Sunday, January 24, 2016

ኢትዮጵያን ለማፍረስም ሆነ ለመገንባት የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ ቁልፍ ነው፡ – ሰርጸ ደስታ

በ ሰርጸ ደስታ
Oromo horsemen march on to Finfinnee against Integrated Master Plan, November 2015
(Satenaw) — የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ በመልከዓ ምድራዊ አሰፋፈሩ ሥፋትም ይሁን አሕዙ በአገሪቱ ውስጥ ከሚኖሩ የሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎች ሁሉ ቀዳሚ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህም በላይ የባሕላዊና ሐይማኖታዊ እሴቶቹ ስብጥርና ከሌሎች አዋሳኝ ሕዝቦች ጋር ያለው መስተጋብር አገሪቷን በትክክልም ሊያማክል የሚችል ሕዝብ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ሕዝብ ለኢትየጵያ እንደ ዋና ማዕከል ሆኖ የአገሪቱን ሌሎች ሕዝቦች እንዳጣመረ ማስተዋል ብልሕነት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እንዳነሳሁት ምንም እንኳን ታሪኩን ለራሳቸው ጥቅም የሚያደርጉ ቡድኖች ቢያነሸዋርሩትም፣ ከትውልዱም አእምሮ እንዲጠፋ ቢደረግም ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ስትገነባ በዋነኝነት ሚና የነበረውም ይሔው ሕዝብ ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ይሕ ሕዝብ በበጎነት ያለውን አስተዋጽዖ የሚያገዝፉና በአገሪቱ ውስጥም የሚኖረውን መሪ ተዋናይነት ሊያሳካ የሚችል መሪና ሥርዓት አጥቷል፡፡ ይህን ሕዝብ ለታላቅ ራዕይ እጩ አድርጎ የተወጠነው የታላቁ ምኒሊክ ታሪክ ተገልብጦ ለዛሬው የዚህ ሕዝብ ትውልድ ስለተነገረው የራሱን የሚያኮራ ታሪክ እንደ ጠላት ታሪክ እንዲያነበው ተደርጓል፡፡ የዚህ ሕዝብ ጉልበትና ጥበብ በምኒሊክ ታሪክ ውስጥ እንደሆነ አስተውለው የተረዱት አደገኛ ቡድኖች ይህን ሕዝብ ከዚህ ታሪክ መነጠል አገሪቱን እንደፈለጉ ለመዘወር ለሚመኙ ወሳኝ መሆኑን አውቀው እየሰሩበት ይመስላል፡፡
በመሆኑም በአገሪቱ ውስጥ የራሳቸውን ምኞት ለማሳካት የሚያሴሩ አካላት ይህንን ሕዝብና እሴቶቹን ማዳከም፣ ግልጽ እንዳይሆንና ውዥምብር ውስጥ በማስገባት ሌላውን በቀላሉ ለመዘወር ይጠቀሙበታል፡፡ እነዚህ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው አካላት ዛሬ አገሪቱን እየመሩ ያሉትን ባለስልጣናት ጨምሮ በአገር ውስጥም በውጭም የሚኖሩ ሲሆኑ፡ ከዜጎች ውጭም የሌሎች አገራትንም ይጨምራል፡፡ ከነዚህ ሀገራት ዜጎች ጋርም በሕቡዕ የሚነቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያን በተደጋጋሚ ታይተዋል፡፡
የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ አንድ ቋንቋ ቢናገርም በጣም የተወሳሰበ ታሪካዊና ማሕበረሰባዊ መስተጋብር ያለው ነው፡፡ የአንድ ዘር ግንድ መነሻ ያለውም ሕዝብ አይደለም፡፡ ይህ ግን እንዲታወቅ ከላይ የጠቆምኳቸው ሕዝቡን ለራሳቸው መጠቀሚያ ለማድረግ ባሰቡ ኃይሎች አይፈለግም፡፡ ኦሮምኛ ተናጋሪው ሁሉ ከመዳ ወላቡ እንደመነጨ አደርገው በብጣሽ ሀረግ ሊያስሩት ይሞክራሉ፡፡ እውነታው ግን ፍጹም ከዚህ የተለየ ነው፡፡
በእኔ ግንዛቤ የኢትዮጵያ የዘር ግንድ ጥያቄና የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ
በዘር ግንድ (በደም) አንድ አይነት በሔር ነን ከሚሉት ይልቅ በድንበር በሚዋሰኑ ብዙ የተለያዩ ብሔሮች መሀከል ያለው ቅርርቦሽ የበለጠ ነው፡፡ የሸዋ ኦሮሞ ከባሌ ወይም ቦረና ወይም ሐረር ኦሮሞ ሕዝብ ጋር ካለው የደም ትስስር ይልቅ በአቅራቢያው ካሉት አማራና ጉራጌ ነን ከሚሉ ሕዝቦች የበለጠ ትስስር እንዳለው መገመት  እንችላለን፡፡ ኦሮምኛ ተናጋሪ ሁሉ አንድ አይነት የደም ዘር አለው ተብሎ ሁሉንም ወደ መዳወላቡ ማቆር ሴራዊ እንጂ ምሁራዊ አይመስለኝም፡፡ አንድ ምሳሌ ላንሳ ዛሬ በግንደ በረት አካባቢ የሚኖር ብዛት ያለው ኦሮምኛ ተናጋሪ አማራ ናቸው ተብለው ከሚታመኑት የሸዋ ነገስታት ዘር እንደሆኑ በግልጽ የተመዘገበ ታሪክ አለ፡፡ ታሪኩ ከነ አጼ ንብለድንግል አካባቢ ብዙም ራቀ የማይባል ነው፡፡
አማራ ነኝ የሚለው ጎጃሜና ኦሮሞ ነኝ የሚለው ወለጋም ከጎጃሜና አማራ ነኝ ከሚለው የሸዋ ሕዝብ የተሻለ የዘር ትስስር እንደሚኖራቸው ቢታሰብ መሠረተ ቢስ አያሰኝም፡፡ አንድ ሌላ ማስተዋል፤ በኦሮሞ ሕዝብ ፍልሰት በሉት እንቀስቃሴ ጊዜ የኦሮሞው ሕዝብ ወሮ ወደገባባቸው ቦታዎች ሰዎች ነበሩ ይመስለኛል፡፡ እና የኦሮሞው ሕዝብ እነዚሕን ሕዝቦች አዋሃዳቸው (assimilate) ተብሎ ሲነገር በስፋት ይሰማል፡፡ ቢያንስ እነዚህ ሕዝቦች ዛሬ ቋንቋቸው ወደ ኦሮምኛ ተቀይሮ በደማቸው ግን ሌላ ሕዝብ ሆነው እየኖሩ እንዳሉ እንዴት ማሰብ ያዳግታል፡፡ በተለይ ምዕራብ ሸዋ፣ ጥቁር እንጭኒ፣ ወንጪ፣ የተጠቀሰው ግንደ በረት፣ ጋፋት ሌሎችም እስካሁንም በአይን በማየት እንኳን መለየት የሚቻልበት ነው፡፡ ዛሬ ድረስ በዝዋይ ደሴት የሚገኙ የዜይ ሕዝብ ምልክት ሊሆነን ይችላል፡፡ ወንጪ ሀይቅ አካባቢም የሚኖረው ሕዝብ እንዲሁ፡፡ ብዙ ብዙ ሊባል ይቻላል፡፡ ጉዳዩ የተነሳው ከኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ ጋር ስለሆነ እንጂ እንዲህ ያለ ውስብሰብነት በአማራ ነኝ ትግሬ ነኝ የሚለውም ተመሳሳይ ነው፡፡ ዛሬ ለምናየው ብሔረተኝነት ቋንቋ እንጂ የደምም ሆነ የባህል አንድነት መሠረት ላለመሆነቸው ለሚያስተውል ግልጽ ይመስለኛል፡፡ የታሪክ ምሁራን ነን የሚሉት ነገሩንም አልነገሩንም፡፡ የመጀመሪያው የኦሮሞ ሕዝብ ባሕል (ዛሬም ድረስ በቦረና ያለ ነው) አንድን ሰው ከወደዱት ፍጹም የሆነ ቤተሰባዊ ውህደትን በመስጠት ስሙ በቀጥታ ከዘር (Biological)አባቱ ተለውጦ በወደደው የቦረና አባት ከዚያ በኋላ ባለው የዚሁ አዲሱ የመውደድ አባት ቢባል ይሻላል ዘር ሥም ይጠራል፡፡ በኦሮሞ ሕዝብ ያሉ የሥም ሐረጎች ትክክለኛውን የዘር ግንድ ላይጠቁሙ የሚችሉበትም እንዲህ ያለ አጋጣሚ እንዳለስ ስንቶቻችን እናውቃለን፡፡
አንዳንዶች በተለይም ደግሞ ኦሮሞ ነን የሚሉት ቢጠሉትም ሐበሽ (ድብልቅ) የሚለው የአረብኛ ሥያሜ ያለምክነያት አለተሰጠንም፡፡ ይሄንን ደግሞ ዓለም የሚያነበው መጽሐፍ ቅዱስ ሳይቀር ይመሰክራል፡፡ በአሁኑ ዘመን ባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ እትሞች “ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን” ተብሎ በትንቢተ ኤርምያስ የተጻፈው ጥንታዊያኑ እትሞች የሚሉት” ኢትዮጵያዊ አበባ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን” ነው፡፡ በእርግጥም እንደዛሬው ዘመን ሳይሆን ከጥንትም ጀምሮ የተለያየ (አበባ) መልክ ያላቸው ሕዝቦች የሚኖሩባት አገር ይችው የእኛዋ አገር ነች፡፡  ዝርያን ከሚያሳዩ መስፈርቶች አንዱ የሰውነት አወቃቀር/አካላዊ መለያ ነው፡፡ ቋንቋና ባህል የአካባቢ ተጽዕዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በመልክ አንዱን ከአንዱ መለየት አይቻልም፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክን በተመለከተ ኦሮሞ ነኝ የሚለውም ምሁር ደብተራ የተባሉትም የጻፉትን ጽፈዋል፡፡ ታሪክ በቲፎዞ እውነት ሊሆን ባይችልም ለየራሳቸው ደጋፊዎቻቸው የሚሉትን ይበሉ፡፡ እኔን ግን አሁን አሁን እያሳሰበኝ ያለው በዚህ ሕዝብ ላይ የሚቆመር ቁማር ነው፡፡ በሐይማኖትም የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ ከሌሎች በበለጠ ብዝሀነት አለው፡፡ ዋነኞቹ የክርስትናውና የእስልምናው ብዛት ሕዝባቸው ከዚሁ ኦሮምኛ ከሚናገረው ነው፡፡ እዚሕ ሕዝብ ላይ ያነጣጠሩ ሴራዎች ከውስጥ ፖለቲካዊ ከውጭ ሀይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ይመስላል፡፡
የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብና አሳሳቢ ሐይማኖታዊ ሴራዎች
በዓለም ላይ በሐይማኖታዊ በጎነት በመጽሐፍ ቅዱስም በቁራንም የተጠቀሰች አገር ብትኖር ኢትዮጵያ ብቸኛ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በጥንታውያኑ ኢትዮጵያውያን ዘንደ በነበረች ስብዕናን ተቀዳሚ መስፈረት ባደረገች ፍልስፍና ምክነያት ነው፡፡ ዛሬ መካ እያለ የሚጎርፈው ሙስሊም የመጀመሪያዎቹን መካ ያባረረቻቸውን የእስልምና ተከታዮች ኢትዮጵያ በእንግድነት እንደተቀበለችና መጠለያ እንደሰጠች በአፉ ቢያወራም ከልብ አያስተውልም፡፡ የአገራችን ብዙ የሚባል የእስልምና ተከታይ የአረብ አገር ናፋቂ እንጂ የእምነቱ መሠረት የሆነችውን የራሱን አገር እምብዛም አያፈቅርም፡፡ አልፎም በተለያዩ ከውጭ የእስልምና ተክታይ አገሮች ጋር በመተባበር በሕዝባችን ውስጥ ብዙ ችግር የሚፈጥሩ ግለሰቦች አሉ፡፡ በተለይም ደግሞ የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ የሰፈረባቸው ምስራቃዊ የአገራችን ክፍሎች ማለትም ሐረርጌ፣ አርሲ እንዲሁም ባሌ በተደጋጋሚ የዚህ ሴራ ኢላማ እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡ በድሮ ጊዜ የሱማሊያ ወረራ እየተባለ የሚጠራው የዚያደባሬ ሙከራም አንዱ ነበር፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ያለውን ውስበስብ ነገር ባለማገናዘብ ዛሬ ብዙዎች የእስልምናን ጽንፈኝነት በኢትዮጵያ ለማሰፈን በሚጥሩ ሴረኞች ፖለቲካና ታሪካዊ ይዘት ያለው በሚመስል ስብከት እንደተታለሉ ሳስብ ስጋት እንዳለ እገምታለሁ፡፡ ሌሎችም የእኔ አይነት ስጋት እንዳላቸው እገምታለሁ፡፡ ከአንድ አመት በፊት መሠለኝ አንድ አየለ ገመቹ የሚባል ፀሐፊ ሊያሰገነዝበን የሞከረውም ይሄንኑ ይመስላል፡፡ ምን ያህሎቻችን የአየለን ጽሑፍ በጥሞና እንዳስተዋልንው አላውቅም፡፡ከላይ በጠቀኳቸው የምስራቅ ኦሮምያ አካባቢ ተወልደው ከባዕድ የእስልምና ተከታይ አገሮች ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች የኦሮምኛ ተናጋሪውን ሕዝብ ኦሮሞ በሚል ብቻ ለራሳቸው መጠቀሚያ እያደረጉት  እንደሆነ የሚያስገነዝቡ ምልክቶች ይነበባሉ፡፡ ሂደቱ ውስብስብም ቢሆን አቅጣጫው የሚጠቁመው እንደዚያ ነው፡፡ የኦሮምኛ ተናጋሪውን ሕዝብ አንድ እንደሆነ ወደ መዳወላቡ ለማቆር የሚደረገውም ጥረት ከዚህ አንጻር ቢታይ የሴራውን ጫፍ ማወቅ ይቻላል፡፡ የአኖሌና ጨለንቆም ታሪክ ከመቶ ምናምን ዓመት በኋላ ዛሬ እንደ ትኩስ ለበቀልና ለጥላቻ ሀውልት የሚቆምላቸው ለሕዝብ ካለ አዘኔታና ፍቅር ሳይሆን የኦሮምኛ ተናጋሪውን ሕዝብ ከሌላው ጋር ሕብረት አትፍጠር የሚል አንድምታ እናለው ይሰማኛል፡፡ ብዙ ለሚዲያ የማይመቹ የማናወራቸው ነገሮች አሉ፡፡ በውጭ አገር ሆነው አገር ቤት በጸብ እንዲታመስና የደሀ ልጅ እንዲያልቅ ወደ እሳት የሚጨምሩትን ድምጾች ባንሰማ መልካም ነበር፡፡  ግን ብጥብጡ እንዲቀጥል ብዙ የሚለፍፉትን መስማታችን አልቀረልንም፡፡
ያለመሪና ዓላማ ለሞት የሚማገድና በዘረኝነት የተለከፈ ትውልድ
ጉዳዩ አሳሳቢ ነው፡፡ የንጉሳውያኑን ስልጣን እናወርዳለን በሚል በድሮ ጊዜ የሆነውን አውራ የሌለው ንብ አይነት እንቅስቃሴ ውጤት ማገናዘብ ካልቻልን እባብ ሞኝን ሁለት ጊዜ ነደፈው የሚለው አይነት ነው የእኛ ነገር፡፡ ከዋነኞቹ ቀንደኛ የፖለቲካ መሪዎች እስከ ሰላም ሰባኪ ነን የሚሉ የሀይማኖት ሰዎች ንግግራቸው የጥላቻና የበቀል ስሜት የሚነበብበት ነው፡፡ ሰላም እንዲሆን የሆነ አካል ስለሰላም ካልተነሳ ሁሉም የአራዊት አዳኝና ታዳኝ ሕይወት ይሆናል፡፡ ብዞዎች ከነጉድፋቸውም ቢሆን የውስጥ ነገራቸውን ገድበው ራሳቸውን እያሻሻሉ ነው፡፡ እኛ ዛሬም ያው ነን፡፡ ለኢትዮጵያ መፍረስ ተማርኩ የሚለውና ብዙም ባይማር ብልጣብልጥ አዋቂ የሆነው ተጠያቂዎች ነን፡፡ እውነታው አብዛኞቻችን የሁከት ናፋቂ፣ የግል ጥቅም ሕልመኞች፣ ከሰፈር ያላለፈ የዘረኝነት መንፈስ የተጸናወተን ነን፡፡ አንደም አገርንንና ሕዝብን የሚማርክ አስታራቂ ጠፋ፡፡ አባቶቻችንን አላዋቂ መሀይብ አደረግን ናቅን፡፡ ወደን በገባንበት የአጥፋው ፍልስፍና እየጠፋን ማጥፋት ኑሯችን ሆነ፡፡
በቅርቡ የአድስ አበባን ማስተር ፕላን አስመልክቶ በተነሳው አመጽ ከበስተ ኋላው ሌሎች ኃይሎች አሉ የተባለውም ያለምክነያት አይደለም፡፡ የሚያሳዝነው ግን የመንግስትን ባለስልጣናት የሚያሳስባቸው በሀገር ደህንነት ላይ የሚመጣው ዘለቄታዊ ችግር ሳይሆን የራሳቸው ሥልጣን ስለሆነ ይሄንኑ አመጽ ሆን ብለው በማንሻፈፍ በሰላማዊ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ለማጥራት እንደ ጥሩ አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ይመስላል፡፡ ከውጭ ሆነው ልዩ አጀንዳቸውን በአገሪቱ በጊዜ ብዛት ለመከወን የሚንቀሳቀሱት ግን እንደውም ውዥምብር ለመፍጠር ባለስልጣኖቻችን ይፈልጓቸዋል፡፡ በውጭ አገር ያሉ ተቃዋሚ ተብዬዎችም እንዚሁኑ የአገር አደጋ የሆኑ ግለሰቦችን  በአንድነት የአመባገነኑን የኢትዮጵያ መንግስት ለመዋጋት በሚል ለጥምረት ሲጋባበዙ እናያለን፡፡  በአገር ጉዳይ ላይ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ በሚል የበቀለኛ እሳቤ ወደፊት መሄድ አይቻልም፡፡
ሕዝብን ከሕዝብ በማሳነስና በማስበለጥ ሳይሆን በአሰፋፈሩ፣ በዝሀነቱና ስብጥሩ ምክነያት የኦሮምኛ ተናጋሪውን ሕዝብ የማያማክል ፖለቲካም በሉት መንግስት ኢትዮጵያን በመልካም ይመራታል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ልብ በሉ ሌሎችን ማሳነስ አይደለም፡፡ ሁሉንም በማስተጋበር ለመምራት ያስችል ዘንድ ይሄ ሕዝብ ወሳኝ ስለሆነ እንጂ፡፡ አገሪቷ ውስጥ አሉ የተባሉ ሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ሁሉ ይሄ ሕዝብ ይዋሰናል፣ በባሕል በእምነት የሚጋራቸው እሴቶች አሉት፡፡ በተቃራኒውም ኢትዮጵያን ለማጥቃትም በሉት እንደፈለጉ ለመዘወር ይሄንኑ ሕዝብ ኢላማ ያደረገ ውጥን ማቀድ ነው፡፡ ይሄን ሕዝብ በፖለቲካና በታሪክ ውዥንብር ውስጥ ከቶ ሌላውን እንደፈለጉ ማድረግ እንደሚቻል አስባለሁ፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለውም መንግስት ራሱን ለመከላከል የሚጠቀመው ይሄንኑ ስልት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ላይ የተንገዳገደና የተወዣንበረ አቋም ባይኖረው ኖሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በእድገትም በሉት በመልካም አስተዳደር የተሻለ ጊዜ እናይ ነበር፡፡ አለመታደል ይሄ አልተሳካም፡፡
ማንንም ለመወንጀል አይደለም፡፡ ለማስተዋል ይረዳ ዘንድ እንጂ፡፡ እስከዛሬ ያለፍንባቸው የጥላቻና የእናጥፋው ፖለቲካ ስልት ብዙ ወገናችን አልቋል፡፡  ፖለቲከኞቻችንንም፣ ሐይማኖተኞችንም እስከዛሬ ሰማናችሁ፡፡ ምክር መስሎን የተቀበልነው ሁሉ እኛንው አጠፋን፡፡  የሽማግሌዎቻችን ቃልና ተግሳፅ የመሐይም ነው ብለን ናቅን፡፡ የራሳችንን ጥለን የሌሎችን ናፍቀን አመጣን መጨረሻችን ማፈሪያ ሆነ፡፡ ማስተዋል አጣን፡፡ ተሳስቼ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁንም ደግሜ አላለሁ ሌላውን ለማሳነስ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ ለማምጣት የኦሮምኛ ተናጋሪውን ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ማነጽ ወሳኝ ነው፡፡  ሌላ ከልብ የሆነ የሕዝብና የአገር ቁጭት ያለው አካል ያሰፈልጋል፡፡ በሕዝብ መነገድ ይቁም፡፡ የኢትየጵያም መሪዋ ከልብ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሊሆን ይገባዋል፡፡  አማራ፣ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ሌላ ሌላ እንደሆነ የሚያስብ አዛው ሰፈር ጠባቂ ቢሆን የሻላል፡፡ አሳዛኝ ደረጃ ላይ እንደደረስን ይሰማኛል፡፡ ኦሮሞዎቹ አማራዎቹ፣ ትግረዎቹ፣ ዎቹ … እያልን እርስ በእረሳችን ተራርቀናል፡፡ ሌላውን ዘረኛ ጎሰኛ እንላለን ይሄው ልክፍት ግን እኛንው ይዞናል፡፡ ይህ ሁሉ እራሱን የለውጥ ሐዋሪያ የሚያደረገው የ60ዎቹ ትውልድ በረከተ መርገሞች እንደሆኑ አምናለሁ፡፡ ሕዝባችን፣ ትውልዱ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ሊታነጽ እንደሚገባ የሰማኛል፡፡ በተለይ ደግሞ በርዕሴ ያነሳሁት ለአገሪቱ አንድነትና መልካም ሥርዓት ለማሰፈን ወሳኝ የሆነው የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ ልጆች ሆን ተብሎ የኢትዮጵያዊነት ስሜታቸው እንዲደበዝዝ እንደተደረገ የሰማኛል፡፡   ሕንድ ሕንድ ሆና የምትኖረው ልዩነት ሳየኖር ቀርቶ ሳይሆን ሁሉም ዜጋዋ አገሬ ሕንድ ብሎ ስለሚያስብ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሕዝብ ያለው ሁሉ ይከበራል፡፡
እግዚአብሔር አገራችንን ኢትየጵያን ይባርክ! አሜን!
አመሰግናለሁ!

2 comments:

  1. Sana hundumtu ni beeka. garuu hanga bara kanatti tokkummaa dhabun oromoo humna warra alagaaf akka jilbeenfatu isa tasiiseera. garu kanaan boodaa haalli walfakkataan akka nu hin mudannee nuti dhaloonni Qubee waadaa seenaa waliin qabna.


    ReplyDelete
  2. Maarree maslif akkas si yaaddesse abbaa garaa

    ReplyDelete