Thursday, September 18, 2014

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም ወይስ ለህዝቦች መሰረታዊ መብቶች እውቅና ያለመስጠት ነው?

በፍቅሩ ቶላ*
ካለፉት 23 ኣመታት ጀምሮ ኢትዮዽያን ለገጠማት የፖለቲካ ቀውስ ዋና መንስዔው ‘ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም’ እንደሆነ ተደርጎ፣ ያለማቋረጥ ሲጻፍና ሲነገር ይሰማል። በመሰረቱ ኢትዮዽያ ሲጀመር ጀምሮ የፖለቲካ፣ የኤኮኖሚና ማህብራዊ ችግሮች ተለይተዋት ኣያውቁም። በተለይም ካለፈው ግማሽ ምዕተ ኣመታት በላይ ለሆነ ጊዜ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ታይቶባት ኣያውቅም። ንጉሳዊው ኣገዛዝ ከተወገደበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ኣንዴ ጦርነት፣ ሌላ ጊዜ ጦርነትም ሆነ ሰላም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። ገዢዎች እራሳቸውን ለማታለል ሰላምና እድገት ኣለ ብሉም፣ ሰላምም ሆነ እድገት የሉም።
ሃገሪቱን ለገጠማት የፖለቲካ ችግር መንስኤ፣ ለዘመናት ስንከባለል የመጣው የኣስተዳደር ብልሹነት እንጂ ኣሁን እንደሚወራው በህዝቦች ማንነት ላይ የተመሰረተው የፌደራል ስርዓት ኣይደለም። በተለይም ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ኣድሎኣዊ የብሄር ብሄረሰቦች ኣያያዝና ኣስከፊ የጭቆና ኣገዛዝ ዛሬ ላንዣበበው የመበታተን ኣደጋ ዋናው ምክንያት መሆኑን መካድ ኣይቻልም። ሁሉም ገዢዎች እኔ ነኝ የማውቅልህ፣ በማለት የህዝቦችን የእኩልነት ጥያቄ ለመመለስ ፈቃደኛ ኣልነበሩም። በተለያዩ ወቅቶች የጭቆና ኣገዛዞች እንዲታረሙ ስጠየቁ ህዝቡ የት ይደርሳል፣ ምንስ ያመጣል፣ በሚል በንቀት ስመለከቱ ኖሩ። በተለይም የኦሮሞና የደቡብ ኣርሶ ኣደሮችን ለጭሰኝነት የዳረገው የመሬት ስሪት እንዲለወጥ ያለማቋረጥ ጥያቄ ቢቀርብም፣ ስርዓቱ በንቀት ዝምታን መምረጡ ለንጉሳዊው ኣገዛዝ በህዝባዊ ኣብዮት መውደቅ ምክንያት ሆኗል።
የህዝቡን ኣብዮት ቀምቶ ስልጣን ላይ የወጣው ወታደራዊው መንግስትም፣ ህዝቡ እንደተመኘው ዲሞክራሲያዊ ኣስተዳደር፣ እኩልነትና ፍትሕን ሳይሆን ኣምባገነናዊ ስርዓት ዘረጋ። ለሃገሪቱ ህዝቦች እኩልነትና እድገት የታገሉትንም በገፍ ፈጃቸው።
ከዚያ ፍጅት የተረፉት፣ ኣማራጭ ሲያጡ ኣምባገነኑን የወታደር መንግስት በነፍጥ ለማስወገድ ወደ ጫካ ገቡ። በዚህም መሰረት የትግራይ፣ የኦሮሞ፣ የሲዳማ ወዘተ የሚባሉ የነጻነት ድርጅቶች ተመስርተው ዱር ቤቴ ኣሉ። ቀድሞ በተማሪነት ዘመናቸው ለኣንድት ኢትዮዽያና ህዝቦችዋ እኩልነት ይታገሉ የነበሩት ወጣቶች በኣሁኑ ጉዟቸው ግን ለየወጡበት ብሄረሰባቸው ነጻነት ለመታገል መሆኑን በይፋ ገልጸው ትግላቸውን ጀመሩ።
ከረጅም ኣመታት ደም ያፋሰሰ ጦርነት በኋላ የወታደራዊው መንግስት ዘመን ኣከተመ። ለየብሄራቸው ነጻ ሃገር ለመመስረት ይታገሉ የነበሩትም የኣቋም ማሻሻያ በማድረግ በኢትዮዽያ የዲሞክራሲ ስርዓት በመዘርጋት በኣንድ ኢትዮዽያ ስር፣ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዲኖር ለዚህም የኣስተዳደር መዋቅሩ ፌደራላዊ እንዲሆን ኣዲስ ህገመንግስት ወጣ። በዚህም መሰረት በህገ መንግስቱ ኣንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ የሚከተለው ተደንግጓል። “ማንኛውም የኢትዮዽያ ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ህዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት ኣለው። ይህ መብት ብሄሩ፣ ብሄረሰቡ፣ ህዝቡ በሰፈረበት መልክዓ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግስታዊ ተቋማት የማቋቋም እንዲሁም በክልልና በፌደራል ኣስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናው ውክልና የማግኘት መብትን ያጠቃልላል” ይላል። በቋንቋ ላይ ተመሰረተ የሚባለው ፌደራሊዝምም ይፋ የሆነው እንግዲህ በዚህን ጊዜ ነበር።
በኣጠቃላይ ከላይ የተጠቀሰው ኣንቀጽም ሆነ ሌሎች በህገመንግስቱ ላይ የሰፈሩት ኣንቀጾች በሃገሪቱ ለዘመናት ሰፍኖ የቆየውን የጭቆናና እኔ ኣውቅልሃለሁ የሚለውን የሚያስቀርና ህዝቦች በራሳቸው የውስጥ ጉዳይ ላይ ለመወሰን በሚያስችላቸው መልክ የተቀረጹ በመሆናቸው ሊደገፉና በስራ ላይ እንዲውሉ ለማስደረግ መታገል ያስፈልጋል። ሆኖም ከህገመንግስቱ ኣንቀጾች ውስጥ በኣንቀጽ 39 ንዑስ ኣንቀጽ ኣንድ ስር የገባው “እስከመገንጠል መብት” የሚለው ሀረግ ሃገሪቷን ለማፍረስ የታቀደ ነው በሚሉ ወገኖች ከመጀመሪያው ተቃዉሞ ገጠመዉ። ይህም በበኩሉ በኣጠቃላይ የህዝቦችን የዲሞክራሲ መብቶች እንዳለ ወደ መቃወም ኣሸጋገራቸው። በዚህ በተጠቀሰው ንዑስ ኣንቀጽ ስር በገባው ሃረግ ላይ የተከፈተው ዘመቻም ቀደም ስል እምብዛም ትኩረት ያልሰጡትን ወገኖች በመቀስቀስ በአንቀጹ ደጋፊዎችና ተቃዋሚ መካከል ከፍተኛ ቅራኔ ሊፈጥር ቻለ። በንዑስ ኣንቀጹ ሀረግ ላይ የታየዉ የተጋነነ ተቃውሞ በሌሎች ዘንድ የቀድሞውን የጭቆና ኣገዛዝ ለመመለስ የሚፈልጉና የሕዝቦችን ተፈጥሮአዊና የዲሞክራሲ መብቶችን ለመቀበል ካለመፈልግ የተነሳ ነው የሚል ትርጉም ስለተሰጠው ቅራኔውን በማባባስ የንዑስ ኣንቀጹ መኖር ሳይሆን ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት የሃገሪቱን ፖለቲካ ኪሳራ ውስጥ እንዲገባ ኣድርጓል።
በኣንቀጹ ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች መካካል የተፈጠረው ግብግብም ለገዢዉ የወያኔ መንግስት ከፋፍሎ መግዛት መልካም ኣጋጣሚን በመፍጠር እነሆ በኣንድ ሃገር ውስጥ ኣብረን የሚንኖር ሳይሆን ጭራሽ ተያይተን እንደማናውቅ ህዝቦች ጎራ ለይተን በጠላትነት እስከ መፈራረጅ እያደረሰን ይገኛል። ሌሎች ጉዳዮች ተረስተው በዚሁ ላይ ስንወዛገብ ድፍን 23 ኣመታት ኣልፈዋል። ዛሬም ይህ ሁሉ መሆኑ እየታወቀ በመጪዎቹ ኣመታትም በዚሁ ጉዳይ ላይ ጊዜ ጉልበትና ገንዘብ ለማባከን የወሰን ይመስላል።
በኣንድ በኩል የፌደራል ኣወቃቀሩን ማውገዝና የማጥላላት ፖለቲካ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጽንፈኛ ብሄርተኞችን እያባዛ መሆኑን ማንም ልክደው ኣይችልም። ለሁሉም ችግሮች እሱን ተጠያቂ ማድረግ በጣም ኣሳሳቢና ኣስፈሪ የሆኑ ችግሮችን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ብልህነት ነው። በሌላም በኩል ገዢው መንግስት የህዝቦችን መብት እየረገጠ፣ ነጻ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችንና የሀይማኖት ነጻነትን እያፈነ ህዝቦችን መንቀሳቀሻ እያሳጣ በመሄዱ ጽንፈኝነት እየተበራከተ መምጣቱ በግልጽ እየታየ ነው። በሌሎች ሩቅም ሆኑ ጎረቤት ሃገሮች የፖለቲካና የሃይማኖት ኣክራሪዎች ተፈጥረው በየቀኑ የንጹሃን ሰዎችን ደም እያፈሰሱ ያሉት በዋናነት መንስኤዎቹ የገዢዎች ከመጠን ያለፈ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች፣ የፖለቲካ፣ የእኮኖሚና የሃይማኖት ጭቆናዎች እንደሆኑ ስለ ኣክራሪዎቹ የሚያጠኑት ባለሙያዎች ከሚነግሩን ሌላ እኛም እንገነዘባለን የሚል ግምት ኣለኝ። በኢትዮዽያም እንደዚህ ኣይነት ምልክቶች ኣይታዩም የምንል ከሆነ እራሳችንን ማታለል ብቻ ይሆናል። ይህንን ለመረዳት ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ ፓልቶኮችንና ፌስቡኮችን መከታተል በቂ ነው። ስለዚህ መሰረታዊ የዲምክራሲ መብት የሆነውን እራስን በራስ የማስተዳደር መብቶችን ለሃገር ኣንድነት ኣስጊ ኣድርጎ በመገመት ያልተጠበቁ ሌሎች ችግሮችን እንዳንጋብዝ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
ለኢትዮዽያ ከፌደራላዊ አስተዳደር ኣወቃቀር ሌላ መፍትሔ ሊኖር ኣይችልም። በዚህ ላይ ኣብዛኞች የሚስማሙ መሆናቸውን በተለያየ ኣጋጣሚ ሲገልጹ ይሰማል። ሆኖም ደጋግመው እንደችግር የሚያነሷቸው የኣሁኑ ፌደራሊዝም “በቋንቋና በህዝቦች ማንነት ላይ ስለ ተመሰረተ የሃገሪቱን ኣንድነት ያናጋል፣ ሀገራዊ ስሜት እንዲቀንስ አድርጓል፣ ለህዝቦች መቀራረብና በፈለጉት ኣካባቢ ተንቀሳቅሰው ለመስራት እንቅፋት ሆኗል” ወዘተ የሚሉትን ነው። እውነቱ ግን ከፍ ብዬ እንዳነሳሁት ኣንደኛ ገና ከመጀመሪያው እራስን በራስ የማስተዳደር የዲሞክራሲ መብት መሆኑን ባለ መቀበል ኣዲሱን የኣስተዳደር አወቃቀር ወይም የፌደራላዊ አደረጃጀትን በጭፍን መቃወም ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ገዢዉ የኢሕአዲግ መንግስት የጻፈውን ህገመንግስት ረግጦ የዜጎችን ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን በመርገጡ፣ የፖለቲካውን ሜዳ በሞኖፖል መያዙ፣ የህዝቦችን እንቅስቃሴ በመገደብ ሆን ብሎ ሁሉም በየክልሎቻቸው ተወስነው እንዲቀመጡና የጋራ የሃገር ጉዳይን እንዲረሱ በማድረጉ ነው።
የትምህርት ፖሊሲውም ለገዢዉ ቡድን የከፋፍለህ ግዛ እንዲያመች ተደርጎ በመቀረጹ የሃገሪቱ ወጣት ትውልድ ከክልሉ ባሻገር ስለ ሌሎች ክልሎችና ህዝቦች እንዳያውቅና እንዳይገናኝ ተደርጎ ለሃገሩ ባዕድ እስከመምሰል ደርሷል። ያለፉትን ታሪኮች ጥሩውንም ሆነ መጥፎውን በታሪክነቱ ብቻ እንዲያውቁ መደረግ ሲገባ ለጥላቻና መለያየት መጠቀሚያ በማድረግ የወጣቱ ትውልድ ኣእምሮ እንዲበከል ተደርጓል። መለያየት ቢፈጠር እንኳን በሰላማዊ ጉርብትና እንዳይኖሩ በመካከላቸው የጥላቻ መርዝ ተረጭተዋል።
በእኔ ግምት የፌደራል ኣወቃቀሩ ችግር ባይሆንም ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ለሃገር ኣንድነት እናስባለን የሚሉት ወገኖች ጉዳዩን ከመጠን ባለፈ በማጋነናቸው ነው። ይህ ኣመለካከት ገዢዉ ቡድን የኣገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም በህዝቦች መካከል መጠራጠርና ጥላቻ እንዲፈጠር ጠቅሞታል። ይህን ተጠቅሞ የሚሰራቸው ጸረ ዲሞክራሲ የሆኑ ድርጊቶቹ እውነትም ሃገሪቷን ለገጠማት የፖለቲካ ችግሮች ሁሉ መንስኤው የፈደራሊዝሙ ኣወቃቀር እንደሆነ ኣስመስሎታል። ይህን ተከትሎ ያለማቋረጥ ሃላፊነት በጎደላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ከየኣቅጣጫው የሚነዛ የጥላቻ ፖለቲካ፣ ኣልፎም የሕዝቦችን ክብር የሚያ ጎድፉ መርዘኛ ንግግሮችና ጽሁፎች የህዝቦችን መቀራረብና ኣብሮነትን በከባድ ሁኔታ ጎድተዋል፣ እየጎዱም ነው።
ተወደደም ተጠላ በባህል፣ በቋንቋና ሃይማኖት የተለያየን ህዝቦች በኣንድ ኢትዮዽያ የሚትባል ሀገራችን ለዘመናት ኣብረን እየኖርን መሆናችን የሚታወቅ ቢሆንም ባለፉት ኣገዛዞች ለእነዚህ ልዩነቶች እውቅና ባለመሰጠቱና በግድ ኣንድ ለማድረግ በመሞከሩ ዛሬ ለገጠሙን ችግሮች መነሻ መሆናቸውን ከላይ ለመግለጽ ሞክሬኣለሁ። ኣሁንም ቢሆን ልክ እንደቀድሞ በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ወደ ጎን በመተው ቢያንስ ለህዝቦች እውቅና የሰጠውን የፌደራል ኣወቃቀር መንቀፍና ሃገሪቷን ለገጠሟት ችግሮች ሁሉ እሱን ተጠያቂ ማድረግ ፈጽሞ የሚያዋጣ መስሎ ኣይታየኝም።
ይልቁንም ተቀራርቦ በመነጋገርና በኣንድነት ለሙሉ የዲሞክራሲ መብቶች በጋራ ሆኖ በመታገል ጸረ ዲሞክራሲ የሆነውን ገዢ ቡድን ማስወገድና ከዚያም የወደፊት የሃገሪቷን ችግሮች ለኣንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት መስራት ያስፈልጋል። በየትኛውም የኣለም ክፍልና የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በሁሉም ጉዳዮች ላይ ሙሉ ስምምነት ባይኖርም ሁላቸውም የሚሰሩት ለኣንድ ሃገር በመሆኑ በጠረጴዛ ዙሪያ በመሰባሰብና በመከራከር፣ በመወያየትና በሰጥቶ የመቀበል መርህ መሰረት በጋራ ሃገራቸውን ይመራሉ እንጂ እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል ህዝባቸውን ለመከራ የሚዳርጉ ጥቂት ናቸው። እኛም ከጥቂቶቹ በመሆናችን ልናፍርበት ይገባል። እንደውነቱ ከሆነ የኢትዮዽያ ኣንድነት ፖለቲከኞች ያለፉትም ሆኑ የዛሬዎቹ በሃገር ስም ይማሉ እንጂ በእውነት ስለሃገር እያሰቡም ሆነ እየሰሩ ኣልነበሩም ዛሬም የሉም ለማለት ይቻላል። ስለሃገር ያስባሉ ቢባሉም በውስጧ የሚኖሩትን ህዝቦች ይረሱና ስለመሬቷ ብቻ ሲጨነቁ ይታያሉ። ሃገር ማለት ጋራና ሸንተረሯ ብቻ ሳይሆኑ ሃገርን ሃገር የሚያስኛት በውስጧ የሚኖሩ ህዝቦች መሆናቸውን ሲረሱ ይስተዋላሉ።
ስለዚህ ለጊዜው ሙሉ በሙሉ በሁሉም ጉዳዮች ላይ መስማማት እንደማንችል ኣውቀን በሚንስማማባቸው ነገሮች ላይ በጋራ ሆነን በመታገል ኣንዱ በኣንዱ ላይ ኣስተሳሰቡንና የፖለቲካ ፍላጎቱን ለመጫን ሳይሞክር ለዲሞክራሲ ተገዥ ሆነን ካልሰራን ገዢው መንግስት ሃገሪቱን ወደማትወጣበት ችግር ውስጥ እንዲከታት ፈቃድ መስጠታችን መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል። ይህንን ኣምባገነን መንግስት ኣሁን በተያዘው የተናጠል ትግል በምንም መንገድ ለማስወገድ እንደማይቻል እስካሁን ያልተገነዘበ ኣለ ብሎ ለመገመት ኣይቻልም። እንደዚሁም በጋራ ስምምነነትና ሁሉም ካልተሳተፈበት ኣንድ ቡድን ለብቻው የኢትዮዽያን ህዝቦች የሚገዛበት መንገድ የተዘጋ መሆኑን ማወቅ ግዜና ጉልበት ከማባከን ያድናል። “ብሄራዊ ፓርቲ ነን” በማለት ፓርቲያቸውን በህዝቦቻቸው ወይም በሚኖሩባቸው ኣካባቢዎች ስም ከሰየሙት ጋራ ኣብሮ መስራት ኣለመፈልግ በራሱ የሚያቀራርብ ሳይሆን የበለጠ የሚያራርቅ መሆኑን ለመረዳት ጠንቋይ መጠየቅ ኣያስፈልግም።
እኔ እንደማስበው መፍትሔ ሊሆን የሚችለው “በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የፌደራል ኣወቃቀር” እያሉ ለዘመናት ስንከባለሉ ለመጡት ችግሮች ሁሉ ሰበብ እንደሆነ እስኪመስል ድረስ ማውገዝ ሳይሆን በመጀመሪያ እስካሁን ይህንን ጉዳይ ኣስመልክቶ የተከደበት መንገድ ስሕተት መሆኑን ተገንዝቦ በጥላቻና ንቀት ሳይሆን በፍቅር ህዝቦች በፈለጉት ኣይነት ኣስተዳደር የመተዳደር ሙሉ መብት ያላቸው መሆኑን እውቅና መስጠትና በህዝቦች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር፣ መከባበርና ኣንዳቸዉ ለኣንዳቸዉ ኣስፈላጊ መሆናቸዉን በማስተማር ከሁሉም በፊት ለህዝቦች ፍቅርና ክብር መስጠት ያስፈልጋል።
ገዢውን መንግስት ማሸነፍ የሚቻለው ሁላችንም በኣንድነት ቆመን ለዲሞክራሲ መብቶች መከበር ስንታገለው ብቻ ነው። ህዝቡም መብቶቹን ለማስከበር በኣንድነት እንዲነሳ ለማድረግ የሚቻለው ፖለቲከኞች የቡድን ፍላጎትን፣ ኣልሸነፍ ባይነትንና፣ መናናቅን እርግፍ ኣድርገው ትተው በእውነት ለህዝቦች ዘላቂ ሰላም፣ ብልጽግናና ተከባብሮ መኖር የሚታገሉ መሆናቸውን በማያወላውል ሁኔታ በይፋ ማሳወቅ ሲችሉ ብቻ ነው። ለዚህም ከሁሉ በፊት በተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች መካከል ስምምነት ላይ መደረስ ኣለበት። ስምምነት ሲባል እውነተኛና ሃቀኛ የሆነ የፖለቲካ ድርድር ማድረግ ኣለባቸው ማለት ነው። በእኔ እምነት ፓርቲዎችን ሊያስማማ የሚችለው የኢትዮዽያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ኣንድነት (መድረክን) መቀበልና ማጠናከር ነው። በኣሁኑ የሃገሪቷ ተጨባጭ ሁኔታ ከሱ የተሻለ የፖለቲካ ኣደረጃጀት ለመፍጠር ከባድ ብቻም ሳይሆን የሚቻል ኣይደለም። በኣሁኗ ኢትዮዽያ ኣንድ ወጥ የሆነ ፓርቲ እንመሰርታልን ስለዚህም ሁሉም መዋሃድ ኣለባቸው የሚባሉት በእውነቱ የህልም እንጀራ ነው። ከላይ እንዳልኩት የሚያዋጣው የፖለቲካ ድርድር ኣድርጎ በምርጫ በሚያገኙት ድምጽ የጋራ መንግስት (coalition government) ለማቋቋም መስራት ይሆናል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኣጠቃላይ የሆነ ብሄራዊ እርቅ እንዲኖር የፖለቲካ ድርድር ኣድርገው የተስማሙ ድርጅቶች መስራት ኣለባቸው። በተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ስምምነትና እርቅ ሳይኖር ብሄራዊ እርቅ ማድረግ ኣይቻልም። እስካሁን የብሄራዊ እርቅ ጥያቄ ለገዢው መንግስት ብቻ ሲቀርብ እንደነበረ ይታወቃል። የገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎች እራሳቸው ባልታረቁበትና የጋራ ተቃዋሚኣቸውን ወይም ጠላታቸውን በኣንድነት ለመታገል ባልቻሉበት ሁኔታ ገዢውን ፓርቲ ለብሄራዊ እርቅ መጥራት ትርጉም የለውም።
የተቃዋሚዎች የማያወላውል የፖለቲካ ስምምነት ማድረግና በኣንድነት መቆም ገዢዉ መንግስት ለፖለቲካ ድርድርና የብሄራዊ እርቅ ጥያቄን እንዲቀበል ስለሚያስገደድ መጀመሪያ ተቃዋሚዎች እርስ በራሳቸው መታረቅ ኣለባቸው።
ከዚሁ ጋር ኣብሮ ሊነሳ የሚችለው የቋንቋ ጉዳይ ነው። ቋንቋ ትልቁ የመግባቢያ መሳሪያ በመሆኑ ከተቻለ ሁሉም ያሃገሪቷ ህዝቦች ኣንድ ቋንቋ መናገር ብችሉ በጣም ጠቃሚ መሆኑን ማንም ኣይስተውም።
ሆኖም ብዙ የኣለም ሃገሮች በተለይም የኣፍሪካ ሃገሮች ባለብዙ ቋንቋ ናቸው። እንደነ ህንድ የመሳሰሉት ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቋንቋዎች ኣላቸው። የእነዚህ ሃገራት ህዝቦች ሁሉ ተግባብተው በኣንድ ሃገር ኣብረው በመኖር ላይ ናቸው። እያንዳንዱ ህዝብ በቋንቋዉ የመጠቀም መብቱ የተጠበቀ በመሆኑ በቋንቋ ምክንያት ግጭት ውስጥ የገቡበት ጊዜ ስለመኖሩ እርግጠኛ ኣይደለሁም። ብዙዎቹ በሃገር ደረጃ በብዛት የሚነገሩትን ቋንቋዎች መርጠው የማእከላዊ መንግስት የስራ ቋንቋ ኣድርገው ይጠቀማሉ። የማእከላዊውን መንግስት የስራ ቋንቋ ለማይችሉት የፓርላማ ኣባላት የትርጉም ኣገልግሎት በመስጠት ሁሉንም በእኩልነት ያስተናግዳሉ። ይህ በኢትዮዽያ የማይሰራበት ምክንያት የለም። ለምሳሌ ሃገሪቱን በተመለከተ የኣማርኛና የኦሮሚኛ ቋንቋዎችን የማእከላዊ መንግስት የስራ ቋንቋ ኣድርጎ ለመጠቀም የማይቻልበት ምክንያት የለም። የተመረጡትን ቋንቋዎች በመደበኛ ትምህርት ቤቶች በማስተማር ዜጎችን ቢያንስ የባለሁለት ቋንቋ ተናጋሪ (bilingual) እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚቻል ብዙ ሃገሮችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ሃገሪቱን በተመለከተ የኣማርኛና የኦሮሚኛ ቋንቋዎችን በሁሉም የሃገሪቱ ትምህርት ቤቶች በማስተማር በእነዚህ በሰፊው በሚነገሩ ቋንቋዎች በቀላሉ መግባባት መፍጠር ይቻላል። ይህ ሲባል ሌሎች ቋንቋቸዉን ይተዋሉ ማለት ኣይደለም። ሁሉም ልጆቻቸውን በኣፍ መፍቻ ቋንቋቸዉ የማስተማርና በውስጥ ጉዳያቸዉ በቋንቋቸው የመጠቀም መብታቸው የተጠበቀ ይሆናል።
የኣማርኛ ቋንቋ ለምን በሁሉም ክልሎች የትምህርትና የስራ ቋንቋ ኣልሆነም የሚለው ኣስተሳሰብ በኣሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም በላይ በሌሎች ላይ በግድ እንደመጫን ስለሚቆጠር ሃገሪቷን ለገጠሟት ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ኣያስችልም። ለዛሬ ችግሮቻችን መነሾ የሆኑትም የውደታ ሳይሆኑ የግዴታ ተግባሮች ነበሩ ካልን እነዚያን መድገም የለብንም። በሌላም በኩል የኣማርኛ ቋንቋን ኣልማርም ወይም መስማት ኣልፈልግም የሚሉት በጣም ተሳስተዋል እላለሁ። ኣንዳንድ የኦሮሞ ምሁራንና ፖለቲከኞች ኣማርኛን መናገር ብሄርተኝነታቸውን የሚቀንስባቸው እየመሰላቸው ቋንቋዉን ተጠቅመው ኣላማቸውን እንኳን ለማስረዳትና ለማሳመን ሳይችሉ መቅረታቸው በከፍተኛ ደረጃ የመብት ትግሉን እንደጎዳ እነሱም ሳይገነዘቡት ኣይቀሩም የሚል ግምት ኣለኝ።
ኣማርኛ ተናጋሪዎችም ኣንዱ ቋንቋ ከሌላው እንደማይበልጥ ኣውቀው በሃገሪቱ ከዳር እስከ ዳር ማለት በሚቻል ደረጃ የሚነገረውን ኦሮሚፋ በመማር ወገናቸው ከሆነው የኦሮሞ ህዝብ ጋር ያለምንም ችግር እንዲገናኙና ሰርተው እራሳቸውንና ህዝቡን እንዲጠቅሙ ያስፈልጋል። በመጀመሪያ የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን እራሱ በቀላሉ ከተለያዩ ህዝቦች ጋር ለመግባባትና ለመቀላቀል ይረዳል። በሕዝቡም ዘንድ መወደድን ያተርፉል። ቋንቋችንን የሚናገር ሰዉ ስናገኝ ምን ያህል ደስ እንደምለንና ተናጋሪዉንም ምን ያህል እንደምናቀርብ እናዉቃለን።
እውነተኛ ዲሞክራሲና እኩልነት ከዚያም ኣልፎ የህዝቦች ኣንድነት ሊመጣ የሚችለው በመተሳሰብና ኣሁን በፊታችን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ተገንዝበን በተለይም ፖለቲከኞችና ያገባናል የሚንል ሁሉ መጀመሪያ ከራሳችን ጋር ቀጥሎም ከሌሎች ጋር ስለህዝቦች ብለን መታረቅ ስንችል ብቻ ነው።
ሃገሪቷን ለገጠማት የፖለቲካ ኤኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች ሁሉ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝምን ተጠያቂ ማድረግም በምንም መልኩ ሊያስከድ እንደማይችል መረዳትና ያ የህዝቦች መሰረታዊ መብት እንደሆነ እውቅና መስጠትና የገዢዉን መንግስት የከፋፍለህ ግዛ የተንኮል ኣሰራር በጋራ መታገል ያስፈልጋል። ኣለበለዚያ ትግላችን ሁሉ የገመድ ጉተታና የህዝቦቻችንን ሲቃይና መከራ ከማራዘም የዘለለ ኣይሆንም።
* ፍቅሩ ቶላ ከኣውሮፓ:- fiqru2010@gmail.com

No comments:

Post a Comment