Monday, February 18, 2013

አዜብ መስፍን የአዲስ አበባ ከንቲባ?


Azeb  Mesfin, wife of Ethiopian Prime Minister Meles Zenawi
(ዘ-ሐበሻ) የቀድሟ ቀዳማዊ እመቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ከዚህ ቀደም በምርጫ ትወዳድርበት የነበረውን የትግራይ ክልል በመተው በአዲስ አበባ ከተማ ለምርጫ እንደምትቀርብ ከወደ አዲስ አበባ የመጡ ዜናዎች አመለከቱ። “የአቶ መለስ ዜናዊን ሌጋሲ እኔ አስፈጽመዋለሁ” በሚል በአቶ መለስ የቀብር መታሰቢያ ፕሮግራም ላይ በድፍረት የተናገረችው ወ/ሮ አዜብ በአሁኑ ወቅት የፌደራሉ ፓርላማ አባል ብትሆንም ኢሕአዴግን ወክላ በመጪው የቀበሌና የወረዳ ምርጫ ላይ ኢሕ አዴግን በመወከል በበቂርቆስ ክፍለከተማ እንደምትወዳደር የዘ-ሐበሻ የአዲስ አበባ ዘጋቢዎች አስታውቀዋል።
በተለይ “አፍቃሬ ኢሕአዴግ” በመባል የሚታወቀው የአቶ ልደቱ አያሌው ኤዲፓ በዚህ ምርጫ ላይ ሙሉ በሙሉ ሳይሆን በከፊል ብቻ እንደሚሳተፍ ባሳወቀበት በዘንድሮው ምርጫ ከወ/ሮ አዜብ ጋር ይወዳደራል ተብሎ የሚጠበቀው የኢዴፓው ወንድወሰን ተሾመ ነው። አቶ ወንደሰን ተሾመ ኢዴፓ ብቸኛው ያቀረበው እጩ ሲሆን ይህም እጩ ከወ/ሮ አዜብ በሚወዳደሩበት የምርጫ ጣቢያ እንዲወዳደር የተደረገው የፖለቲካ ትርፍ ኢሕአዴግ ለማግኘት አስቦ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ትዝብታቸውን ለዘ-ሐበሻ ይገልጻሉ።
ባልተለመደ መልኩ ከትግራይ ክልል ተነስታ በአዲስ አበባ ከተማ ለምርጫ የምትወዳደረው ወ/ሮ አዜብ ምርጫው የተበላ እቁብ በመሆኑ በቀጥታ አሸንፋ የአዲስ አበባ ካቢኔ ውስጥ በመግባት የኦሕዴዱን ኩማ ደመቅሳ ቦታ በመቀበል የከተማዋ ከንቲባ እርሷን ለማድረግ የታቀደ ነገር እንዳለ ያስታውቃል ያሉት ታዛቢዎች በተለይም ከሰሞኑ ከወ/ሮ አዜብ ጋር ቅርርብ አላቸው የተባሉ አንዳንድ የአዲስ አበባ መጽሔቶች “የሴት ጠ/ሚ/ር ማየት ናፈቀን” የሚል ጽሁፍ ሁሉ መጻፉን ከወ/ሮ አዜብ ወደ አዲስ አበባ ከንቲባ መምጣት ጋር አያይዘውታል – ታዛቢዎቹ።
አቶ አርከበ እቁባይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በነበሩበት ወቅት በአዲስ አበባ የታዩ ለውጦችን ቢያደርጉም የአዲስ አበባ ሕዝብ በምርጫ 97 ወቅት “አርከበ ለከተማዋ እድገት ብትጥርም፤ ኢሕአዴግን ወክለህ ብቻ ስለመጣህ አንመርጥህም” የሚል ምላሽ ከህዝቡ አግኝቶ ኢሕአዴግ በምርጫው በ0 በተሸነፈበት ወቅት ከወ/ሮ አዜብ ጋር እንደማይዋደዱ የሚነገርላቸው አቶ አርከበ በባልየው በአቶ መለስ ዜናዊ “በአዲስ አበባ ላይ ቀለም ከመቀባት በስተቀር ያመጣኸው ለውጥ የለም” በሚል በስብሰባ ላይ በግልጽ ተሰድበው ነበር።
በአሁኑ ወቅት ሕወሃት በክፍፍል ላይ እንዳለ እየተዘገበ መሆኑ ይታወቃል። የአቶ ስብሃት እና የወ/ሮ አዜብ ግሩፕ በየፊናው ተፋጧል። አሁን ወ/ሮ አዜብን በአዲስ አበባ ከንቲባነት አማሎ ድርጅቱን የማዳን ሥራ እየተሰራ ነው የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ።

No comments:

Post a Comment