው ይባላል። ጥሪው እንዴት መጣልዎት? በጉብኝትዎ የእነዚህን ሰዎች አመለካከትስ እንዴት አዩት?
አቶ በቀለ:- ማህበሩ በኦሮሞ ታሪክ፣ ባህል እና ማንነት ላይ የሚያተኩሩ ጥናቶችንና ምርምሮችን በማካሄድ ትንተና ይሰጣል። የጥናቱን ውጤትም ኦሮሞ ጆርናል የሚባል በዓመት ሁለት ጊዜ የሚታተም መጽሔት አለ፤ በዚያ ያትማል። በዚያ ማህበር የሚታቀፉት የአንድን ድርጅት አቋም የሚደግፉ ብቻ አይደሉም። በውስጡ የኦነግን ሀሳብ የሚደግፉ አሉ፣ የእኛን ሀሳብም የሚደግፉ አሉ፣ የሌሎች ድርጅቶችንም የሚደግፉ አሉ፣ የማንኛውንም ሀሳብ የማይደግፉም አሉ። ግን በኦሮሞ ፖለቲካ ድምዳሜ ላይ የሚያተኩሩ ሰዎች የሚገኙበትና ሁሉን አቀፍ የጥናት ማህበር ነው። ጥሪውም የቀረበልኝ ያለኝን ልምድ እንዳካፍል ነው።
የኦሮሞን ትግል በምናነሳበት ጊዜ በዓላማው ዙሪያ ሁለት አይነት ትግሎች አሉ። የመጀመሪያው ኦሮሞን መገንጠል የሚደግፍ ሲሆን ሌላው ደግሞ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ እንጂ ከማንም አይገነጠልም የሚለው ነው። የእኛ ትግልም ሁለተኛውን ነው የሚከተለው። ነገር ግን ሁለተኛውን ዓላማም በየትኛው የትግል ስልት እናሳካዋለን? የሚለው ጥያቄ ይነሳል። በአንድ በኩል በሰላማዊ መንገድ በሌላ በኩል ደግሞ በትጥቅ ትግል የሚለው ነው።
ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ በቆይታዬም ሆነ ከስብሰባው ታዳሚዎች ከሚያነሱት ሀሳብ እና ከሚጠይቋቸው ጥያቄዎች መረዳት የቻልኩት ከተለያዩ ድርጅቶች የመጡ ሰዎች መሆናቸውን ነው። ስብሰባ ላይ የተገኙት ሰዎች ማን ምን እንደሆነ ማወቅ አልችልም ነበረ፤ ማወቅም አልፈልግም ነበር። ባጠቃላይ ግን አሁን ያለው ነገር በፊት ከነበረው በተሻለ የመቀራረብ ሁኔታ እና በኦሮሞ ውስጥ የመብት ጥያቄዎች ላይ የመተባበር ስሜቶች ከፍተኛ ሆነው ነው ያገኘሁት። ለምሳሌ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን ተከትሎ አሁን በኦሮሞ ላይ እየተካሄደ ባለው የጅምላ እስራት፣ የማፈናቀል እና ቋንቋውንና ማንነቱን የማጥፋት አካሄድ ላይ ሁሉም ተመሳሳይ አቋም ያለው መሆኑን ነው የተገነዘብኩት።
ሌላው ደግሞ በማንኛውም ትግል ተጽእኖ ማሳደር የሚችል አቅም ያለው ድርጅት እና ሰው መሆኑንም ተረድቻለሁ። በሰላማዊ ትግሉ እኛ ገፍተን ከሄድን ከኋላችን ሆኖ ሊረዳን የሚችል ብዙ ሰው እንዳለ ተረድቼ መጥቻለሁ። እኛ የምንዳከም ከሆነ እና መንግስት ደግሞ በሁሉም መንገድ እንዳንንቀሳቀስ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር የሚዘጋ ከሆነ ‘ይሄው ያልነው ደረሰ፤ አዋጩ መንገድ ይሄ ነው’ ብለው ወደ ሌላ መንገድ ሊዞሩ እንደሚችሉ ነው የተገነዘብኩት።
የእኔ እምነት ዛሬም፣ ነገም ሆነ፣ ለወደፊት በሰላማዊ ትግል የዚህችን አገር የወደፊት እጣ ፈንታ በፍጹም መሰረታዊ በሆነ መንገድ መለወጥ ያስፈልጋል የሚል ነው። ወደ አገር ከተመለስኩ በኋላ እየሰራሁ ያለሁትም በዚሁ ላይ እሰከመጨረሻው ምዕራፍ ለመጓዝ ነው። በፊት የነበረውን ባህል፣ ተሞክሮ እና እስከዛሬ ድረስ የመጣንበትን መንገድ ሰብረን አንድ ጊዜ መውጣት የሚያስፈልገን ደረጃ ላይ ደርሰናል። አለበለዚያ እንደ ህዝብ ወደፊት አንድ አገር ይዘን የማንቀጥልበት ደረጃ ላይ የደረስን መስሎ ነው የሚታየኝ።
ሰንደቅ:- የአዲስ አበባን መሪ እቅድ (ማስተር ፕላን) ፓርቲያችሁ እንደማይቀበለው በመግለጫ አስታውቃችኋል። እርሰዎም በግልዎ ድርጊቱን (የማስተር ፕላኑን ትግበራ) የባህል ዘር ማጥፋት (CulturaL Genocide) ነው ሲሉ ገልጸውታል። ለመሆኑ ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ እንዳይሆን ፓርቲያችሁ የተቃወመው በምን ምክንያት ነው? ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ ቢሆን የኦሮሞ አርሶ አደሮች ሊጎዱ የሚችሉበት መንገድስ ምንድን ነው?
አቶ በቀለ:- ማስተር ፕላኑ ሊጎዳ የሚችልበትን መንገድ ሳይሆን ሊጠቅም የሚችልበትን መንገድ ማስረዳት የሚችል ሰው የለም። ምክንያቱም ከዚህ በፊት የተነሱ ገበሬዎች የት ነው ያሉት? ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ከ150 ሺህ በላይ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲነሱ ተደርገዋል። አሁን የት ነው ያሉት? የሚለውን ጥያቄ ስንመለከት ትናንት በቀየው ተከብሮ ይኖር የነበረ አባወራ ዛሬ እንደ መናኛ ነገር ተጥሎ የምታየው በምን ምክንያት ሆነና? ቤተሰቡ የተበተኑበት ስንት ሰው ነው? የስንቱ ልጆች ናቸው የተሰደዱት? የስንቱስ ናቸው ለሴተኛ አዳሪነት የተዳረጉት? ማንም ንጹህ ህሊና ያለው ሰው ይህን ችግር ይረዳዋል። ይህን ግፍ ልብ ይለዋል።
እኔ ኦሮሞ ስለሆንኩ ሳይሆን ድርጊቱ አማራ ላይም ሆነ ትግሬ ላይ ወይም በየትኛውም ህዝብ ላይ ቢፈጸም እቃወማለሁ። ምክንያቱም የአንድ ህዝብ ማንነት ለምን ይጠፋል ብዬ ስለምጠይቅ ነው። አንዱ አካባቢ የሚካሄድ ልማት የአካባቢውን የቆየ ባህል፣ ማህበራዊ መስተጋብር እና አጠቃላይ የህብረተሰቡን ማንነት እያጠፋ መሆን የለበትም። ምክንያቱም ልዩነታችን ውበታችን ነው የምንለው ይህንን ነው። አንዱ ሌላ ቋንቋ ሌላው ደግሞ ሌላ እየተናገረ አብሮ መኖር ይቻላል። የግድ አንድ ቋንቋ መናገር አይጠበቅብንም። ወንድ እና ሴት በምንም አይነት መንገድ አንድ አይነት አይደሉም በፍጹም የተለያዩ ቢሆኑም የሚረዳዱ እና ተነጣጥለው መኖር እንደማይችሉ ሁሉ (complmentary) የአንዱ ቋንቋ፣ ብሔር እና ማንነት መጥፋት ለምን ያስፈልጋል? ይሄ አስተሳሰብ ለምን መነጨ? ከተማን ማስፋፋት ከሆነ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉትን ቦታዎች በሙሉ ተጠቅመን ጨርሰናል ወይ? ጨርሰን ከሆነስ ደግሞ ከከተማው ውጭ ያሉትን እያለማን ሂደናል ወይ? የሁለት እና የአራት ሰዓት ጉዞ የሚያስኬድ ቦታ ላይ ሂዶ ኮንዶሚኒየም ቤት መገንባት ይሄ ከተማን ማስፋፋት ነው ወይ? ወይስ ሌላ ዓላማ አለው የሚለውን ስናይ ያን ህዝብ ሆኖ ማሰብ እና ቅንነት ያስፈልጋል። አንድ ህዝብ ማንነቱ ሲጠፋ ዝም ብሎ ማየት አይቻልም። መቼም ማንነቱ ከጠፋ በኋላ ሊነሳ አይችልም። አሁን እየሆነ ያለው ይሄ ነው።
ሰንደቅ:- እርሶዎ ከሚሉት በተጓዳኝ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 40 ቁጥር 3 ላይ የከተማም ሆነ የገጠር መሬት የህዝብና የመንግስት መሆኑን እና መሬት የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ንብረት መሆኑን ይገልጻል። ስለዚህ ይህን የህገ መንግስቱን አካል እንዴት ያዩታል?
አቶ በቀለ:- አንደኛ ነገር ህጉ ችግር ያለበት መሆኑ ከመጀመሪያው ያስታውቃል። ነገር ግን ህጉን በቅንነት ከተረጎምነው ችግር የለውም፡፡ ምክንያቱም መሬት የህዝብ እና የመንግስት ቢሆን ችግር የለውም። በትርጉሙ ላይ የሚታየው ግን መሬት የህዝብ እና የመንግስት ሳይሆን የመንግስት ብቻ ነው። የሚያሳዝነው ደግሞ የጥቂት ባለስልጣናት ሀብት መሆኑ ነው። በዚህ ወቅት ስንት የመንግስት ባለስልጣናት ናቸው እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው መሬት ባለቤት የሆኑት? ይህን በትክክል እንደ ዜጋ እየተራረምን መሄድ አለብን። ባለስልጣናቱ ያንን ቦታ የሚያገኙት እነማንን እያፈናቀሉ ነው? መሬት የህዝብ እና የመንግስት ከሆነ ህዝቡም ከመንግስት እኩል መብት አለው። መንግስት ለማስነሳት የሚያስችል መብት ያለውን ያህል ገበሬውም እኮ ከመሬቱ ያለመነሳት መብት አለው። ግን ይህ እየተደረገ አይደለም። እየተደረገ ያለው ገበሬውን ትነሳለህ ይሉታል ይነሳል፡፡ ምክንያቱም ህጉ በቅንነት እየተተረጎመ አይደለም።
አገርን ለማልማትማ ቢሆን ይሄ አገር ሲለማ ሁሉም ተጠቃሚ እንደሚሆን ይታመናል። አሜሪካ ስለለማች እኮ ነው የምንሰደደውና እነሱን እያገለገልን በሰላም የምንኖረው። ካልተቸገረ በስተቀር አገሩን ጥሎ መሰደድ የሚፈልግ ሰው የለም። ያ ሁኔታ የሚፈጠር ቢሆን፣ መንግስት ፍትሃዊ የሆነ ልማትና ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር ቢኖረው ኖሮ እኮ ማንም አገሩን የሚጠላ የለም። የከተሞች ማስፋፋት ወይም የተቀናጀ ማስተር ፕላን አይደለም፤ ዘረፋ ነው እየተካሄደ ያለው።
ሰንደቅ:- በዚህ ጉዳይ ላይ ከፌዴራል መንግስትም ሆነ ከክልሉ ገዥ ፓርቲ ኦህዴድ ጋር የመወያየት እድል አልነበራችሁም?
አቶ በቀለ:- እኛ ከህዝቡ ጋር ቡራዩ ላይ ልንወያያይ እንፈልጋለን፤ አዳራሽ ፍቀዱልን ብለን ጠይቀን እሺ ካሉን በኋላ የውይይቱ ቀን ሲደርስ ‘አይ ዛሬ የብአዴን በዓል ስለሚከበር አዳራሹን ለናንተ አንሰጥም’ ብለው መለሱልን። በዚህ የተነሳም ከህዝቡ ጋር ሳንወያይ ቀረን። እኛን ከህዝቡ ጋር እንድንገናኝ አይፈቅዱም። ኦህዴድ እንደ ፓርቲ ከእኛ ጋር እንዳይወያይ የፓርቲ ነጻነት የሌለው ፓርቲ ስለሆነ ይህን ማድረግ ስለማይችል አላደረገውም። አንዳንዶቹ ከእኛ ጋር መወያየት እንደሚፈልጉ ብናውቅም በግለሰብ ደረጃ እንጂ በፓርቲ ደረጃ አይደለም። በግላቸው መወያየት ቢፈልጉ እንኳ ከስራቸውም ሆነ ከኃላፊነታቸው ይባረራ፤ ይገመገማሉ። ስለዚህ ያንን ማድረግ አይችሉም።
ሰንደቅ:- የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 49 የፌዴራል መንግስቱ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ መሆኗን ይደነግጋል። በዚሁአንቀጽ ቁጥር አምስት ላይ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ስለሚኖራት ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ይገልጻል። የግንኙነቱ ዝርዝር ወደፊት በህግ እንደሚገለጽም ይደነግጋል። የሁለቱን አካላት (ኦሮሚያንና አዲስ አበባን) ግንኙነት በተመለከተ የወጣ ህግ አለ? ባለፉት 21 ዓመታት ኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ የተጠቀመው ምንድን ነው?
አቶ በቀለ:- በስራ ላይ ሊውል የሚፈለግ ህግ በሚወጣበት ጊዜ በማግስቱ ነበር በስራ ላይ የሚውለው። ይሄ (የኦሮሚያንና የአዲስ አበባን ግንኙነት የሚያመለክተው የህገ መንግስቱ አንቀጽ) ከወጣ ረጅም ጊዜ ቢሆነውም ህግ አልወጣለትም። አሮሞ ከአዲስ አበባ መጠቀሙ ቀርቶ አዲስ አበባን እየጠቀመ ያለው ኦሮሚያ ክልል ነው። ጭራሽ የአዲስ አበባን ቆሻሻ የተሸከመው ኦሮሚያ ክልል ነው። ይህ የሆነው ስርዓቱ በጦርነት ወደ ስልጣን የመጣ መንግስት ስለሆነ ነው። በጦርነት ወደ ስልጣን የሚመጣ መንግስትን የምንቃወመውም ለዚህ ነው። አሸናፊ የሚሆነው ገዥ ሲሆን ተሸናፊው ደግሞ ሁሉን ያጣ እና አሽከር ይሆናል። አሸናፊውን ከበርቴ ሲያደርግ ተሸናፊውን ያዋርዳል። ያ ደግሞ ጊዜውን ይጠብቅና ሌላ ጊዜ ይነሳል። ዘላቂ ሰላምን አያመጣም። ስለዚህ በሰላማዊ ትግል እየሞትንና መስዋዕት እየከፈልን የመንግስትን ስልጣን ወደ መያዝና የመንግስትን ስርዓት ወደ መቀየር መሄድ አለብን። ያን ጊዜ ጠላትነት በመካከላችን ይጠፋል፡፡ እከሌ አሸናፊ እከሌ ተሸናፊ የሚባል ነገር አይኖርም። ለዚህ ነው እኛ ይህንን ሁሉ መስዋዕት እየከፈልን፣ እየታሰርን ምንም ሳናጠፋ በደል እየደረሰብን፣ በድህነት እየተንገላታን፣ ተምረን እንዳልተማርን እየሆን እየተዋረድን፣ በየቦታው እየተደበደብን መከራችንን እያየን የምንኖረው፡፡ የዚህ አገር ስርዓት በሰላማዊ መንገድ መቀየር ግዴታ ነው፤ ይሄ ኡደት አንድ ቦታ ላይ ተቆርጦ መቅረት አለበት የሚል ጽኑ እምነት ስላለን ነው። ይሄን አገር ከመበታተን መታደግ አለብን ብለን ካመንን በሰላማዊ መንገድ እስከመጨረሻው ገፍተን መሄድ ግድ ይለናል።
No comments:
Post a Comment