Thursday, June 13, 2013

ይቺ ለአባይ የተፃፈች ደብዳቤ ናት፡፡ አፃፃፏ “ስዲ ወ ግጥሚ” አይነት ናት፡፡

ይድረስ ለአባይ ባለበት… (ከአቤ ቶኪቻው)

June 13, 2013 አቤ ቶኪቻው
ጉዳዩ፤ በጣም አበዛኸው…!
Abe Tokichaw's letter to Abbay (Nile) River.
ይቺ ለአባይ የተፃፈች ደብዳቤ ናት፡፡ አፃፃፏ “ስዲ ወ ግጥሚ” አይነት ናት፡፡ ትንፋሽ ያለው ሰው እንደ ግጥም ቢወርዳት ግጥም ግጥም ትመስላለች፡፡ ትንፋሽ የሌለው ሰው ደግሞ እንዲሁ ቢዘልቃት ስድ ንባብ ትሆናለች፡፡ እስቲ እንደዚህ አዳዲስ ፈጣራዎችን እናስተዋውቅ… ብዬ አካብጄ በአዲስ መስመር እጀምራታለሁ ትድላችሁ…!!
ውድ አባይ፤ ከእናታችን ማህጸን ተገኝተህ ገና በቅጡ ሳትጠና እና ሳትጠናና በልጅነት አፍላ ፍቅር ድንገት አየተሃት ከወደድካት ግብጽ ጋር ከተጋባህባት ዕለት አንስቶ ለጤናህ እንደምን አለህ… ከቶ!
እኛስ እንዳለን አለነው፡፡ አንተን ያኽል ወንድም፤ አንተን ያኽል አጋር፤ ውጪ ሀገር የሚኖር ታላቅ፣ እጅግ ታላቅ፣ ሃብታም የናጠጠ፤ ጥሩ ስርፋ ደህና ቦታ ይዞ የተቆናጠጠ፤ ዘመድ ቢኖረንም ዛሬም አልጠገብንም፡፡ ዛሬም አልወዛንም፡፡ ዛሬም አልወፈርንም፡፡ እንዲሁ እንደቀጠን፣ እንዲሁ እንደራበን፣ አመድ እንደመሰልን አለን አባይ፡፡ እንዲሁ አለን፡፡
ያዩህ ሲነግሩን፤ ከግብፅ ጋር ተኝተህ፤ ት……ልቅ አልጋ አንተው ተዘርግተህ፣ ት……ልቅ ፍራሽ አንተው ተከምረህ፣ ት…ልቅ አንሶላ አንተው ተነጥፈህ፣ ት…ልቅ ብርድ ልብስ አንተው ተደርበህ፣ ት…….ልቅ እንትን አንተው እንትን ሆነህ፤ “አቤት ፍቅራችው ሲያስቀና” እያሉ ብዙ ሰዎች ያወራሉ፡፡
“አምሮበታል፣ ዘንጧል፣ ቢጠሩትም አይሰማ! ከርሷ በቀር አይለማ፣ ከርሷ በቀር… እንዴት የሚያስቀና ፍቅር እንዴት የሚያስቀና ትዳር መስርቷል” ይሉሃል፡፡
ለመሆኑ ከእናት ከአባት ፈቃድ ውጪ፤ የማንአለብኝነት ጋብቻ እንዴት ደስስስስ አሰኘህ እንዴት አሞቀ ጉልቻ…?  ሽማግሌ እንኳን ሳይላክ በቅጡ እንዲሁ እንደዋዛ፤ ጎጆ ስትወጡ እሷስ እንዴት ዝም አለች? ቤተሰቦቿስ ምን አሉ? ገሌ ገብተህ ስትቀር “እሰይ አበጀህ” ነው የሚሉ…?
እንደው የሚገርመኝ እንደው የሚደንቀኝ ይቺ ግብፅ ብሎ ሴት፤ ገና በአፍላነት ያየሃት፣ በህጻንነትህ የወደድካት፣ በልጅነትህ የተኛሃት፣ በአደባባይ እንትን ያልካት፣ እናትህን አስረስታ፣ ቀልብህን ሁሉ አስታ፣ ያሳጣችህ ይሉኝታ፤ ብትሰጣት ብትሰጣት፤ “አረ በቃህ… እስቲ ደግሞ ለእናትህ… ካፈራነው ባትልክ እንኳ ካፈራችው አስቀርላት ዝም ብለህ አትንጠቃት እርሷስ ቢሆን ማን አላት…?” የማትልህ እንዴት ያለችው ሚስት ናት!
አባ…ዬ!
ድሮ አፈሩን አጥበከው ከራስህ ጋር በጥብጠከው ቀይ ቀለም አስመስለህ፤ ለዛች ለሚስትህ ይዘህ ሽው ስትል ብቻ ነበር የምናውቀው፡፡
አሁን ደግሞ በቅርቡ ይዘሃል አሉ አዲስ ውሽማ፤ ከራሷ በቀር ሌላ እግዜርን እንኳ የማትሰማ! እርሷ እንዳለችህ ደግሞ፤ ገንዘባችንን፣ ብራችንን፣ ባላረንጓዴ ቀለሙን፤ የቁርስ ምሳ እራት የልጆቻችን ቀለቡን፤ እፍስፍስ አድርገህ እየወስድህ “ግዴየለም እመልሳለሁ” እያልህ ይዘህ ሽውውውው ትላለህ፡፡
እኛም እንደ ትላንቱ ዛሬም እየዘፈንን፤ እያልን እልል ዝም ብቻ ነው የምንል፡፡ “አባይ ማደሪያ የለው ደሞዝ ይዞ ይዞራል፤ አባወራው ከነልጁ ጾሙን ጥቅልል ብሎ ያድራል፡፡ አባይ ወንዛ ወንዙ ብዙ ነው ደም ወዙ” እያልን እየዘፈን ዝም ብቻ ነው የምንል፡፡
አረ ለመሆኑ፤ ስንት ድረስ ነው የሚበቃህ…? ስንት ድረስ ነው የሚያጠግብህ…? መቼስ ነው የምትመልሰው…? አፈር አንሶህ፣ ውሃው አንሶህ፣ ደሞዝ ደግሞ የምትወስደው… እስቲ ንገረኝ አባይ መቼ ነው እዳህን የምትከፍለው…? ምንስ አድርገህ ምን ሰርተህ ነው የእናትህን እና የእኛን ሀቅ እንትፍ ብለህ፤ ምትመልሰው…? እስቲ ንገረኝ አባይ! አህያ እንኳ በወለደች አረፈች ይላል ያገሬ ሰው፤ እናታችን አንተን ወልዳ  ቢቀርላት እንኳ ማረፉ፤ ምናል እፎይ ባለች በቀረላት ዘረፋ…?
አንተ!
ምንድነው እንዲህ የሚያደርግህ? በቃኝ ማለትን የማታውቀው፤ ትንሽ ይሉኝታ የሌለህ፤ አረ በማን ወትተህ ነው…!? እልፍ ሲሰጡህ ስንዝር፤ አፈር ሲሰጡህ ብር፤ ደሞ ይዘህ ብርርር! የምትለው አረ ከየት ተማርከው…!
አባይ…
በልጅነትህ ግብጽን አግብተህ ከሱዳን ተዳርተህ፤ በስተርጅናህ ደግሞ እንትናን ወሽመህ ሁሉም አምጡ አምጡ ይላሉና፤ አንተም ስጡ ትላለህ? ለእኛ እና ለእናትህ ለኢትዮጵያስ እስቲ ቁርጥ ቀን ንገረኝ መቼ  እንኩ ትለናለህ…?
እስከዛሬ የምትወስደው አፈሩም ሆነ ብሩ፤ “እሱ ካለ ምን ይደረግ” ብለን እንጂ ኖሮን ተርፎን አይደለም ካገሩ፤ ይሄንን አንተም ታውቃለህ፤ ቁባቶችህም ያውቃሉ! ዝም ብለው እንጂ እየወሰዱ ዝም የሚሉ፤ አዎ… እንደሌለን ያውቃሉ፡፡
ግድ የለም “ከሌለው ላይ የሚሰጥ እርሱ የተባረከ ነው” ይላል እና መፃፉ ባትከፍሉንም አንኳ እንዳሻችሁ ብታጠፉ፤ ትዝብት ሆኖ ትርፉ… ግዴለም ውስዱ ግዴየለም ዝረፉ፡፡ ገንዘብ አላፊ ነው አፈርም ጠፊ ነው ተብሎ ባጻፍም ያው እኔ ብያለሁ፡፡
ግና አባይ…
የአሁን ዳር ዳርታችሁ ምንም ደስስስስ አላለኝ፤ እንደው ትከሻዬን ሩሄን ነው የቀፈፈኝ፡፡ ውሽማ እና ሚስትህ እዛ እና እዚህ ሆነው ያለንን ሲወስዱ፤ በእኛው ሲነግዱ በእኛው ሲያረግዙ በእኛው ሲወልዱ ጸጥ ብንላቸው፤ አሁንም አርግዘው ሌላ እንዳማራቸው ሌላ እንዳሰኛቸው ወዲህ እና ወዲያ ሆነው ሲያወጉ ሰማናቸው፡፡
አበዛከው አባይ፤ ያለንን ብንሰጥህ፣ ፀጥ ዝም ብንልህ፣ አክብረን ነው እንጂ፤ ፈርተንህ መሰልንህ…? ነፍሰጡር ሚስትቶችህ፤ ያለ ዕቅድ አርግዘው፣ ነፍሰ ጡሮች ሆነው፣ ነፍስ ነፍስ ሸቷቸው፣ ነፍስ አምጡ ቢላቸው፤ አንተም ይሉኝታ አልባው ብትወስድ የማይበቃህ የቀደመው አንሶህ አሁንም ከጀለህ!
አበዛኸው አባይ
በጣም አበዛኸው…!
ወዳጅህ

1 comment:

  1. What a perfect and meaningful piece is that!!!
    God bless u and our LAND ETHIOPIA!!!

    ReplyDelete