የመንግሥት ሌቦች አደራ-ቢስነትና ሕዝብ ኃላፊነት
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ስለመንግሥት ሌቦች እየተናገረ ነው፤ ሌቦቹን ግን እሱም አያውቃቸው፤ እነሱም እየሰሙት አይደለም፤ የመንግስት ሌቦች የተባሉት የሚግጡባቸው ዋናዎቹ መስኮች ታክስ፣ መሬትና የንግድ ውድድር መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጾአል፤ ከዚህም በላይ የተባሉትን የሌብነት መስኮች ከለምነት ወደበረሃነት ለመለወጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ኃላፊነት አለበት ያለ መሰለኝ፤ ሥልጣን ሳይኖር ኃላፊነት ከየት ይመጣል? እንግዲህ የፌዴራል ፖሊሱንና ሌላውን አልፎ፣ የደኅንነቱን ሰራዊት አልፎ፣ የጸረ-ሙስና ኮሚሽንን አልፎ፣ ዓቃቤ ሕግን አልፎ ሕዝብ እነዚያን ለምለም መስኮች ማድረቅ እንዴት ይችላል? ሌቦቹ ያሉት በመንግስት ጎራ ብቻ ሳይሆን በህዝብም ጎራ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቆም አድርጎአል፤ እንዲህ ከሆነ ‹‹አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ›› የሚባለው ሁኔታ ሰፍኖአል ማለት ይመስላል፤ ይህ እውነት ከሆነ ሌብነት ሥርዓት ሆኖአል ማለት ነው።
ሌብነትን ሥርዓት የሚያደርገው ምንድን ነው? የባለስልጣን ጉልበተኛነትና የስልጣን ተጠቃሚ ደካማነት፣ የጨቋኝ የተጨቋኝ ግንኙነት የተስፋፋ ሲሆንና በእነዚህ ግንኙነቶች ውስጥ ወይም በእነሱ መሀከል የሚዳኝ ሕግ ሲጠፋ ወይም ሲደበዝዝ ነው፤ የዚህ ሁኔታ አንዱና ዋናው መገለጫው ፍርሃትና የማድበስበስ ባህል ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስረዳው በሙስና ወይም በንቅዘት ጉዳይ የሌብነት ወንጀልን የሚፈጽሙት ጉልበተኛው ባለስልጣንም ደካማው በስልጣን ተጠቃሚውም ናቸው፤ ሁለቱም ሕግን ረግጠው ጥቅማቸውን ብቻ የሚያደልቡ ናቸው፤ በዚህ ሚዛን ሁለቱም ሌቦች እኩል ናቸው፤
በተጨማሪ ደግሞ ጉልበተኛው ባለስልጣን አደራ አለበት ይባላል፤ ነገር ግን አደራውን የተቀበለው ከማንና በምን መንገድ መሆኑ በግልጽ ካልታወቀ ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ የሚለው መመሪያ በሥራ ላይ በዋለበት ሁኔታ ጉልበተኛው ባለሥልጣንና ምስኪኑ የምኞት ባሪያ አሁንም ወንጀላቸው እኩል ይመስለኛል፤ የባለሥልጣኑን ወንጀል ከምስኪኑ የምኞት ባሪያ ወንጀል የሚለየው የባለሥልጣኑ አደራ በላነት ሊባል ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን በአደራ በላነት ሊያስከስሰው የሚችለው ሁኔታ የሚፈጠረው መንግሥተ-ሕዝብ ወይም ዴሞክራሲ በሚባለው ሥርዓት ነው።
በመንግሥተ-ሕዝብ ሥርዓት ሕዝብ ተቆጣጣሪም ዳኛም ሆኖ ለባለሥልጣኖቹ መሾምና መሻር ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ ዳኞችንና ዓቃቤ ሕጎችን ለማሻር ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ እንዲያውም ገዢውን ቡድን ሕዝቡ ሊለውጠው ይችላል፤ በዚህም ምክንያት ባለሥልጣኑ የሕዝብ ባለአደራነት ግዴታ አለበት ለማለት ይቻላል፤ በዚህም ምክንያት ባለሥልጣኑ የሕዝብ አገልጋይ እንጂ የአለቃው አሽከር አለመሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ በአሰራሩ ለህዝብ ግልጽነትና ተጠሪነትን ማሳየት ግዴታው ይሆናል፤ በዚህም ምክንያት ተገልጋዩ ሕዝብ በባለስልጣኖቹ ላይ ያለውን ሥልጣንና መብት አውቆና ተረድቶ በሙሉ ልብና በነጻነት በባለሥልጣኖቹ ላይ የሚያየውን ጉድለት ሳይፈራና ሳይሰጋ በአደባባይ መናገር ይችላል፤ በእንደዚህ ያለ ሥርዓት ውስጥ ሕዝቡ ባለሥልጣኖቹን የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት ለማለት ይቻላል።
ሕዝቡ ለጉልበተኞች ሌቦች በተጋለጠበት ሥርዓት ውስጥ ሕዝቡ ባለሥልጣን ሌቦቹን የማጋለጥ ኃላፊነት አለበት ማለት እንዴት ትክክል ይሆናል? ሕዝቡ ማድረግ የሚችለው ማሳበቅ ብቻ ነው፤ ይህም ቢሆን በያለበት ከሚርመሰመሱት ከመንግሥት አሳባቂዎች ጋር ያጣላል፤ ሌብነትን ለማቆም አስፈላጊ የሆኑት መዋቅሮች ሁሉ አሉ፤ ምንም የጎደለ አይመስለኝም፤ የጎደለው ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ነው፤ ተደጋግሞ የሚሰማው ገጠመኝ አቤቱታ ያቀረቡበት ባለሥልጣን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሥልጣን ጨምሮ አቤቱታ የቀረበበት ወንበር ላይ ጉብ ብሎ ይገኛል የሚል ነው፤ እንግዲህ የተከሰሰው ሰው ዳኛ ሆኖ ሲገኝ ዳኝነት ከየት ሊገኝ ነው! ሌላ ቀርቶ በጠኔ የሚወድቁ ተማሪዎችን ምሳ ለማብላት ለሚጥሩ በጎ አድራጊዎች ግልገል ጉልበተኛ ባለስልጣኖች እንቅፋት እንደሚሆኑ ተደጋግሞ ይሰማል፤ እነሱ ድርሻቸውን ሳያገኙ በጠኔ የሚወድቀው ደሃ ተማሪ እርዳታ አያገኝም ነው? ወይስ ማናቸውም እርዳታ በእኛ በኩል ማለፍ አለበት ነው? ወይስ እኛን አስኮንናችሁ እናንተ አትጸድቁም ነው? በህክምናም በኩል ተመሳሳይ ችግር እንዳለ በሐሜት ደረጃ ይወራል፤ ነገር ግን ስለዚህ ተጠቃሚው ሕዝብ ኃላፊነቱን ተቀብሎ ከሐሜትና ከወሬ ይልቅ እውነቱን አደባባይ ለማውጣት ፈቃደኛ አይደለም፤ ለዚህ አልበቃም፤ የባሰ ይመጣል ብሎ ይፈራል፤ ጉልበተኛውን ባለስልጣን ይፈራል፤ ጉልበተኛውን ባለሥልጣን ለማሳጣት የሞከረ የምኞት ምስኪን ሌላ ትልቅ ወንጀል ተለጥፎበት እከብራለሁ ሲል ይደኸያል፤ ስለዚህ ጎመን በጤና ይልና ከጉልበተኛው ጋር ጮማውን አብሮ ይቆርጣል፤ ብሉ ሌበል ዊስኪውን አብሮ ይጠጣል፤ ሕዝብም ውሃውን ፈልጎ ይጠጣ!
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያሸነፉ ሌቦች ማንን ሊፈሩ ነው!
ዱሮ፣ ዱሮ በደጉ ዘመን በዱሮው ማዘጋጃ ቤት ፍርድ ቤት ነበረ፤ እዚያ የሰማሁትን ደማም ነገር አስታውሳለሁ፤ አንድ ኢጣልያዊ የከባድ መኪና ሹፌር በሁለት ጉዳይ ተከስሶ ቀርቦአል፤ አንደኛ የትራፊክ ሕግ በመጣስ፣ ሁለተኛ በመንግሥት መኪና የንግድ ዕቃ በመጫን ተብሎ ተነገረ፤ ዳኛው መነጽራቸውን አፍንጫቸው ጫፍ ላይ አድርገው እየጻፉ እንዳቀረቀሩ ‹‹ጥፋተኛ ነህ አይደለህም?›› ብለው ሲጠይቁት፣ ‹‹ኢኔ ሹፌር ኖ፤ መኪና የራስ…. (እንትና) ኖ፤›› ሲል ዳኛው የራስ እንትናን ስም ሲሰሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀና አሉና የዓቃቤ ሕጉንም ስም አስታውሳለሁ፤ ‹‹ሞገስ! ብለህ ብለህ ከማን ጋር ልታላትመኝ ነው?›› ሲሉት ዘመናዩ ዓቃቤ ሕግ ‹‹ባለቤቱ ራስ እንትና ናቸው ካለ፣ እሳቸውን ያቅርብ፤›› አለ፤ ደማሙ እውነተኛ ዳኛ ቀበል አድርገው
በዓቃቤ ሕጉ እያሾፉ ‹‹እኮ ራስ እንትና እዚህ እንዲመጡ!›› አሉና ወደጣልያኑ ዞር ብለው ‹‹በል ሂድ ወዳጄ!›› ብለው አሰናበቱት።
ፈጣሪ ሰውን በአምሳሉ ከፈጠረ በኋላ ከዕጸ በለስ በቀር ሁሉንም ቅርጥፍ አርገህ ብላ ቢለው ዕጸ በለስንስ ለማን ትቼ አለና እሷንም ቅርጥፍ አድርጎ በላና ያስከተለውን ውጤት የማያውቅ አለ?
No comments:
Post a Comment