Saturday, May 25, 2013
በየፊናችን እየተማረርን መማራችን ለበጎ ነው (አዲስ አበባ)
እቲ ናይ ቀደም ሰላም ዘመን ክምለስ፤
ሰላም ኢልና ንዝመር ብሃደ መንፈስ፡፡…
(ከኤርትራው ተወላጅ ድምጻዊ ርዕሶም ገ/እግዚአብሔር የዘፈን ግጥም የተወሰደ)
ይሄ ኢሣት የሚባል ቴሌቪዥን በትዝታ ባህር እያስዋኘ ጊዜየንም ዕንባየንም እያስጨረሰኝ ነው፡፡ በግማሽ ሜትር ርቀት እሱው ጋ - እቲቪው አጠገብ – ከተደቀንኩ የሚያስነሳኝ የለም፡፡ ቤቴ ሁሌ በአምባጓሮ እንደታመሰ ነው፡፡ ቤተሰብ የሚፈልገውና እኔ የምፈልገው ለየቅል በመሆኑ ትንሹ አምባገነን ሆኛለሁ፡፡ ለነገሩ አምባነንነት የሚጀምረው ከቤት ነውና ይቺ ተፅዕኖየ እየተሰማችኝ መጥታለች፡፡ ምን ላድርግ?
ትናንትና ጧት ላይ ሲሳይና ተወልደ ይበልጡን በግንቦት ወር ዙሪያ የሚያጠነጥንና እልህና ቁጭት ውስጥ የሚከት ዝግጅት እያቀረቡ ሳለ አንድ ሙዚቃ ጋበዙን፡፡ የዚህ ሙዚቃ አዝማች በመግቢያየ ላይ ያስቀመጥኩት ነው፡፡ የአማርኛንና የትግርኛን ቋንቋዎች ተቀራራቢነት የምገልጽላችሁ ይህን እላይ ያስቀመጥኩትን የሁለት ስንኞች ዘለላዎች ወዳማርኛ ላለመተርጎም በመፈለግ ነው – ተቻችሏልና – ከዚህ በላይ እንደምን ይነገር – ያው ነው፡፡ ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ፤ (እኛን የሚያለፋን ክፉ መንፈስ ብቻ፡፡)
በተለይ ከ1960ዎቹ የመጨረሻ ዓመታት አንስቶ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለቀቀው የአውሬው ክፉ መንፈስ በሀገራችን የሠለጠነው ክፉ አውሬ ያላደረገን ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያችንን እንደገና መሥራት እጅግ አስቸጋሪ እስከሚሆንብን ድረስ የአጋንንት ኃይል ተጫውቶብናል፡፡ ተመሳሳይ የባህልና የኢኮኖሚ እንዲሁም የሃይማኖትና የሥነ ልቦና ቀመር ባላቸው የአንዲት ሀገር ሕዝብ መካከል በሌሎች ሀገራት ያልታዬ የመከፋፈልና የዘረኝነት አባዜ ታይቶብናል፡፡ የታዩብንን ኆልቁ መሣፍርት የሌላቸውን ጉድፎች ከመግለጽ ይልቅ ያልታዩልንን ጥቂት መልካም ገጽታዎች መናገሩ ሳይቀለን አይቀርም – እነሱም ካልደበዘዙ፡፡
ለዐይን ይበጃል ተብሎ የተቀቡት ኩል ዐይንን እንደሚያጠፋ ሁሉ የነበሩንን አነስተኛ ችግሮች ለማስወገድ ብለን አንዳንዶቻችን በወሰድናቸው እርምጃዎች የጋራ የትስስር ገመዶችን (social fabrics) ከመበጣጠስ ጀምሮ አጠቃላዩ ማኅበረሰብኣዊና ሀገራዊ ኅልውናችን ጥያቄ ውስጥ እስኪገባ ድረስ ረጂም የጥፋት መንገድ ተጉዘናል፡፡ የሀብትና ሥልጣን ሱስ እንዲሁም አጥንትን ሰርስሮ የገባው የቂም በቀል ልክፍትና የጥላቻ መንፈስ ከደም ዝውውር ሥርዓታችን በቀላሉ ስለማይወጡ እንጂ አሁን ሰዓቱ የንስሃ ነበር፡፡ ንስሃው ቀርቶ ከምንሠራቸው ተጨማሪ ጥፋቶች መቆጠብ በራሱ ትልቅ መልካም ዋጋ የሚያሰጠው ነበረ፡፡ ‘Better late than never’ ይላሉ ፈረንጆች – አርፍዶም ቢሆን አንድን (መልካም) ሥራ መሥራት የሚገባ መሆኑን ለማጠየቅ፡፡ ግን ማን ዐውቆት? የዘመኑንስ መቃረብ ማን ተረድቶት? …
ርዕሶም ገ/እግዚአብሔር ለአንድ ድሃ ዘመዴ የሚሆነኝን ዕንባ ሊያውም በጧቱ አስነባኝ፡፡ እግዚአብሔር ይባርከው፡፡ የብዙ ልጆች አባት የነበረውና በሻዕቢያ ሠርጎ ገቦች የተገደለው የነምሥግና ደግ መንፈስ፣ የነዶክተር ፍስሐጽዮን መንግሥቱ ደግ መንፈስ፣ የሌሎቹም የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛት የኤርትራ ዕንቁ ልጆች ደገኛ መንፈስ ከመለኮት ጥበቃ ጋር በነፍስና በሥጋው አይለዩት፡፡ ልጅነቴን አሳየኝ፡፡ የደጉን ዘመን አሻራዎች በዘፈኑ አስቃኘኝ፡፡ አዲስ አበባ ላይ በተወሰኑ ቦታዎች ፈልጌ ስላጣሁት ይህን ዘፈኑን በኢሜሌ ለሚልክልኝ ወገን – ምን ሽልማት ላዘጋጅ እባካችሁን – አዎ – አዲስ አበባ አሥመራ የደርሶ መልስ የመኮንን ነጋሽ ወይም የሀጂ አብዱ አሊያም የወሎ ፈረስ ሀገር አቋራጭ ትኬት በአድራሻው እልክለታለሁ፡፡ በእነዚህ አልሄድም ለሚል የንሥር አሞራ ትኬትም አለኝ፡፡ (እነዚህንና ሌሎችን የሕዝብ ትራንስፖርት ማኅበራት የሚያስታውስ ይኖር ይሆን? ዘመኑ እኮ እየራቀ ሄደ!)
ርዕሶምን ወደድኩት፡፡ እንዲህ ይላል – ጦርነት ይብቃን፤ እንደ ቀድሞ ሠናይ ዘመን ወደ አንድነታችን እንመለስ፤ የአንድ ቤተሰብ ልጆች ተበታትነን አንቅር፤ በአክሱም በአድዋ በጎንደር በጎጃም ባህር ዳር አድርገን በአውቶቡሶችቻችን ልክ እንደዱሮው በፈለግነው አቅጣጫና ወደፈለግነው ቦታ እንደርሱ አገላለጽ ወዳፈተተን የኢትዮ-ኤርትራ ግዛት እንዳሻን እንመላለስ፤ ከሸዋ ወደ አሥመራ ያላንዳች ኮንቮይና ያላንዳች የጉዞ ሰነድ በአንድ ሀገር ልጅነት እንዘዋወር፤ በምፅዋ በሃሰብ በአውሣ በደሴ በኮምቦልቻ ከሚሴ አድርገን ትሬንታ ኳትሮዎቻችን፣ ኤን ትሬዎቻችን፣ ሎንቺናዎቻችን እንደቀድሞው ደጉ ዘመን ሰውም ሆነ ዕቃ እየጫኑ ይመላለሱ፤ (በተንኮለኞችና በመሠሪዎች) ከሸልቶው የተለየው ሪሞርኪ ይቀጠልና መኪናው የተሟላ አቋም ይኑረው – የተበጠሰው ግንኙነት ይቀጠል፤ በሃይማኖትና በቋንቋ ልዩነቶች መቆራቆስ ይብቃ… ይለናል – ሰሚ ከተገኘ የርዕሶም ዘፈን ታሪካዊ ነው፡፡ የቀድሞውን ዘመን በጨረፍታም ቢሆን ላዬ ለእንደኔ ዓይነቱ ከርታታ ዜጋ ይህ ዘፈን ካላስለቀሰው ሌላ ምንም ሊያስለቅሰው የሚችል ነገር የለም – አለበለዚያም ራሱ አስለቃሽ ነው ማለት ነው፡፡
የደረስንበት ዘመን ለወሬ ብዙም የሚያምር አይደለም፡፡ ከአሁን ወዲያ ወሬና የፖለቲካ ትንተና ሳይሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ብቻ ነው ሀገራችንን ከወረሯት መዥገሮችና ገሃነማዊ የእሳት ትሎች ነጻ ሊያወጣት የሚችል፡፡ በመቶዎች የአስተሳሰብና የአመለካከት ጎራዎች እየተቧደኑ በነገር ጅራፍና በአሽሙር ጦር መተጋተጉ፣ በመቶዎች የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት እየተደራጁ በቃላትና በተቃውሞ ሰልፍ ጠላትን በምናብ ‹ማደባየቱ›፣ ወጡ ሳይወጠወጥ በርቀትም በቅርበትም በህልማዊ ሥልጣን ነፍዞ መቆራቆሱ፣ ተመሳሳይ በሽታን ለማከም ተመሳሳይ የዘረኝነት ክትባትን ተከትቦ በዚያ ያረጀ ያፈጀ የጎጠኝነት ፈሊጥ ተሰባስቦ የ‹እገሌ ብሔር ነጻ አውጪ ድርጅት› እያሉ በወያኔዊ ቅኝት መጓዙ፣ ከአንዱ እያኮረፉ ወደሌላው በመግባት ከነባሩ የበሰበሰና የገማ ስብዕና መገለጫ ጋር አዲስና የቆዩ እንቅስቃሴዎችን ማጨንገፉ፣ ለሥልጣንና ገንዘብ ሲባል በሕዝብ የማቴሪያልና የሞራል ሕይወት መጫወቱ… ላለፉት 22 ዓመታት ተሞክሮ ‹እነሱ›ን ከመጥቀም ባሻገር ‹እኛ›ን ጨምሮ ሁላችንንም የሚጠቅም አንዳችም ለውጥ ባለማምጣቱ ከዚህ በኋላ በዚህ የተበላ ዕቁብ መንገድ መራመዱ ዋጋ የለውም – የሕዝብን የነጻነት ፍለጋ መንፈስ በማቀጨጭና አለኝታን በማሳጠት ረገድ የተጫወተው ሚናም ቀላል አይደለም – ሕዝቡን ሰጥ ረጭ ያደረገውም ይሄው ነው (‹አገባሻለሁ ያለ ላያገባሽ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ› የሚባለው ይህን ዓይነቱን መጥፎ አጋጣሚ ለመግለጽ ነው)፡፡ ከአሁን በኋላ ማድረግ የሚገባን ‹እነሱ›ንም ‹እኛ›ንም በእኩል የሚጠቅም፣ ሀገራችንን ከውርደት የሚያድን፣ ሕዝባችንን ካለመኖር ወደመኖር የሚያመጣ አዲስ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመር እንጂ የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባየ እንዲሉ በጀመርነው የንግግርና የጽሑፍ እንካስላንትያ መቀጠሉ ብዙም ፋይዳ ያለው አይመስለኝም፡፡ ከነተረቱ የወሬ የለውም ፍሬ ነው፡፡ ሕዝቡ የሚፈልገው ዜና ‹ እንደዚህ የሚባል ጠንካራ የተቃዋሚ ኃይል እነዚህን ጠቅላይ ግዛቶች ተቆጣጥሮ ወደመናገሻዋ ከተማ ወደ አዲስ አበባ በከፍተኛ ፍጥነት እየተጓዘ ነው› የሚል እንጂ የነገር ወንጭፍ ሰልችቶታል፡፡ የዚያ ዓይነት ዜና በተነገረ ማግሥት – ለዚያ ዓይነቱ ዜና ያብቃን እንጂ – በየትኛውም ኢትዮጵያዊ ሥፍራ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ ለማንኛውም ጥቂት ነጥቦችን እንዳመጣጣቸው ላክልና ላብቃ፡፡
1. ቪኦኤ ‹ወጣቱ የፖለቲካ ተንታኝ› እያለ የሚያሞካሸውን የጁሃር ሲራጅ መሃመድን የኢሣት ቃለ መጠይቅ ተከታተልኩ፡፡ እጅግ የሚመስጥ ነው፡፡ ልጁም የዋዛ አይደለም፡፡ ጥሩ አንባቢ ነው፡፡ የልጅ ዐዋቂ ቢባል አያንሰውም፡፡ ይደግ ይመንደግ፡፡ ከዐይን ያውጣው፡፡ እንደልደቱ አያሌው የትንታግ አንደበት ባለቤት ነው – ያነጻጸርኩት አንደበታቸውን ነው፤ አንደበት ደግሞ የእውነተኛ ማንነት መገለጫ አይደለም – ተግባር ነው ዋናው የማንነት ማሳያ፡፡ የተሰማኝን ቅሬታ ግን በእግረ መንገድ ልግለጥ፡፡ እናም ለጁሃር ብቻ ይህችን ጸሎትና አስተያየት ልሰንዝር፡፡
የተሟላ ኢትዮጵያዊ ስብዕና እንድትላበስ፣ ከሌንጮ ለታዊ ሻዕቢያ ተከል ኋላቀር አስተሳሰብ ነጻ የወጣህ እንድትሆን፣ ከአንድ ብሔር ተቆርቋሪነት ወጥተህ የሁሉም ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች አለኝታ እንድትሆን ፈጣሪ ይርዳህ፡፡ ይህን የምለው በቃለ መጠይቁ ከተናገረው ሳይሆን ካልተናገረው ነገር ግን ለኔና መሰል ወገኖቼ ከዐይነ ውኃው ከሚገባን ተነስቼ የተረዳሁትን ነው፡፡
ጉዳዩ እንዲህ ነው፡፡ በእንግሊዝኛው paralanguage ይሉት ነገር አለ፡፡ በቋንቋ የመግባባት ሂደት ቀላል አይደለም – እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ እየመረቅሁህ የምረግምበት፣ እየሰደብኩህ የማመሰግንበት፣ ፍቅሬን እየገለጥኩልህ ጥላቻየን የማንጸባርቅበት የአነጋገር ሁኔታ አለ፡፡ ወርቃማ ቃላትን፣ ሰውነትን በሃሤት የሚያለመልሙ ሀረጋትንና ዐረፍተ ነገሮችን በአንደበቴ እየተናገርኩ ባለሁበት ሁኔታ የሰውነት እንቅስቃሴየና መላው የአነጋገር ድባቤ ሲጠና ግን ከምናገረው በስተጀርባ የተለያዩ የእውነተኛው ስሜቴ ነጸብራቆች የሆኑ ተቃራኒ መልእክቶች ሊተላለፉ እንደሚችሉ መታወቅ አለበት፡፡ ቋንቋ ብቻውን እውነተኛውን ማንነታችንን አያሳይም ማለት ነው፡፡ ድባብና ዐውድ እንዲሁም ድምፀት ቋንቋ አከል የመግባቢያ ሥልቶች ናቸው፡፡ ሁሉንም እንደወረደ ከወሰድነው ለተሳሳተ ግንዛቤ ልንጋለጥ እንችላለንና ንግግርን ከዐይነ ውኃ ጋር በማዛመድ የሰውን እውነተኛ ማንነትና ስሜት ከተራው ሥነ ልሣናዊ ዐውድ ወጣ ባለ መንገድ ለመረዳት መሞከር ይገባናል፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ማለት ቢቻልም ለአሁኑ ይብቃን፡፡
ጁሃር የኢትዮጵያን ስም መጥራት በልጆች አነጋገር የሚደብረው ይመስለኛል፡፡ በዚያ ቃለ መጠይቁ ጠያቂው ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ ለመጥራት ቢሞክርም ተጠያቂው ገሸሽ ሲያደርግና ወደኦሮሚያ ክፉኛ ሲያዘነብል አስተውያለሁ ፤ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ፡፡ ግን ለምን እንዲህ ሆነ? ብለን መጠየቅ እንችላለን፡፡ ምክንያቱን ከመገመት በስተቀር በግልጽ ለማወቅ ይከብዳል፡፡
ጁሃር የወያኔ ዘመን ምሁር ነው፤ ያልዘሩት አይበቅልምና የተቃኘበት ዘፈን ሁሉ ከኮዝሞፖሊታኒዝም አነስ ሲልም ከኢትዮፒያኒዝም እጅግ ባፈነገጠ መልኩ የአንድ ብሔር አቀንቃኝ ሊሆን የመቻሉ ምሥጢር ጊዜው ያቀረበለት ምርጫና እርሱም ምናልባትም ሳይወድ በግዱ የተቀበለው አካሄድ ይመስላል፡፡ እናም እንደ ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሣ ጥናታዊ ዘገባ ከ80 በመቶ በላይ በጋብቻና ወሊድ ትስስር እርስ በርሱ ተጋምዶ እንደውሃና ወተት የተዋሃደውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ‹ኦሮሞ፣ አማራ …› እያለ በወያኔ በተቀደደለት ቦይ ለመፍሰስ መሞከሩ ትንሽ አሳስቦኛል፤ ከልጅ አንደበት ይህን መሰል ፍካሬ የማንበቤ ዕድለቢስነቴም አስቆጥቶኛል፡፡ ይህ ብርቅዬ ልጃችን እንደገና ቁጭ ብሎ ማሰብ ይኖርበታል – እኔ እሱን የኔ ብዬ ያለመሻከክ እንድቀበለው እርሱም የጋራ እናታችንን እማዬ እንዲላት እጠብቃለሁ – የእንጀራ እናቱ አይደለችምና፡፡ ገና ወጣት እንደመሆኑ ቅኝቱን ለብልጣብልጥነት ሥልት ሳይሆን ለእውነት ብሎ ካስተካከለ በመለኮታዊ የዕውቀት ትውፊት ታድሏልና ሁላችንንም የሚጠቅም የሁላችንም ተስፋ ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለው፡፡ አሁን በያዘው ጎዳና ቢቀጥል ግን አዝናለሁ የትም ይደርሳል ብዬ አላስብም፡፡ ላስፈራራው አይደለም፡፡ እውነትን መናገር ስላለብኝ ነው፡፡ ዘመኑ የጎጥና የሸንተረር፣ የነገድና የአጥንት ጥራት ሳይሆን የሰብኣዊነት ነው፡፡ እንስሳት የዕድገት ደረጃቸው እንደሚፈቅድላቸው ዐይጥ ከዐይጥ ፣ ድመት ከድመት፣ ውሻም ከውሻ… ይሰባሰቡ፡፡ ሰዎች ግን ሰዎች ስለሆንን በደምና በአጥንት ሳይሆን በሰውነታችንና በሀገራዊ የጋርዮሽ ዜግነታችን እንሰባሰብ፡፡ (ከአሁን በኋላ ደግሞ መታወቂያችን ላይ ‹ብሔር› የሚል ነገር መኖር የለበትም፤ ዜግነት የሚለው በቂ ነው፡፡)
‹ከአነጋገር ይፈረዳል፤ ከአያያዝ ይቀደዳል› ነውና ጁሃር የአዲሱ ዘመን ሐዋርያ መሆን ከፈለገ በዘር የታሸውና ኦሮምኛ ተናጋሪን ሕዝብ ከኢትዮጵያ አጀንዳ እየነጠለ ኦሮሚያና ኢትዮጵያ የሚባሉ ልይት ኑባሬዎች ያሉ ያህል መስበኩ አዋጪ ካለመሆኑም በተጨማሪ ሌላ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ አንድን ሕዝብ በዘርና በሃይማኖት እየነጣጠሉ አንዱን ጨቋኝ ሌላውን ተጨቋኝ እያደረጉ ማቅረብ ስህተት ነው፡፡ በመሠረቱና እንደእውነቱም ከሆነ ተጨቋኝ እንጂ ጨቋኝ ሕዝብ የለም፡፡ እርግጥ ነው – ከአንድ ሕዝብ አብራክ የሚገኙና ከዚያ ሕዝብ የተወሰነውን ክፍል አስተባብረው የራሳቸውን ህልምና ቅዠት በሌሎች ላይ የሚጭኑ አሰለጦች እንዳሉ ሩቅ ሳንሄድ እዚሁ ሀገራችን ውስጥ በከባድ ክፍያ ተምረናል – ይህን የፈጠጠ ጠባሳ ለመሻር ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብንም መገንዘብ አለብን፡፡ ከዚያ ውጭ አማራ/ትግሬ የሚባል ጨቋኝ ኦሮሞ/ደቡብ የሚባል ተጨቋኝ ነበረ/አልነበረም በሚል ጉንጭን ማልፋት ተማርኩ ከሚል ቀርቶ ከደንቆሮም ሰው አይጠበቅም – ከዚያ የተሻለ ፍሬያማ ውጤት የሚያስገኝ ሥራ ባልጠፋበት ዘመን የዱሮ ታሪክ እያነሱ ወርቃማ ጊዜን ማባከንም ሞኝነት ነው፡፡ አማራው በኦሮሞው ውስጥ፣ ትግሬው በአማራውና በኦሮሞው ውስጥ ፣ ጉራጌው በሃዲያውና በሰሜኑ ውስጥ፣ ሰሜኑ በምዕራቡና በምሥራቁ ውስጥ የአንዱ ደም በሌላው ደም ውስጥ እየቀለጠ ሰምና ወርቅ ሆነው ይኖሩ እንደነበር ከዘነጋን የተሸረጠብን አንዳች ክፉ መንፈስ፣ ተዳብሎን ያለ ሸርና ተንኮል አለ ማለት ነውና ራሳችንን እንመርምር፡፡ የጋራ ችግርን በጋራ መፍትሔ ማስወገድ እየተቻለ ሽል ምንጠራ ውስጥ መግባት አስፈላጊም ተገቢም ወቅታዊም አይደለምና በተለይ ምሁራን የተባላችሁ ወገኖች ተጠንቀቁ፡፡ መማር ጥሩ ነው – ነገር ግን ዐወቅሁ ብላ መጽሓፋቸውን ያጠበችውን የቄሱን ሚስት መሆን አይገባም፡፡ ሕዝብ ‹ማን ይምራህ? እንዴት ይምራህ? ችግርህ ምንድን ነው?› ተብሎ ይጠየቃል እንጂ ያላሳከከውን በማከክ ያልነበረና የማይፈለግ ቁስል መፍጠር ነውር ነው፡፡ እኛ እንደሕዝብ አብረን ነው የኖርነውና እየኖርንም ያለነው፡፡
ከኔ ቤት ቀጥሎ ተስፋጋብር አለ፤ ከተስፋጋብር ቤት ቀጥሎ የሻመና ቶቆ ቤት አለ፤ ከርሱ ቤት ፊት ለፊት የደቻሳና የጫልቱ ቤት ይገኛል፤ ከነሱ ቤት በስተኋላ ግደይና ስንሻው ቡና እየተጠራሩ በሀዘኑም በደስታውም እየተገናኙ በሰላም ይኖራሉ፡፡ በአብረኸት ሠርግ ጣይቱና ዘርመጪት ልባቸው እስኪጠፋ ይጨፍራሉ፡፡ በሐጎስ ቤት የክርስትና ድግስ ይነጋልና አበቅየለሽ ታፋቸው እስኪገነጠል ጮቤ ይረግጣሉ፡፡ በፈይሣና በካሣሁን የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ፍትዊና ሃንቆሬ ስቅስቅ ብለው ያለቅሳሉ … እኛ እንዲህ ነበርን፤ ነንም፡፡ ባልና ሚስቶቹ አደፍርስና አምለሰት፣ ዘርዓይና ገመቺሣ፣ ዘርትሁንና ጎይቶም፣ ቦጋለና ትብለፅ ያፈሯቸው ልጆች እነሜሮን ሣሚ ዳኒ ቲቲ … የጋራ ሀገር ይፈልጋሉ፡፡ በዘርና በጎሣ የተሸነሸነች ሳትሆን እንደጥንት እንደጧቱ የዝውውር ነጻነት ያልተገደበባትና በዘር ምክንያት የመፈናቀል ጣጣ የሌለባትን ኢትዮጵያ ይፈልጋሉ፡፡ አሁን ለተጨማሪ ጊዜ ይህንን ሕዝብ እንዴት ነው ኦሮሚያ ጎጃሚያ ጎንደሪያ ወሎዊያ … እያልን እንደደሮ ሥጋ የምንበልተው? ግፍ አይደለም? ትንሽ ማፈር አለብን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደፍልስጥኤምና ኮሶቮ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሦርያውያን አጥንት ድረስ የዘለቀ የእርስ በርስ ጥላቻ ላይ ገና አልደረሰም – ይህ እውን እንዲሆን የመሪዎች ጥረት ቢኖርም፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ጠብ የለብንም – የብልህ አመራር እጦት እንጂ፡፡ በፍቅርና በመቻቻል የሚኖር ሕዝብ በዘር እየለዬ በር ሳያንኳኳ በየቤቱ የሚገባን ሌባና ቀጣፊ አይቀበልም፡፡ እርግጥ ነው – ይህንን አብሮነት ለመበጣጠስ ብዙ ቢሞከርም እንደምንም ይዘነው እስካሁን ድረስ ዘልቀናል – አሁን ቆም ብለን ማሰብ ይገባናል፤ ምክንያቱም ነገሮች እንዳሉ የማይቀጥሉበት ሁኔታም አለና፤ ለዚህ ደግሞ ምሁራን ትልቅ ድርሻ አላቸው – ከየቀለሱት የግል ጠባብ ዓለም እየወጡ ሰፊ ሜዳ ላይ ይገናኙ፡፡ በቀናነት ይወያዩ፤ የሚበጀንንም ይወስኑና በጋራ ለጋራ ድል ያነሳሱን፡፡ ዘርና ሃይማኖት ደግሞ በትግሉ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና ስለሚያሳድሩ እነዚህ ልዩነቶች በየትኛውም ሚዲያም ይሁን መድረክ ግዘፍ ነስተው መራገብ የለባቸውም፡፡ የሌሎች ሀገሮች መንግሥታት ሕዝባቸውን አንድ አድርገው ለመግዛት ቀና ደፋ ሲሉ በተገላቢጦሽ የኞች የምንላቸው መሠሪ ልጆቻችን እያለያዩ ሲቀጠቅጡን ኖረዋል፡፡ ሰላምና ፍቅር ጠላታቸው የሆኑ ያህል የሕዝብን ሰላምና መረጋጋት አይወዱም፡፡ የብልጽግናቸውና የሥልጣናቸው እርዝማኔ መሠረት የሕዝብ ስቃይና መከራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እነሱም እኛም ዕድለቢሶች ነን፡፡
ጁሃርን በሚመለከት አንድ ነገር ደግሜ ልናገር – ይህ የደስ ደስ ያለው መልከ ቀና ወጣት ‹እኔ መቼ እንዲህ አልኩ? መች ወጣኝ?…› ሊል ይችላል፡፡ እውነቱን ነው፡፡ እኔ ነኝ በጥራዝ ነጠቃዊ የሥነ ልቦና ‹ዕውቀቴ› ልጁን ያነበብኩት፡፡ የምንደሰትበት እንጂ የምናዝንበት አጋጣሚን ፈጣሪ ያርቅልን እስኪ፡፡
2. ልጅ ተክሌ ወይም ተክለ ሚካኤል ከካናዳ በቅርቡ የጻፈውንና ሌላም ጊዜ የሚጽፈውን ሁሌ እከታተላለሁ፡፡ የእውነትን ክኒን እንዳለች ለመዋጥ እጅግ መራር በመሆኗ ለብዙዎች አስቸጋሪ ናት፡፡ ውሸት ግን አንጎልን ወደተፈለገው አቅጣጫ እየጠመዘዘች ስለምታነሆልል እርሷን ለማዳበልና በቤተሰብነት ለመያዝ የማይጣደፍ የለም፡፡ በተለይ በአሁኑ ዘመን የሀሰት ጓደኞች ሥፍር ቁጥር የላቸውም፤ እውነት እየኮሰመነች ናት – መጨረሻዋ ያማረ ቢሆንም፡፡
ተክሌ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ ባህል በዳበረበት የምዕራቡ ዓለም ከአሥር ዓመት በላይ የኖረና እውነትን ተናግሮ ከመሸበት ለማደር የቆረጠ ወጣት ይመስላል (ልደቱን እንዴት እንደወደደው ግን አልገባኝም – ወይም ስለመውደድ አለመውደዱም የተሳሳተ ግንዛቤ ይዤ ሊሆን ይችላል፡፡)፡፡ ለሀገራችን ፊት ለፊት የመሞከሻሸት ዞር ሲሉ ግን በሃሜት የመጎሸማመጥ ባህል ይህ የተክሌ ዓይነቱ አካሄድ ታላቅ መፍትሔ ሥራይ ነው፡፡ በቃ – ብዙ ነገሮች ይብቁን፡፡ አየናቸው – ሞከርናቸው – ተጎዳንባቸው እንጂ አልተጠቀምንባቸውም፡፡ ስለዚህ አካፋን አካፋ እንበል፡፡ እናም የእውነትን ዘገር ከያዝን ስለማንም ይሁን ስለምንም የሚሰማንን እንነጋገር፡፡ አነሳሳችን በቀናነት ይሁን እንጂ አለባብሰን መሄድን በመተው ስሜትን በማይጎዱ ቃላት አንገትን በማያስደፉ ውብ አገላለጾች ወዳጅ ዘመድን እንውቀስ፤ እንተች፤ በሳይቃጠል በቅጠል እንተራረም፡፡ እየተሸፋፈነ የሚሄድ ቁስል መጨረሻው ካንሰር ነው፡፡ ‹ጨዋ ሲጋባ የተፋታ ያህል ነው› የሚለውን ብሂል በደንብ እናጢነውና አፍረጥርጠን መነጋገርን እንልመድ፡፡ በጀርባ ከመተማማት በግልጽ ተወያይተን ቅሬታን ማስወገድን ብንለምድ ተጠቃሚዎች እንሆናለን፡፡
በለውጥ ኅልውናም እንመን፡፡ አንድ ሰው ትናንት ሌባ ከነበረ ዛሬ ጨዋ የማይሆንበት ምክንያት የለም፤ ትናንት ወያኔ ከነበረ ዛሬ ፀረ – ወያኔ የማይሆንበት ምክንያት የለም፤ ትናንት ውሸታም ከነበረ ዛሬ እውነት ተናጋሪ የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም፤ ዋናው ለውጡ አሳማኝና ትክክለኛ ነው ወይ የሚለው ነው፤ ለውጡ በርግጥ የባሕርይ ለውጥን ያስከትላል ወይ ብለን መፈተሸ ነው ያለብን፤ ያን በጥልቀትና ከተለያዩ አቅጣጫዎች አንጻር መመርመር ይገባናል፡፡ ይህን የምናደርገው መንሸራተት እንዳይኖርና ሠርጎ ገብን ለመከላከል ነው፡፡ ለውጡ ለሥልት ነው ወይንስ ሃቀኛ ነው ብለን እንፈትሽ እንጂ አንድ ለውጥ ስናይ የለውጡ አስፈሪነት እንዳባተተን ወይም እንዳስበረገገን ያህል ድንገት ዱላ እየመዘዝን አናት አናትን መቀጥቀጥ ወይም ብዕር እያወጣን በቃላት እሩምታ ንጹሓንን ድባቅ መምታት ተገቢ አይደለም፡፡ ፀረ ለውጥ ሆነን ትግሎችን ወደኋላ ማስኬድ የነጻነት ጠላት መሆን ነው፡፡ በነገረኛ ብዕርና ፓልቶክም ሰዎችን ከመጠጋታቸው አናባርር፡፡ ብዙ ወገኖቻችን ራሳቸውን ከትግል ያራቁትና እያራቁ የሚገኙት የይሉኝታቢስ ወንድሞቻችንን ይሉኝታቢስና ሚዛን የማይደፋ የስድብና የዘለፋ ዛቻን እየፈሩ እንደሆነ ይነገራልና ከእንግዲህ እነዶኪሾትና እነአያ እንደልቡ ጥንቃቄ ቢያደርጉ ይመረጣል፡፡ ከሁሉም ከሁሉም በቅድመ ሁኔታ ያልታጠረ ቀናነትንና መደማመጥን እንላበስ፤ ከአሉታዊነት ይልቅ አወንታዊነት ጠቃሚ መሆኑን እንገንዘብ፡፡ ለማሰብ ጊዜ ይኑረን፡፡ አንድን ነገር ለማጣራት ጊዜና ትዕግሥት ይኑረን፡፡ በአንድ ቅኝት መጓዝ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናልና ዙሪያ ገባችንን እያየን ራሳችንን በተገቢው መንገድ እናዘምን፡፡ ደግሞም እርስ በርስ በከንቱ አንጠፋፋ፡፡ ለሚያልፍ ዘመን የማያልፍ ትዝብት አናስቀምጥ – እንተማመን ፡- ሕዝቡም ሆነ ታሪክ ሁሉንም ለይቶ ያውቃል፡፡ ማን ለምን ምን እንደሚያደርግ በዚህ ዘመን ለማንም ድብቅ አይደለም፡፡ የ‹ዝምብ ልጃገረድ› በምትታወቅበት ሀገር ውስጥ ዘረኝነት ወይም ይህን መሰል ሌላ ከፋፋይ ሥልት በማታገያነት ለምን ጥቅም ላይ እንደሚውል የማያውቅ ይኖራል ብሎ መገመት ጅልነት ይመስለኛል፡፡ በተጨማሪም ‹እንግዲህ ጀመረው!› ‹አሄሄ… ያ ሰውዬ ያን የነገር ጭቃውን በነእንትና ላይ ሊለጥፍ ተነሣ…› ከመባል ይልቅ በገምቢ አስተያየት ሰጪነት በሰዎች መሃል መወሳት ትልቅ መታደል መሆኑን እንረዳ፡፡…
ስህተትን የማይሠራ የሞተ ብቻ እንደሆነ አምነን ስህተት ከሠራን ያን ስህተት ነቅሶ ለማውጣትና የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ማመንታት የለብንም፡፡ ከነባር ሥርዓቶች የወረስናቸውን ፀረ ዴሞክራሲያዊ የትዕቢትና የማንአለብኝነት ባሕርያትን አክ እንትፍ እንበላቸው፡፡ ጎዱን፡፡ አብረውን የሚዘልቁ ከሆነም ገና ብዙ ይጎዱናል፡፡ ትዕቢት ሣጥናኤልን ከክብሩ አውርዶታል፡፡ ትዕቢት ተቆጥረው የማያልቁ ምድራውያን ታላላቅ ሰዎችን ከክብር ሥፍራቸው አዋርዷል፡፡ ዝና ይጠፋል፤ ሀብትም ይበናል፤ ማናቸውም ነገር እንዳለ እንደማይቆይ ተረድተን ትህትናንና መከባበርን መላበስ፣ ትዕቢትን መጠየፍ ይኖርብናል፡፡
ዛሬ ሰዎች የወደዱን ለምንድነው ብለንም እንጠይቅ፡፡ የወደዱን ምክንያት አላቸው፤ ያ ምክንያታቸው ግን ሊጠሉን ሲጀምሩ እየደበዘዘ ይሄድና ለመወደዳችን ያወጣነው ወጪና የተነሳንበት ወረት እንደጤዛ እንደሚረግፍ ዕንወቅ፡፡ ዝናን ማትረፍ ከባድም ቀላልም ነው፡፡ ማቆየቱ ግን ሸክም ነው፡፡ ምክንያቱም አንዳንዴ ክፉ መንፈስ እየገባብን የትዕቢትና የትምክህት ልምሻዎች ይኮደኩዱንና ልባችን በውዳሤ ከንቱ ይማስናል፡፡ ያም ልክ እንደጥንቱ የአፈ ታሪክ ንጉሥ ዕርቃናችንን መሆናችን እስከሚረሳን ድረስ ራሳችን ለራሳችን በምንፈጥረው ዓለም ውስጥ እንዳክራለን – ለተወሰነ ጊዜም በእኛው የዕውር ድንበር ዓለም ውስጥ ሌሎችንም ልናዳክር እንችላለን፡፡ ያኔም እንደገና በተምኔት ከፍ ከፍ እንልና መነሻችንን እንረሳለን – ‹ታሞ የተነሣ ፈጣሪን ረሳ› እንዲሉ ዓይነት፡፡ የምድራችን ትልቁ ችግር እንግዲህ ይህ እዚህ ላይ እያየነው ያለነው ጉዳይ ነው፡፡ ማንንም አላሰብኩም፤ እናንተም ማንንም ሳታስቡ አጠቃላይ እውነታውን ብቻ ተረዱልኝ፡፡
የኢትዮጵያውያን ችግሮች መባቀያ ደግሞ ይሄው ብቻ እስኪመስል ድረስ ሥር ሰድዷል፡፡ የዚህ ሁሉ ወፈ ሰማይ የፖለቲካ ድርጅት ምሥረታ ምሥጢሩ ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡ ሀገርን ነጻ ማውጣት ሱቅ በደረቴ ንግድ የመጀመር ያህል ቀላል ይመስል ‹እኔ በእገሌ ድርጅት ሥር ገብቼ የነእገሌ ታዛዥና ተላላኪ ልሆን? እነሱ ደግሞ ብለው ብለው የኔ አለቃ ሊሆኑ? አላውቀውምና ነው…› ከሚል ትዕቢት በመነሣት አዳሜ በውጪም በውስጥም የየራሱን ድርጅት ያቋቁማል – ይህም በትንሹ ከንቱነት ነው – እልፍ ሲልም ድንቁርና ነው፤ ይህ ዓይነቱ ጠባብ ጅማሮ ስንዝር ሳይሄድ ይፈርሳል፡፡ ጨዋታው ፈረሰ ዳቦው ተገመሰ ዓይነት የልጆች ዕቃ ዕቃ ጨዋታ፡፡ … ስለሆነም በማንኛውም ዘርፍ ለሀገር እንታገላለን የምንል ወገኖች ትልቁ ጠላታችን ይሄ ትዕቢት የሚሉት ልብ አሳባጭ የክፉ መንፈስ ውላጅ ነውና መድሓኒቱን ገዝተን ወይም ጠበል ቢጤ አስመጥተን አጠገባችን እናስቀምጥ፡፡ ትዕቢት ራሳችን ላይ መውጣቱ ሲሰማን ወይም ሰዎች ሲጠቁሙን ቶሎ ብለን እንዋጥና ወይም እንጠመቅና እንደወያኔ ብዙ ጥፋት ሳናደርስ እንፈወስ፡፡ አለበለዚያ ይህች ሀገር ለረጂም ጊዜ ትሰቃያለች(ያነበብኩትን ወይም የሰማሁትን የትንሣኤ ዘመን ወሻክቼ ባልተጨበጠ ተስፋ የሰውን ሆድ መቀብተት አልፈለግም እንጂ ሁሉም የክፋት ዘመን እንደሚያበቃ ከነምልክቱ ልጠቁም በወደድኩ ነበር፡፡) ለማንኛውም ትዕቢትና ውድቀት ጓደኛሞች መሆናቸውን እንረዳና መፍትሔ እንፈልግ፡፡
3. በሀገር ቤት የ‹ፀረ ሙስናው ትግል› ተጧጡፏል፡፡ እሰዬው ፣ ይጧጧፍ፡፡ በዚህ ሽኩቻ ውስጥ የተረገዘ ሀገርን የሚጠቅም ነገር ይኖረው ይሆናል፡፡ አለበለዚያማ … ቆይማ ቀጣዩዋን ክስ ባጭሩ እንቃኝ፡፡
ኢየሱስን ጠላቶቹ ሊፈትኑት ፈለጉና አንዲት ሴት ይዘው ወደርሱ በመቅረብ ‹ ኢየሱስ ሆይ፤ ይህቺን ሴት ስታመነዝር አገኘናት፤ በሙሤ ሕግ መሠረት በድንጋይ ተወግራ እንድትሞት ሕጉ ያዝዛል፡፡ አንተስ ምን ትላለህ?› ይሉታል፡፡ ኢየሱስም ‹ከእናንተ ምንም ዓይነት ኃጢኣት ያልሠራ የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወርውርባት› ይልና አንገቱን አዘቅዝቆ አፈሩ ላይ ይጫጭር ገባ (ምን እንደጫጫረ እስካሁን አልታወቀም ይባላል፡፡) ቀጥ ሲል ከተከሳሽዋ ሴት በስተቀር ሁሉም አንድ ባንድ ሄደው ማንም የለም፡፡ ‹አንቺ ሴት ከሳሾችሽ ወዴት አሉ?› ብሎ ይጠይቃታል፡፡ ጥለዋት እንደሄዱም ትገልጽለታለች፡፡ … ‹በይ ከአሁን በኋላ ኃጢኣትን አትሥሪ› ብሎም በነጻ ያሰናብታታል፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከፍርድ ቤት ወደቤት ሄደች እነእስክንድርን የሚያስባቸው ከሰውም ሆነ ከአምላክ ግዛት ጠፋ እንጂ፡፡ በሞራል ትምህርቶች ይህ የክርስቶስ ምሳሌ የሚስተካከለው ያልተገኘ ትልቁ ምሰሶ ነው፡፡ ኃጢኣትን የማይሠራ ማን አለ? ማንም፡፡ ትልቁ መልካም ተስፋ ግና ከኃጢኣት ለመመለስ ያለን የማይገፈፍ መብት ነው፡፡ ይህን መብት ማን ይጠቀምበት? የባከነ መብት! ብዙዎች የናቁት ዘመን የጣለው መብት?
አለበለዚያማ ብዬ ወዳቋረጥኩት ሃሳብ ልመለስ፡፡ አለበለዚያማ ከዝንጀሮ ቆንጆ ተመርጦ አንዱዋ ባሪያ ሌላዋ ሞናሊዛ ሊሆኑ ይቻላቸው ነበርን? እናም የምናውቀውን ሀገራዊ እውነት ስንፈትሸው በወያኔ ሥርዓት ውስጥ ካለሙስና እስትንፋሱ የምትቀጥል አንድም ባለሥልጣን የለም – በየትኛውም መንገድ ይሁን ሙስና ውስጥ መዘፈቁ አይቀርም – በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ፡፡ ሙስና ደግሞ ዓይነቱና መልኩ ብዙ ነው፡፡ ሙስና እንኳንስ በሌሎች መሥሪያ ቤቶች በትምህርት ተቋማትም ሳይቀር ተንሰራፍቶ የማለፊያ ነጥብን ለማሟላት በዓይነት ከሚቀርብ የንብረትና የወሲብ ጉቦ አንስቶ እስከገንዘብ ድረስ ለመምህራንና ለትምህርት ባለሙያዎች እንደሚሰጥ በስፋት ይነገራል – ከዚህ በላይ የሀገር ሞት የለም፡፡ ሙስና እንኳንስ በዓለማዊ የሥልጣን ቦታዎች በሃይማኖት ተቋማት ሳይቀር የወረርሽኝ ያህል ተስፋፍቶ አነስተኛ ገቢ ካለው ደብር ከፍተኛ ገቢ ወዳለው ደብር ለመዛወር፣ እልቅና ለማግኘት፣ በክህነት አገልግሎት ለመቀጠርና ለአነስተኛ የዝውውር ጥያቄዎች በሺዎች የሚገመት ብር እንደሚከፈል እንሰማለን – ከዚህ በላይ የሞራል ዝቅጠት የለም፡፡ ሙስና በቤተ መንግሥት ይቅርና በገዳማትና በአብያተ ክርስቲያን ሳይቀር የዘመኑ ፋሽን በሆነበት ሁኔታ ድንገት ተነስቶ እገሌንና እገሊትን ማሠር ከጎኑ ሌላ የቦካ ቂም መኖሩን ከማመልከት ባሻገር እንዲያም ሲል በቧልታይ ድንቃይ የልጆች ኮሜዲነት ከማሣቅ በተጓዳኝ ሌላ የሚሰጠው ትርጉምም ሆነ ሀገራዊ ፋይዳ የለውም፡፡ እንትን ላይ ተቀምጦ እንትን ገማኝ አይባልም፡፡ ያለሙስና የሚንቀሳቀስ የመንግሥት ባለሥልጣን አለ ማለት መኖር ያቆመ ባህታዊ ሕዝብንና ሀገርን በቅንነት ለማገልገል ቆሎና ደረቅ ዳቦ እየቀመሰ በመንግሥት ሥራ ላይ ተሰማርቷል ማለት ነው፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በተቋቋመ ማግሥት ቢሮውን በቁሣቁሶች ለማሟላት ገበያ የወጣው የግዢ ሠራተኛ ራሱ በሙስና እንደተያዘ በወቅቱ ሰምተናል፡፡ ሙስና የጊዜያችን የኑሮ ማጣፈጫ ቅመም ነው፡፡ ማንም ያለርሱ አይኖርም፡፡ እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ አሜሪካና አውሮፓም ውስጥ ሙስናን ዝምቡን እሽ የሚለው የለም፤ ተንቀባርሮ ይኖራል፡፡ ታየኝ እኮ ‹የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናቱን በሙስና ወንጀል ጠርጥሮ አሠረ!› ሲባልና ሲነገር – ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ፡፡ እንዲያው ጥቂት አያፍሩም ጎበዝ?! የሙስና እናት ባለችበት ሀገር እንዲህ መደረጉ ሕዝብን መናቅ ይመስለኛል፡፡ 80 ሚሊዮኑን ሕዝብ እንደምን ቢቆጥሩት ይሆን? ወይ ጊዜ!
4. የኑሮ ውድነቱ ሕዝቡን እየጨረሰው ነው፡፡ የዕቃዎች ዋጋ በየቀኑ እየጨመረ ብዙ ሰው በሚለብሰው ሳይሆን ቀምሶት በሚያድረው ወይ በሚውለው መጨነቅ ከያዘ ቆዬን፡፡ በተቃራኒው ወደወያኔው ጉያ የተሸጎጡ በርካታ ዜጎች በተለይ በአሥራዎቹና በሃያዎቹ የሚገኙ ገና በቅጡ ያልባለቁ ወጣቶች ገንዘቡን እንዴት እንደሚያገኙት በማይታወቅ ሁኔታ ሌት ከቀን ሲምነሸነሹ ይታያሉ፡፡ ዊስኪና ድራፍት ቤቶች፣ ሥጋ ቤቶችና ሌሎች ንግድ ቤቶች ገዢ አጥተው አይከስሩም፡፡ የወያኔዎቹ ልጆች ብዙዎቹ ትምህርት ስለማይገባቸው አቋርጠው ሌት ከቀን ጭፈራ ላይ ናቸው፤ ከወያኔዎቹ በርካታዎቹ ትምህርት ዋጋ አለው ብለው ራሳቸው ስለማያምኑ በልጆቻቸው ስም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በባንክ እያስቀመጡላቸው ለአካለ መጠን እስኪደርሱላቸው በዱርይነት ተሠማርተው እንዲኖሩ ፈቃደኞች የሆኑ ይመስላሉ – የ14 እና 15 ዓመት ዕድሜ የወያኔ ኩታራ ልዩ ኢግዝኪዩቲቭ መኪና ይዞ ሃሽሽና ሲጋራ እየማገ በጭፈራ ቤት ሲደንስ እንደሚያድር እሰማለሁ – በዚህ ዙሪያ ራሴ የማውቃቸው ብዙ ጉዳዮችም አሉኝ፡፡ (ውድ ኢየሩሳሌም አርአያ፡- ስለነበረከትና ሰዓረ ልጆች፣ ስለአምባሳደር ጎይቶምና ስለሌሎቹም ዋልጌ ልጆች እየተከታተልክ ብትጽፍልን ልጠቁምህ፡፡)
እርግጥ ነው ብዙዎቹ ወያኔዎች ትዳራቸው የፈረሰና በሞራላዊ ሕይወታቸው ከላይ እስከታች የተበሳበሱ በመሆናቸው ለልጅ አስተዳደግም እንደዚሁ ተገቢውን ቦታ የሚሰጡ አይደሉም፡፡ በዚያም ምክንያት ይመስላል የሕዝብ እርግማን ተጨምሮበት ልጅ እንዳይወጣላቸውና እነሱም ሽንታቸውም ባክነው እየቀሩ የሚገኙት፡፡ ሚስቱን ያልቀየረ ነባር ታጋይ ማግኘት ይከብዳል ይባላል፡፡ አሮጊቶቹን እየጣሉ ሕጻናትን ማግባትና በየቦታው ቅምጥ ማስቀመጥ በነሱ ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ ለልጆቻው ገንዘብን ለማውረስ ባንኮችን በብር ከማጨናነቅ ውጪ ለአብራካቻው ክፋዮች የሚሆን ፍቅር የላቸውም ይባላል፡፡ እነሱም ልጆቻቸውም ያልታደሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ልጆቻቸው የሚይዙት መኪና ሌላ ነው - የሚመነዝሩት ረብጣ ረብጣውን ነው፡፡ ሴት ሲያሳድዱ ደግሞ አባቶቻቸውን ያስንቃሉ፡፡ እንደሸሚዝ ነው የሚለዋውጡ ይባልላቸዋል – ዱሮውንስ ያልዘሩት መች ይበቅላል? የወያኔ ቡችሎችና ተለጣፊዎች የሚያሽቃንጡባቸው ተሸከርካሪዎችም ልዩና ውድ ናቸው – የባሕርይ ምስስላቸውም እንከን አይወጣለትም፡፡ ዋጋቸው በብዙ መቶ ሺዎች ምናልባትም በሚሊዮኖች የኢትዮጵያ ብር የሚገመቱ መኪናዎች ሲርመሰመሱ ለማየት ከአውሮፓና አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ሳያስፈልግ አይቀርም፤ ለአንድ ሺህ ሰው ሦስት መኪናዎች ብቻ በሚሰላባት ሀገር ውስጥ እነዚሁ ጥቂት መኪኖች ባብዛኛው የተያዙት በወያኔ ጭፍራዎችና በመንግሥታዊና ግላዊ ድርጅቶች ነው፡፡ ሀገራችን የለየላት የዕንቆቅልሽ ምድር ሆናለች፡፡ አንዱ የሚቀምሰው አጥቶ በጠኔ ሲያጣጥር ታያለህ – አንዱ ጥጋት ላይ፡፡ ሌላው ሐመርን በመሳሰሉ ዘመናዊ መኪናዎች እየተንፈላሰሰ በሺዎች በሚቆጠር ብርና ዶላር የሌሊት ክበባትን ሲያደምቅ ታያለህ – በሌላው ጥጋት፡፡ በአንድ እጅ ጣቶች የሚቆጠሩ የጥቂት ሺህ ብር ደመወዝተኛ ባለሥልጣናት ትላልቅ ሆቴሎች ውስጥ ገብተው በቁርጥና በዊስኪ ሲዝናኑና ለአንድ ጊዜ የመገባበዣ ክፍያ የሦስትና የአራት ወር ደሞዛቸውን ድምር ሒሳብ ከፍለው ሲወጡ የምታየው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ አግራሞትህ ላይ ሌላ አግራሞትን እንድትደርብበት ያህል – እነዚሁ ባለሥልጣናት በማታው የቴሌቪዥን ዜና ላይ በሃሳብ ያልተስማሙዋቸውን ሌሎች ባለሥልጣናትን በሙስና ማሰራቸውን የምትሰማውና በለበጣ የምትስቀው እዚህችው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ለጉድ የፈጠራት የደም ምድር አትልም? ቃየሎች በአቤሎች ላይ የሰለጠኑባት አስገራሚ ኢትዮጵያ!
የዱሮና ዘንድሮን ልዩነት በቃላት እንኳን ለመግለጽ እየከበደን ነው፡፡ የዐርባ ብር ደሞዝተኛ ዱሮ ቤት መሥራት ይችል ነበር፡፡ የአራት ሺህ ብር ደሞዝተኛ ዛሬ ቤት ተከራይቶ እንኳ መኖር ይከብደዋል፡፡ ዛሬ መቶ ሊትር ቤንዚን በሚቀዳበት ገንዘብ ዱሮ ሁለትና ሦስት አሮጌ መኪና ይገዛበት ነበር፡፡ የዛሬ የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ ዱሮ ወደ 60 ኩንታል ገደማ ይገዛበት ነበር፡፡ ዘንድሮ ለሐኪም ቤት ካርድ ማውጫ ብቻ የምትከፍለው ገንዘብ ዱሮ መላ ቤተሰብህን ሊያሳክም የሚችል ነበር፡፡ ዱሮ በስሙኒ የምትገዛው 12 ዕንቁላሎች የሚመረቁልህ ሙክት ዶሮ ዛሬ ከነዕንቁላቹ (200 ሲደመር 36) 236 ብር ደርሷል – ነገ ደግሞ ከዚህ ሊያጥፍም ይችላል፡፡ ዘንድሮ ቤትህን ለማደስ የምታወጣው አሥር ሺህ ብር ዱሮ አሥር አነስተኛ ቪላዎችን ሊያሠራህ ይችል ነበር፡፡ በሞራልም፣ በሃማኖትም፣ በሥነ ምግባርም… በሁሉም ዘርፍ ብትቃኝ የደረስንበት የኪሣራ መጠን በምንም ዓይነት ምድራዊ መሣሪያ ሊለካ የማይችልና ለማንሰራራትም ከተዓምር በታች በመፍትሔነት የማይታሰብበት አሳሳቢ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በቃኝ፡፡
የርዕሶምን ያን ሕይወት አለምላሚ ዘፈን እባካችሁን ላኩልኝ፡፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment