June 12, 2013
ጥላሁን ዛጋ
አባይ
መነሻ ምንጩን ሰሜናዊ የኢትዮጵያን ክፍል በተለይም ጣና ሃይቅንና በዙሪያው ያሉ አፍላጋት አድርጎ ረጅም ጉዞውን
ጣና ሃይቅ ላይ በሚፈጥረው ንብርብሮሽ የአለምን ህዝብ በሙሉ አስደምሞ ይጀምራል፣ እግረ መንገዱን ሌሎች ገባር
ወንዞችን በጉያው ሸክፎ እስከሜዲትራኒያን ባህር ያለውን በማይልስ የሚቆጠረውን የርቀት ጉዞ ይቆርሰዋል፣ በ75᎖912
ስኩዌር ኪሎሜትር የተፋሰስ ስፋትና በ23᎐6 ቢሊየን ሜትርኪዩብ አመታዊ አማካይ የፍሰት መጠን ጋምቤላንና ሌሎች
የኢትዮጵያን ሰሜናዊ ክፍሎች የሚያዳርሰው ባሮ ወንዝ እንዲሁም በ82᎖350 ስኩዌር ኪሎሜትር የተፋሰስ ስፋትና
በ9.6 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ አመታዊ አማካይ የፍሰት መጠን ከላስታ ተራሮች ተነስቶ ወደምዕራብ በመፍሰስ እንደገና
አቅጣጫ ቀይሮ ወደ ሰሜን የሚመለሰው የተከዜ ወንዝ በአባይ ጉያ የሚሸከፉ ዋናዎቹ ገባሮች ናቸው።
በመሆኑም
አባይ ይህን የታላቅነት ግርማውን እንደያዘ ያለከልካይ ለዘመናት ሲፈስ የኖረና የህብረ-ኢትዮጵያዊነት መገለጫ
እንዲሁም የሁሉንም ብሔር-ብሔረሰቦች ስሜት በአንድነት የሚነካ የኢትዮጵያ ወንዝ ነው። እንደየክፍለዘመኑ እንዲሁም
ማህበረሰባዊ የእውቀትና ብስለት ደረጃ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያወያየ፣ ያነጋገረና ያከራከረ ስሜት ቀስቃሽና የሀገር
ወዳድነትም መገለጫ ሆኖ ለዘመናት የዘለቀ ወንዝ ነው፣ በተመሳሳይም በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ መሪዎች
ለፖለቲካቸው ውበት ማድመቂያ እንዲሁም ለኢትዮጵያዊነታቸው መሃላ ማህተም ሆኖላቸው ቆይቶአል።
ለምሳሌ
ያህልም ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ በግዛት ዘመናቸው ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ያላትን ድርሻ የማስከበር መብቷን
መጠቀምን በተመለከተ የራሳቸውን ድርሻ ተጫውተዋል። በወቅቱ ከተሰሩት ስራዎች በጥቂቱ ለመግለጽ እንደራሴ
ከነበሩበት ግዜ ጀምሮ ነበር ጥረታቸውን ያካሄዱት። ኒውዮርክ ከሚገኘው ከ J G white Engineering
Company ጋር በጣና ሃይቅ ላይ በ20 ሚሊየ ዶላር ግድብ ለመስራት ጥናት እና እቅድ ተጠናቆ ነበር። ከዛም
በተጨማሪ 1956 – 1964 ስምንት አመት የፈጀ ባለ 17 መድብል ጥናት በ10 ሚሊየን ከአሜሪካ ሪክላማሽን ቢሮ
ጋር በተደረገው የትብብር ጥናት ከግምጃ ቤት 10 ሚሊየን መድበው ጥናቱ እንዲከናወን አድርገዋል ። የጥናቱም ውጤት
በ17 መድብሎች የቀረበ ሲሆን በአባይ እና ገባር ወንዞች ላይ አራት ግድቦችን የመስራት እቅድን ያካተተ ነበር።
ይህ እቅድ ተጠናቆ ቢሆን ኖሮ በሱዳን እና በግብፅ ላይ የሚደርሰውን የውሃ ሙላት መጥለቅለቅ የሚያስቀር ከመሆኑም
በላይ በግብጽ በመስኖ ከሚለማው ጠቅላላ መሬት 17 በመቶውን ያህል የሚሆን በሃገራችን እንዲለማ የሚያስችል ነበር።
ደርግ
በዲፕሎማሲው መስክ በአባይ ላይ ኢትዮጵያ ያላትን መብት ለማስከበር አሉ የተባሉ ሙሁራንን በማሳተፍ ከፍተኛ ጥረት
አድርጓል ከዛም በዘለለ (multi-purpose) ሁለገብ የሆነውን የጣና በለስን ግድብ በመስራት ለመጀመርያ ግዜ
የአባይ ገባር ወንዝን ለሃገሪቱ የመስኖ አገልግሎት እንዲውል ከፍተኛውን ስራ ሰርቷል። ሌላው ከጣልያን መንግስት
ቃል በተገባ 300 ሚሊየን ዶላር እርዳታ የደርግ መንግስት የጣና ሃይቅን ወደ በለስ ወንዝ በመቀልበስ አምስት
ግድቦችን ለመገደብ እቅድ አጠናቆ ስራ ጀምሮ ነበር ሆኖም በ1991 ደርግ ሲወድቅ እና ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ
ባልታወቀ ምክንያት እንዲቆም ተደርጓል ሆኖም እንደገና ከ10 ዓመት በሁዋላ ሽፈራው ጃርሶ የሃይድሮ ኤሌክትሪክን
ጨምሮ በአዲስ እንደሚሰራ አሳውቆ እንደነበር ብናውቅም የት እንደደረሰ ግን የሚታወቅ ጉዳይ የለም። ለመሆኑ የጣና
በለስ ፕሮጀክት ለምን ተቋረጠ ? ይህ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊጠይቀው የሚገባ መሰረታዊ ጥያቄ ነው።
ይህ
በእንዲህ እንዳለ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ያለው ህወሓት መራሹ ገዢ ቡድን በሚያዚያ ወር 2003 ዓ/ም እንደ
ኢትዮጵያ አቆጣጠር የአባይን ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ ሲያደርግ ታሳቢ ያደረገው ምንድን ነው? ከላይ ለመጥቀስ
እንደተሞከረው ለፖለቲካው ውበት ማድመቂያ እንዲሁም በግዛት ዘመኑ ለፈፀማቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መደበቂያ
ጭንብል እንጂ ሃገራዊ ወይም ምጣኔ-ሃብታዊ ፋይዳው ተገምግሞ እንዳልሆነ ጥቂት ማሳያዎችን እናንሳ፣ እንደሚታወቀው
ገዢው ቡድን በተለያዩ ጊዜያት ፖለቲካዊ ውጥረቶች ሲከሰቱ የህዝብን ቀልብ ማስቀየሻ የሚሆኑ ኩነቶችን በመፍጠር
የትኩረት አቅጣጫን ለማስቀየር ሲታትር ያለፉት ሁለት አስርት አመታትን መቃኘት የሩቅ ትዝታ አይሆንም፣ የግንቦት 97
ምርጫን በግድያና በማጭበርበር በድል አሸነፍኩ ካለ በሁዋላ በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረውን የለውጥ መንፈስ
/እንቅስቃሴ/ በሚሊኒየም አከባበር ፌሽታ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2003 መጀመሪያ ጀምሮ የተቀጣጠለው
የአረቡ ዓለም እንቅስቃሴ ማዕበል ወደዚህች ነፃነት ናፍቆቷ ወደሆነችው ሀገር እንዳይዛመት ደግሞ “የህዳሴው ግድብ”
በማለት የተጠቀማቸው የፖለቲካ ግለት ማብረጃዎች እንደሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው። ይህም ሆኖ ግድቡ ሀገራዊና
ምጣኔ-ሃብታዊ ፋይዳ /ጠቀሜታ/ ቢኖረው መገደቡን ባልጠላን ነበር።
ብዙሃኑ ሕብረተሰብ በተለይም ዲያስፖራው
ግድቡ ላይ ተቃርኖ አለው ለምን? ይህን ፕሮጀክት መቃወም ልማትን መቃወም ነው? እነዚህንና ተያያዥ ጉዳዮችን
ከመዳሰሳችን በፊት የዚህን ፕሮጀክት አዋጭነት፣ ቴክኒካል ይዘት እንዲሁም ሌሎች ተግዳሮቶችን በጥቂቱ ለመዳሰስ
እንሞክር።
1/የፕሮጀክቱአዋጭነት/profitability/
አንድ
ፕሮጀክት ሲታሰብ አዋጭነቱ ላይ ጥናት ሳይደረግ አይጀመርም፣ የግድቡ ፕሮጀክት አዋጭነቱ ላይ ጥልቅ ጥናት
አልተካሄደም፣ ከዚህ አንፃር ብዙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በግድቡ ወጪ ዙሪያ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል የሚል
ጭንቀት አላቸው፣ ለምሳሌ ያህልም 5ቢሊየን ዶላር ያህል ገንዘብ ለአንድ ፕሮጀክት ብቻ ማፍሰስ ሃገራዊ ብክነት
እንዲሁም ከፍተኛ ክስረት ያስከትላል ምክንያቱም ግድቡ በቅርቡ ላሉ የሀገሪቱ ክልሎች ሌሎች አገልግሎቶችን ሳይሰጥ
ለሱዳን ለኬንያና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የኤሌክትሪክ ኃይልን በመሸጥ ብቻ የተወሰነ በመሆኑና እንደመስኖ፣
የመጠጥ ውሃ፣ የአሳ እርባታና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ያላካተተ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ከግድቡ ግንባታ በሁዋላ ለደለል
ማስጠረጊያ የሚወጣው ወጪ ሲታሰብ በጥቂት አመታት ውስጥ ለግድቡ የወጣውን ያህል ወጪ እንደሚወጣ ጥናቶች ያሳያሉ።
2/ቴክኒካል ጥናት/technicalassessment/
እንደሚታወቀው
እንደአባይ ያሉ ታላላቅ ወንዞች ከከፍተኛ ቦታዎች ተነስተው ቁልቁል ሲወረወሩ ይዘውት የሚሄዱት ደለል አፈር አመታዊ
ልኬቱ በብዙ ሺህ ቶን የሚቆጠር ሲሆን አባይም ከፍተኛ የሆነ አፈር የመሸርሸር ባህሪ ያለው ወንዝ ነው። ይህ
በእንዲህ እንዳለ አሁን የሚያርፍበት ቦታም ሸለቆአማ በመሆኑ ከፍተኛ ግፊት ስለሚኖር ደለል ሊሞላው ይችላል። ይህ
ደለል የመሙላቱ ችግር ደግሞ ግድቡን ሊገፋው ይችላል ወይም መጥረግ እንኳን ቢያስፈልግ ግድቡ ከተሰራበት በላይ ወጭ
ይጠይቃል ይህ ደግሞ ለገዳዲን የሚያክል ትንሽ ግድብ እንኳ መጥረግ ባለመቻላችን አዲስ አበባ በውሃ እጥረት
በተደጋጋሚ ትጠቃለች ታድያ ይህ ግድብ ደግሞ ከሁለት ግዜ የባህር ዳርን ውሃ ያጥፋል ታድያ በምን ወጭ ነው
ሚጠረገው? በየስንት ግዜውስ ይጠረጋል ? የተጠረገው የት ይደፋል ? ምን አልባትም ጥራጊውን ለመድፋት 100
ኪሎሜትር መሄድ ሊያስፈልግ ቢችል እንዴት ነው ሚቻለው ? ከወጭ አንጻር ግድቡ ከተሰራበት በላይ ለመጥረግ ያስወጣል።
3/ከውጪው አለም ጋር ስለሚደረጉ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች
እንደዚህ
አይነት ታላላቅ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች ለምሳሌ ግድቦች፣ታላላቅ ድልድዮች፣ ፋብሪካዎችና፣ ሌሎችም ሃገራዊ ግንባታዎች
ሲካሄዱ የሀገሪቱ እንዲሁም ከውጭ ያሉ ታላላቅ ምሁራን ጥልቅ ጥናት ማድረግ አለባቸው። ዲፕሎማሲያዊ ክፍተቶች መሞላት
አለባቸው፣ ፖለቲከኞች፣ ተቃዋሚዎች፣ የሀገሪቱ ህዝቦች፣ የሀገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ፣ የተፋሰሱ ሃገራት፣
ጎረቤት ሃገራት እነዚህና ሌሎች ያልጠቀስናቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ ሊያውቁት በጥልቀት ሊመክሩበት ሊከራከሩም
በተገባ ነበር፣ ነገር ግን እነዚህ በሙሉ ሳይፈፀሙ ይልቁንም የሀገሪቱ ፓርላማ እንኩዋን ሲታወጅ እንደተራው ሕዝብ
እንጂ ሲታቀድእንኳን ባልሰማበት ሁኔታ ስለ ግድቡ ማውራት አይታሰብም።
4/የፕሮጀክቱ ግልጽነት /Transparency/
ከላይ
ለመግለፅ እንደተሞከረው የፕሮጀክቱ አላማ ከእለታዊ የፖለቲካ ትርፍ ጀርባ ታላቅ ኢኮኖሚያዊ ሴራ ያለበት መሆኑን
የሚያውቁት ሕወሃቶችና ተመሳጣሪዎቻቸው ብቻ ናቸው፣ ይኸውም ከታች ግራፉ ላይ እንደምትመለከቱት የአባይ ግድብ
የሚያስፈልገው ብር አለ፣ የዋጋ ንረትን ሳያጠቃልል ወደ 80 ቢሊየን ነው ከዚህ ውስጥ አጠቃላይ ባለ በሌለ ሃይል
ቃል የተገባው ገንዘብ ወደ 9 ቢሊየን ብር ነው። ከዚህ ውስጥ በእጅ ላይ የሚገኝ ብር ወደ 5 ቢሊየን ነው። ታድያ
ይህን ያህል መጠን ያለው ብር ብቻ በተገኘበት ሂደት ልማታዊው መንግስታችን 20% የግድቡ ስራ ተጠናቋል ይለናል
እንግዲህ በ5% ገንዘብ 20% መስራት የመቻሉ ጉዳይ እንዴት ይታያል ። ከዛሬ 2 ወር በፊት 14 በመቶ ተሰርቷል
ተብለን ነበር አሁን ደግሞ 6% በሁለት ወር ተሰርቷል ተባለ ይህ ፍጥነት ከየት መጣ ? ወይንስ ኢትዮጵያውያን ቁጥር
አይችሉም አይጠይቁም ተብሎ ነው ? ለምንድን ነው ይህ ሁሉ የሃሰት ዘመቻ ? ይህ አይነት ተራ የማደናገርያ እና
የማታለያ ዘመቻዎች ባሉበት ሂደት ተአማኒነት ያለው ስራ መስራት ይቻላል ማለት ዘበት ነው ።
ሌላው የግድቡ
ስራ የሚሰራው ድርጅት የአባይ ግንባታ ለሳሊኒ ኮንስትራክሽን ያለምንም የዓለም አቀፍ የጫረታ ደንብን ሳይከተል
በቀጥታ ስራው ተሰጥቷል። በመንግስት በኩል በዚህ ጉዳይ ላይ ሲጠየቁ የተለመደ ማታለያ መልስ አላቸው ይኸውም
የአባይን ጫረታ አደባባይ ካወጣን ግብጽ አደጋ ትፈጥራለች የሚሉት ያልተጨበጠ ወሬ ነው። ለዚህ ምክንያታቸው ሃሰት
ለመሆኑ ማረጋገጫ ሳሊን የተባለው የጣልያኑ ድርጅት የግቤ ቁጥር ሁለት እና ሶስትን ግንባታ ያለምንም ጫረታ ነው
የወሰደው ታድያ ግብፅ ግቤ ላይም ችግር ትፈጥራለች ማለት ነው? ታድያ ግቤ ላይ ለምን ጫረታ ሳይወጣ ስራው ተሰጠው ?
የሚገርመው እኮ ይህ ሳሊኒ በግቤ የተቋራጭ ስራ ላይ የሰራው ተንዶበት ከፍተኛ ወጪ ያስወጣን እና እጅግ ብቃት
የጎደለው ድርጅት መሆኑ እየታወቀ ለምን አባይን የሚያክል ትልቅ ስራ ተሰጠው ? እንግዲህ ብዙዎች እንደሚሉት ጫረታ
ሳይወጣ በሚደረግ ሂደት ዙርያ ከጀርባ ድርድሮች ይኖራሉ ግለሰቦችን ወይም ድርጅቶችን የሚጠቅሙ ስራዎች ቀደም ተብለው
ይሰራሉ ለዛ ሲባል ግልፅነት ሳይኖረው በድብቅ ይሰራል። ለምን ተደበቀ ስራው ግልፅ አልሆነም ሲባሉ ደግሞ
የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር መሸፋፈን ይሞከራል። ለምሳሌ ዋናውን ስራ የወሰደው ድርጅት እሱ ደግሞ
sub-contruct ወይም የእቃ አቅርቦት የመሳሰሉ ስራዎችን ለሚፈለገው አካል ይሰጣል። ለአብነት ያህል በአባይ
ግድብ ላይ ስሚንቶ በማቅረብ ላይ ያለው የሞሶቦ ድርጅት ነው ፣ ብረታ ብረት እና ሌሎች ስራዎችን በማቅረብ የኤፈርት
ድርጅቶች ተሳታፊ ናቸው ሌሎችንም የተቋራጭ ስራዎችን የወሰዱት እነዚህ ከአንድ አካባቢ የመጡ ግለሰቦች እና
ድርጅቶች ናቸው። በዚህ ደግሞ ኪሳቸውን ያደልባሉ። ስለሆነም ገንዘቡ እስኪያልቅ ድረስ እነ ሞሶቦ እና እነ
ኤፈርትን የመሳሰሉ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ህዝብ የተገኘውን ገንዘብ ያሟጣሉ ማለት ነው። ይህ ባለበት ሁኔታ እና
በዚህ የመንግስት ባህርይ ለምን ህዝብ ከዚህ ስርአት ጋር ይተባበራል? ለምንስ ይህን ስርአት ያምነዋል?
5/የፕሮጀክቱ ጠቃሚነት ለማን?
በእርግጥ
ግድቡ በመገደቡ ለጥቂት ጊዜያት ግፋ ቢል ለአንድ ዓመት የውሃ እጥረት የግርጌ ተፋሰስ ሃገራት በተለይም ግብፅ
ሊያጋጥማት ይችላል፣ ከዚያ በሁዋላ ግን ከኢትዮጵያ በተሻለ 80 ወይም 85 በመቶ ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑ ያውቁታል፣
ምክንያቱም ከዚያ በሁዋላ ላሉት ምናልባትም ብዙ መቶ አመታት ደለል ያልተሸከመ ንፁህ ውሃ ያገኛሉ፣ ስለዚህም ግድቡ
ለኢትዮጵያ/single purpose/ለሌሎቹ ደግሞ /multiple purpose/ፕሮጀክት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።
ስለዚህ
ለዚህ ፕሮጀክት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ድጋፍ ያለማድረግ እንዲሁም ይህን ፕሮጀክት መቃወም ሃገርን ከክስረትና
ከጉዳት ይልቁንም ከከፋ የረዥም ጊዜ ድህነት እንዲሁም የእዳ ሰቀቀን ማውጣት እንደሆነ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል
ቢረዳውም ሌሎችም ወገኖች ከዚህ ሃገርንና ወገንን ከሚጎዳ ተግባር እንዲታቀቡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
No comments:
Post a Comment