Monday, October 30, 2017

“ህዝባችን መንግሥት ያሉበትን አሳሳቢ ጉዳዮች በግልጽ እንዲረዳ ተገቢው ሥራ የተሰራ አይመስለኝም፣ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በአሁኑ ጊዜ በአምቦ እየተካሄደ የሚገኘውን አመጽ ለማርገብ የፀጥታ ኃይሎች እየወሰዱት የሚገኘውን እርምጃ በመኮነን ላይ መሆኑ ነው፣ ሆኖም መንግሥት ይህን እርምጃ ለመውሰድ የተገደደው በአምቦ ከተማ ለረጅም ጊዜ ለፀጥታ ሥጋት የሆኑ ኃይሎችን ለመመከት በማሰብ ነው።


“ህዝባችን መንግሥት ያሉበትን አሳሳቢ ጉዳዮች በግልጽ እንዲረዳ ተገቢው ሥራ የተሰራ አይመስለኝም፣ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በአሁኑ ጊዜ በአምቦ እየተካሄደ የሚገኘውን አመጽ ለማርገብ የፀጥታ ኃይሎች እየወሰዱት የሚገኘውን እርምጃ በመኮነን ላይ መሆኑ ነው፣ ሆኖም መንግሥት ይህን እርምጃ ለመውሰድ የተገደደው በአምቦ ከተማ ለረጅም ጊዜ ለፀጥታ ሥጋት የሆኑ ኃይሎችን ለመመከት በማሰብ ነው። በመሆኑም በአምቦና አካባቢው የሚገኙ የልማት እንቅፋቶችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችንን በቦታው በማሰማራት ተግባራዊ የሆነ  እርምጃ  በመውሰድ ላይ ይገኛል፣  ድል ለጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን!”                       ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል
ሰሞኑን በተለያዩ ያገራችን ክፍላት ሲካሄድ የነበረውንና አሁንም በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ዓመጽ ተኝተንም ሆነ ተነስተን የሚያሳስበን ጉዳይ በመሆኑ ዓይናችንንና ጆሮአችንን በተገኘው የሚድያ ቀዳዳ ላይ ቀስረንና አነጣጥረን፣ ካሁን አሁን የሆነ ቸር ወሬ እንሰማ ይሆን በሚል ተስፋ ቀናትን መግፋት የተለመደ ነገር ሆኖአል። በደምቢዶሎ ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጎ ይህን ያህል ሰው ሞተ ይሄን ያህል ሰው ቆሰለ ወይም ታሰረ፣ በሻሸመኔ ይህን ያህል ሰላማዊ ሰልፈኞች ተገደሉ፣ ታሰሩ ቆሰሉ፣ በጎንደር ፖሊሶች ይህን ያህል ሰው አቆሰሉ፣ ታሰሩ ወዘተ በሚሉ የመርዶ መዓቶች በማህበረሰብ ሚዲያ ይነገሩንና ቁጭ ብለን አልቅሰን ሳይወጣልን በበደሌ ደግሞ በተፈጠረው ሁከት ይህን ያህል ሰው ሞተ ይህን ያህል ሰው ቆሰለ የሚል ሌላ ተጨማሪ መርዶ ይነገረንና እናርፋለን። ገዳዩም መግደል የማይሰለቸው፣ ሟቹም ሞቶ የማያልቅበት የጀግኖች መናሀርያ እንደ ኢትዮጵያችን ያለች ሌላ አገር ትኖር ይሆን ብዬ ራሴን ደጋግሜ እጠይቃለሁ።
ሁለት ነገሮች ሁሌም መልስ ያላገኘሁላቸው ጉዳዮች አሉ፣ የመጀመርያው፣ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በተለይም ዋና መቀማጫቸውን በመዲናችን ያደረጉት የተመድና የአፍሪካ አንድነት ባለሥልጣናት፣ ይህ ሁሉ ሰላማዊ ዜጋ መብቱን በመጠየቁ ምክንያት ብቻ እንደ እንስሳ በራሱ መንግሥት በየአደባባዩ ሲረሸን እያዩ ለምን ድምጻቸውን ከማሰማት ተቆጠቡ የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ፣ የዜጎቹን መብት ለመጠበቅ የመጀመርያ ግዴታ ያለበት የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህ ሰላማዊ ዜጎች በየቦታው ሲገደሉ እንዴት ገዳዮቹን “አድኖ“ ይዞ ለፍርድ ማቅረብ አቃተው የሚለው ነው። ምናልባት ግድያው የተፈጸመው የጸጥታ ኃይሎች ራሳቸውን ለመከላከል በሚደረገው ግብግብ ሳቢያ ሊሆን ይችላል፣ ወይም ደግሞ ሟቾቹ በርግጥም ያገሪቷን አንድነትና የህዝቦቿን ነጻነት የሚፈታተኑ ጸረ ህዝብ አጥፍቶ ጠፊ ሊሆኑ ይችላሉ። ሌላም ሌላም። ያም ሆኖ ግን የሰውን ልጅ ነፍስ ማጥፋት በማንኛውም ምድራዊ ህግ የተከለከለና ይህ መብት በዓለም ዓቀፍ ውሎችም መሰረት ከመብቶች ሁሉ ልቆ በመጀመርያ ተርታ የተመደበ በመሆኑ የዚህን መብት ጣሽ ሊፈርድበትም ነጻም ሊያወጣው የሚችለው ያገሪቷ ፍርድ ቤት ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ህገ መንግሥትም ሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ህጋችን ይህንኑ ያረጋግጣል። በሌላ አነጋገር፣ የሰው ልጅ ነፍስ፣ የህግ እንጂ የፖሊቲካ ጉዳይ ባለመሆኑ ፖሊቲከኞች፣ ፍርድ ቤቱ ከወነጅላቸው ወይም ለምሥክርነት እንዲቀርቡ ካላዘዛቸው በስተቀር ከቶውኑ በዚህ ጉዳይ ጣታቸውን መክተት የለባቸውም።
ባገራችን ግን የምንገነዘበው ተቃራኒውን ነው፣ ወደ ሶስት መቶ የሚጠጉ ዜጎች ቅንጅትን ደግፋችኋል ተብለው በመዲናችን በጠራራ ፀሃይ በአግዓዚ ጦር ሲገደሉ፣ ወይም ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ የኦሮሞ ተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ በተለያዩ ቦታዎች በዚሁ የአግዓዚ አሸባሪ ጦር ሲገደሉ አንድም የጦሩ አባል በግድያ ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት አልቀረበም፥ እንድያውም ይባስ ብሎ፣ ”ጦሩ የወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝና አግባብ ያለው ነው“ ብሎ ያገሪቱ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ዘገባቸውን ለፓርላማው አቀረቡና አረፉ። በግሌ እንደ ሰው ልጅ መብት ተሟጋች፣ ዓይኔንና ጆሮዬን ነው ማመን አቃተኝ፥ ሰው እንዴት ሰው ገድሎ ፍርድ ቤት አይቀርብም? ደግሞ ፓርላማውስ የወንጀል ጉዳይ ለማጣራትና ገዳዮችን “የወሰዳችሁት እርምጃ ትክክል ነው” ብሎ ለመወሰን ቀርቶ ጉዳዩን እንኳ ለመመልከት ምን መብት አለው በማለት ጥያቄዎቼን ማዥጎድጎድ ጀመርኩ። ለካ ለጥያቄዬ  መልስ ሰጪ አካል፣ ማለትም የዜጎችን ብሶት የሚያዳምጥ መንግሥት አለመኖሩን ዘንግቼ ኖሮአል። የሚገርመው ደግሞ አንድ ሺህ ሰላማዊ የኦሮሞ ተማሪዎችን ከገደሉት የአግዓዚ ጦር አባል አንድም ግለሰብ በግድያ ወንጀል ሳይከሰስ፣ አስራ ሶስት ፖሊሶችን ገድላችኋል ተብለው ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ የኦሮሞ ወጣቶች በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው ዛሬም እሥር ቤት ይገኛሉ።
ጋብ ብሎ የነበረው ሁከት ሰሞኑን ደግሞ በተጋጋለ መንፈስ በአምቦ ከተማ መገንፈል ጀመረ፣ የመብቶች ጥሰትና የምግብ አቅርቦት እጥረት ተዳምሮ በጣም በመንገሽገሹ፣ ህዝቡ እንደተለመደው በሰልፍ ወጥቶ መብቱን መጠየቅ ጀመረ፣ እዚያው አጠገባቸው ፊንጫአ የሚመረተውን አንድ ኪሎ ስኳር በስድሳ ብር መሸመት (ያውም ከተገኘ) የተሳነው ሕዝብ፣ ባለተሳቢ የጭነት መኪናዎች ስኳር ጭነው ወደ ሰሜን ሲያመሩ እያየ የተበሳጨው ህዝብ ጥያቄውን በሰላም ለማቅረብ ወደ ጎዳና ወጣ፥ ያልተረዱት ነገር ቢኖር የነሱ የሆነና የሚሰማቸው መንግሥት አለመኖሩን ብቻ ሳይሆን መብታቸውን መጠየቅ ራሱ በመከላከያ ሠራዊት የሚያስገድል ትልቅ ወንጀል መሆኑን ነው። የሆነውም በትክክል ያ ነበር። የክልሉ የፖሊስ ሠራዊት የህዝቡን ብሶት ከቅርብ ሆኖ ይከታተል ስለነበር በሰላማዊ ሰልፈኞቹ ላይ እርምጃ  አልወስድም ብሎ ከሰላማዊው ህዝብ ጋር ሲወግን፣ መከላከያ ሠራዊቱ (አግዓዚ ጦር አባላት) በብረት ለበስ መኪናዎች ታጅበውቦ ከተፍ ይሉና፣ ያገሪቷን ህልውና ይተፈታተኑ ከነበሩት አደገኛ ህጻናትን መካከል አስራ አምስቱን ያለአንዳች ርህራሄ በጥይት ግንባር ግንባራቸውን ብለው በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን አሰፈኑ። አገራችን ኢትዮጵያንም ከአደጋ እንዳዳኗትና የተፈታተኗትን ጠላቶቿንም በማያዳግም ሁኔታ እንደደመሰሱ ለአዛዣቸው በሬድዮ መልዕክት አስተላለፉ፥ አዛዣቸው ዶ/ር ዓምደጽዮንም በመከላከያ ሠራዊታችን ድል እየተኩራራ በሬድዮና በቲቪ ለሚወዳቸውና ለሚወዱት ህዝባቸው ከላይበመግቢያው ላይ የጠቀስኩትን የደስታ መግለጫ አስተላለፉ። የአገሪቷ ጠላቶች ተደመሰሱ፣ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊትም በደስታ ፈነደቀ። በነጋታው ቶሮንቶ የሚገኘው ሂዩማን ራይትስ ሊግ ኦፍ ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ የተባለው የሰው ልጆች መብት ተሟጋች ድርጅት “ያገሪቷን ጸጥታ ለማደፍረስ ሲሞ ክሩ” የተገደሉትን ኅጻናት ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ለዓለም ህብረተሰብ አሳወቀ። ራቡማ ሲኑቴ – ተማሪ, 2) ጫልቺሳ ጋሩማ – ተማሪ 3) አሸብር ዱጋሳ – ተማሪ, 4) ፍራዖል ደጀኔ – ተማሪ, 5) ሚጡቶልቻ (ተማሪ) ኩመላ አሸናፊ (ተማሪ) ድሪባ ጉተታ (ተማሪ) ቶለሳ ጉደታ (ተማሪ) አሸናፊ (ተማሪ) ቀነኒ ጉደታ (ተማሪ) ሊበን ጃዌ (ተማሪ)
እውነትም ላገሪቷ ጸጥታ የሚያሰጉና የልማት እንቅፋት ኃይሎች! የዛሬ ዘመን የፌስ ቡክ ትውልድ ልጆች ቶሎ ይበስላሉ ይባላልና እነዚህ ኅጻናት እንደተባለውም የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና የህዝቦቿን ጸጥታ ለማደፍረስ ብሎም እድገቷን ለመግታት ለዚህ እኩይ ተግባር ተሰለፈው ይሆን ብዬ ራሴን ለመጠየቅ ሞከርኩ። ድሮ ድሮ ጥንት ተማሪ በነበርንበት ዘመን “ንጉሳዊውን ሥርዓት ለመገርሰስ” እናደርግ በነበረው “ትግል” ኪሳችንን በድንጋይ ሞልተን በሰልፍ ስንወጣ፣ ፖሊሶቹ “እጅ ከፍንጅ” ሊይዙን ሲሞክሩና እኛም ላለመያዝ ስንሮጥ፣ በመካከላችን አንዳች ዓይነት መግባባት የነበረ ይመስለኛል፥ ደርሰውብን እንኳ ከያዙን እንደሁ ለይስሙላ ቂጣችንን በዱላ መታ መታ አድርገው “አንተ አትጠፋም ከዚህ፣ አርፈህ አትማርም፣ ለመሆኑ ወላጆችህ የት እንዳለህ ያውቃሉ?” ብለው ከጃቸው እንድናመልጥ ያመቻቹልናል እንጂ ህጻን ተማሪን የሚገድል ፖሊስ አይተንም ሰምተንም አናውቅም። እኛም ግፋ ቢል ”ረባሽ“ እንባል እንደሆን እንጂ “ላገሪቷ ጸጥታ አስጊ ናቸው” ተብለን ስንፈረጅ ትዝ አይለኝም። ታዲያ ዛሬ ምነው ነገሮች ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኑና ህጻናትም ያለዕድሜያቸው በስለው ያገሪቷን ጸጥታና የግዛት አንድነት መፈታተናቸው፣ የጸጥታ አስከባሪ ኃይሉም ከሰው ያልተፈጠረ ይመስል ህጻናትን በጥይት የሚቆላው? የህጻናት ዕድገት ከተፈጥሮ ህግ ውጭ ሊሆን ስለማይችል፣ ያልተለመደ ሊባል የሚችለው የአግዓዚዎች የአውሬነት ባህርይ ነው ብዬ ብደመድም ከዕውነት የራቅሁ አይመስለኝም።
ሁለት ነገሮች ግን በጣም ከነከኑኝ፥ የመጀመርያው፣ ያገር መከላከያ ሠራዊት ብቸኛ የሥራ ድርሻ ያገሪቷን ዳር ድንበር ከውጭ ወራሪ ኃይል ለመጠበቅ ነውይላል ህገ መንግሥታችን፣ ታድያ እነዚህ ከደብተርና ከእስክሪፕቶ ሌላ አንዳች ያገሪቷን የግዛት አንድነትንም ሆነ የህዝቦቿን ጸጥታ የሚፈታተን የጦር መሳርያ ያልያዙና በሰላም ተሰልፈው የመብታቸውን መከበር ይጠይቁ የነበሩ ጨቅላ ኅጻናት እንዴት ተደርጎ ነው በመከላከያ ሠራዊቱ እንዲገደሉ የተደረገው? ሁለተኛው ደግሞ፣ ዶ/ር ደብረጽዮንስ ራሱ ያገሪቷን መከላከያ ሠራዊት ለማዘዝ ሥልጣን አለው ወይ? የሚለው ነው። ለጊዜው ለሁለቱም መልስ የማገኝ አይመስለኝም፥ “ይዘገያል እንጂ እንበሳለን” ብላለች ጥንዚዛዋ። አዎ ይዘገያል እንጂ ሰውን የገደለ ወይም ያስገደለ ሰው በህይወት እስካለ ድረስ አንድ ቀን ለፍርድ መቅረቡ አይቀርምና እግዜር ዕድሜና ጤና ከሰጠን እናይ ይሆናል ብዬ ራሴን አጽናናሁ።
ሌላው ሁልጊዜ የሚገርመኝ ክስተት ደግሞ የህዝባችን የጀግንነት ባህርይ ነው፥ እንደው ሳስበው አንድም ፈሪ የሌለባት የጀግኖች ብቻ አገር ትመስለኛለች፣ ዓባይን የደፈረ ጀግና፣ ጀግናውና ቆራጡ መሪ፣ የአምቦ አመጸኛ ህጻናትን ደምስሶ የኢትዮጵያን ህልውና ያስከበረው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት! ጀግና ህዝብ! የጀግና ዘር፣ ጀግና ከጀግና የተወለደ! ጀግና ጀግና ጀግና ሁለንተናችን ጀግና! ተመራማሪ ቢኖር በጀግኖች ብዛት ከዓለም አንደኛ እንደምንሆን ጥርጣሬ  የለኝም። ያልገባኝ ነገር ግን፣ እኔ እስከማውቀው ድረስ በተለይ በኦሮሞ ባህል ጀግና ማለት ሃያላን የሆኑትን የዱር አውሬዎች እንደ አንበሳ ዝሆን ወይም ነብር የመሳሰሉትን የገደለ፣ ወይም ደግሞ ህዝቡን ከጠላት ወረራ ያዳነ ማለት ነው፥ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ባህልም ከዚህ የተለይ ትርጉም ያለው አይመስለኝም። ህገ መንግሥታችንም ሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ህጋችንም ይህንኑ ባህላችንን የሚያንፀባርቅ ነው፣ ታድያ እንዴት ሆኖ ነው ኢትዮጵያውያንን ከውጭ ወራሪ ኃይል እንዲከላከል የተቋቋመው መከላከያ ሠራዊት የራሱን ኢትዮጵያውያን ወገኖችን ያውም ግብር እየከፈለ የሚያኖረውን አርሶ አደር ልጆች የሚገድለው? ወይ መከላከያ ሠራዊቱ (አግዓዚ ጦር የሚባለው ጉድ) እነዚህን ልጆች እንደ ባዕዳን ቆጥሮአቸዋል ወይም ደግሞ መከላከያ ሰራዊቱ ራሱ የባዕድ አካል ነው ማለት ነው። ከሁለት አንዱ ትክክል ይሆናል እንጂ ሰራዊታችን እኛኑ መልሶ ወግቶ እንደ ድል አድራጊ ከመንግሥት የደስታ መግለጫ መልዕክት ሊተላለፍለት አይችልም። አሁንማ ሁኔታው ሁሉ ግራ የሚያጋባ ሆነና እንኳን መከላከያ ሰራዊቱ የወያኔው መንግሥት ራሱ ኢትዮጵያዊ መሆኑን እየተጠራጠርኩ መጣሁ።
ለዶ/ር ደብረጽዮን አንድ መልዕክት አለኝ፣ ኢትዮጵያዊ ነዎት ብዬ ስለገመትኩ ምናልባት ሌሎች ባዕዳን አካላት አሳስተዎት እንደሆነ ላስታውስዎት ብዬ ነው፥ በባህላችንም ሰላማዊ ሰው በተለይም ልጅ አይገደልም። በድንገት እንኳ በመኪና ገጭተው ህጻን ልጅን ሲገድሉ ይቀውሳሉ። እንግዲህ እስዎም ልጅ ይኖርዎታል ብዬ ስለማስብ እስቲ ላንዲት ደቂቃ ቆም ብለው የገዛ ልጅዎን በሆነ ምክንያት ሌላ ሰው ስገድልብዎት ያስቡና የሚሰማዎትን ይንገሩኝ፣ በበኩሌ፣ እንኳን የገዛ ልጆቼን ሰው ገድሎብኝ ይቅርና በስዎ ትዕዛዝ አምቦ ላይ መከላከያ ሰራዊትዎ (የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አይደሉም ብዬ ነው) የገደላቸውን ህጻናት ባስታወስኩ ቁጥር እርር ቅጥል እላለሁ። እርግጠኛ ነኝ የነዚህ ህፃናት ወላጆች ደግሞ እስዎን በአካል ቢያገኙዎት ሥጋዎን ዘልዝለው እንደሚበሉ፣ በተለይም ከህግ በላይ መሆንዎንና ዳኛ ፊት ቀርበው እንደማይፈረድብዎት ካወቁ። ግን ደግሞ ጊዜው ይዘገይ እንደሁ እንጂ፣ በሰው ልጆች ላይ በተለይም ደካማ የህብረተሰብ አባላት ላይ ጊዜያዊ ጉልበትን ተማማኖ ግፍ የፈጸመ ሰው፣ የሰማያዊው እንዳለ ሆኖ፣ ከምድራዊ ፍርድ እንኳ ሊያመልጥ አይችልም። ዘላለማዊ ጉልበት ወይም ዘላለማዊ መንግሥት የለም። ዶ/ርም ያረጃሉ፣ የወያኔ መንግሥትም ይወድቃል። ዛሬ የተማመኑበት አሸባሪው የአግዓዚ ጦርም እንደማንኛውም ነፍሰ ገዳይ ቡድን ይኮነንና እንዳልነበር ይሆናል፥ የመግደል ትዕዛዝ እየሰጣቸው ህጻናትን እንዲገድሉ ያዘዛቸውም ዶ/ር ደብረጽዮንም ከተደበቀበት ዋሻ ተፈልጎ ለፍርድ እንደሚቀርብ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ አይኖረኝም። የፖሊቲካ ሥልጣኑን ተመክቶ የሰው ልጅን መብት የገፈፈ ባለሥልጣን በህይወት እስካለ ድረስ ከፍርድ እንደማያመልጥ በበለጠ ለማወቅ ደግሞ እስቲ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ህጋዊ ሰነዶች ቢሮ ይሂዱና የስዎ የወያኔ መንግሥት በፊርማው ያጸደቃቸውን ዓለም ዓቀፋዊ ዉሎችን ይዘት ይመርምሩና የስዎን የወደፊት ዕጣ ምን እንደሆነ ይመልከቱ። ለማንኛውም የአምቦን ኅጻናት በጅምላ እንዲገድሉ ለመከላከያ ሰራዊቱ ትዕዛዝ መስጠትዎን ራስዎ በራስዎ ላይ በአደባባይ ስለመሰከሩ ለወደፊት የሚቋቋመው እውነተኛው ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ምሥክር ለማፈላለግ በቀጠሮ ብዙ የሚያመላልስዎት አይመስለኝም።
ዶ/ር ደብረጽዮን፣ እንዳለ የሚቀር ነገር የለም፥ ሁሉም በውዴታም ሆነ በግድ ሥፍራውን ይለቃል። እስዎም የሰው ልጅ እንደመሆንዎ መጠን ከዚህ የተፈጥሮ ህግ ውጭ ሊሆኑ አይችሉም። ስለዚህ እባክዎትን የዛሬውን ጉልበትዎን ተማምነው ግፍ አይሥሩ፣ ልጆቻችንንም አይግደሉብን፥ “እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያዊ አይደሉም እንዴ?” የሚል ጥርጣሬ ውስጥም አይክተቱን። በዚህ አስከፊ ጸረ ህዝብ ድርጊታችሁ ምክንያት የትግራይ ህዝብን ጨምሮ ከመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ደመኞች ሆናችኋል። የሥልጣን ዕድሜያችሁን ለማራዘም ስትሉ ብቻ፣ ህዝቦችን አታጋጩ፣ መብቴ ተገፈፈ ብሎ ሰልፍ የሚወጣውን ወገናችሁን እየገደላችሁ በዕብሪት ተሞልታችሁ መፎከሩን ብትተውና  ከህዝቡ ጋር የምትታረቁበትንም መንገድ በጊዜ ፈልጉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅር ባይ ነው። እንኳን እናንተን ይቅርና ከጣሊያን ጋር አብሮ የወጋን፣ ያደማንና ያቆሰለንን ባንዳ ሁሉ ይቅር ብለን አብረን ኖረን የለ! ስለዚህ እናንተም ከዚህ በትዕቢትና ዕብሪት ከተሞላ አጓጉል ህይወት ውጡና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችሁ ጋር በሰላም ለመኖር መላ ምቱ። የፖሊቲካ ሥልጣንን በሞኖፖሊ መያዝ ብቻ ሳይሆን ሃብቱንም ቢሆን እንኳን ለራሳችሁ ይቅርና ለልጅ ልጆቻችሁም የሚበቃ አፍርታችኋልና ይህንን “ለፍታችሁ ያገኛችሁትን“ ሃብት አርፋችሁ የምትበሉበትን ዘዴ ቀይሱ። የደቡብ አፍሪቃ ነጮች እንዴት የፖሊቲካ ሥልጣኑን  ዕርግፍ አርገው ትተው በኤኮኖሚው ዘርፍ ላይ ብቻ በማተኮር በሰላም ለመኖር እንደቻሉ ያጥኑት፣ ጠቃሚ ትምህርት ያገኙበታል። አለበለዚያ ዛሬ ሥልጣናችንን ተቀናቀኑ ብላችሁ፣ ለተበደሉት ጠበቃ፣ ድምጽ ለሌላቸው ደግሞ  ድምጽ  የሆኑ፣ እንኳን የአንድን ኢትዮጵያዊ ነፍስ ማጥፋት ይቅርና ክፉ ቃል እንኳ ካፋቸው የማይወጣቸውን፣ ብጫ ቱታ እያለበሳችሁና በካቴና ቀፍድዳችሁ በአደባባይ የምታሳፍሯቸው የበቀለ ገርባና የመረራ ጉዲና ዕጣ ፈንታ ይጠብቅዎታል። አሁንም በሩ አልተዘጋም፣ ከታቃናቃኝ ድርጅቶች ጋር በእኩልነት ቀርባችሁ ለመደራደርና ሥልጣንን በዕኩልነት ለመጋራት ዝግጁ ሁኑ። ሌላው አማራጭ ደግሞ አይቀሬው ህዝባዊ ዓመጽ አስከትሎት የሚመጣው ሱናሚ የመጣ ዕለት፣ ታሪክ ነጋሪ እንኳ ሳያስቀር ሁላችሁንም ጠራርጎአችሁ ሊሄድ ይችላልና በጥብቅ ያስቡበት።
እንግዲህ ዶ/ር ደብረጽዮን፣ ምርጫው የስዎ ነው፣ የሚሻልዎትን ደግሞ ከእስዎ በላይ የሚያውቅልዎት የለም። ከዚህ ከትዕቢት መንፈስ ተፈውሳችሁ፣ ኢትዮጵያውያንን ከመበደል እንድትቆጠቡና፣ ሁላችንም በዕኩልነት እጅ ለጅ ተያይዘን ይቺን ደሃ አገራችንን ሃብታም ማድረግ እንኳ ቢያቅተን፣ ደሃም ሆና ህዝቦቿ ግን በሰላምና በእኩልነት የሚኖሩባት፣ እነ በቀለ ገርባና አንዳርጋቸው ጽጌም ለተበደሉት ወገኖቻችን ጠበቃ ሆነው በመቆማቸው ብቻ ዘብጥያ ወርደው የሰቆቃ ህይወት ሰለባ የማይሆኑባት፣ የአምቦ እናቶችም ልጆቻቸው ተገድለውባቸው የሃዘን ድባብ እንዳይለብሱ፣ ፈጣሪ ብቻ ቅን ልቦና ሰጥቶአችሁ፣ ወደ እኛ እንድትቀላቀሉ ምኞቴ ነው። ፍላጎት ካለ ሁሌም መውጫ አለ ይላሉ ፈረንጆች። ምክራችንን ደግሞ አትናቁ። የዕድሜ ባለጸጎች ከመሆናችን ሌላ በልምዳችንም ካካበትነው ተነስተን ነውና ለመምከር የቃጣን። ህዝቡ አሁንም የወይራ ቅጠል ጉንጉን ይዞ ሲቀርባችሁ በልዋጩ ባሩድና እርሳስ አትስጡአቸው። እስቲ ሰከን፣ ተንፈስ በሉና፣ አየር ላይ መንሳፈፉን ትታችሁ ወደ ምድር ውረዱ። ጓደኛዬ ደረጀም እንዳለው፣ ሁልጊዜ ከጀግኖች ሰፈር የሚደለቀውን ከበሮ ብቻ ከመስማት፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከፈሪዎች ሰፈርስ ምን ይወራል ብላችሁ ለማዳመጥ ሞክሩ። ምክር አትናቁ፣ አንዲት ዕብድ ናት አሉ ጧት ተነስታ “ቅዳሜ ሰፈሩ በሙሉ ሊቃጠል ስለሚችል ቤቶቻችሁን ዘግታችሁ ገበያ እንዳትሄዱ” ብላ ስትለፈልፍ “ይቺ ዕብድ ደግሞ እንደ ለመደችው..….” ብለው ማንም ሳይዳምጣት ቀረና ቅዳሜ ሁሉም ወደ ገበያ ሄደ፥ ዕብዷም በተነበየችው መሰረት ችቦዋን ይዛ የሰፈሩን ቤቶች በሙሉ አቃጠለች፣ ገበያተኛው ማታ ተመልሶ ሲመጣ በሆነው ሁሉ ተናዶ እዬዬ ሲል የሰማችው ዕብድ “እኔኮ ነግሬአችሁ ነበር፣ ቤት ይቃጠላልና ገበያ አትሂዱ ብዬ” አለች አሉ። መጽሃፉም እኮ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ ነው የሚለው።
******
ጄኔቫ፣  30 ኦክቶበር 2017 /

No comments:

Post a Comment