Sunday, November 22, 2015

በቴፒ ከተማ ላይ ውጥረት ነግሷል


ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ቴፒ ከተማ ውስጥ ውጥረት ነግሷል፣ የፌዴራል ፀጥታ ኃይሎች አካባቢውን በመቆጣጠር ላይ ይገኛሉ፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት የፀጥታ ችግር ዋነኛ መንስዔ ቴፒ ከተማ የምትገኝበት የኪ ወረዳ የእኛ ነው የሚል አቋም በያዙ የሸኮ ብሔረሰብ ተወላጆችና በሸካ ብሔረሰብ ተወላጅ አመራሮች መካከል አለመግባባት በመኖሩ ነው፡፡

አለመግባባቱን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ኃይል የመረጡ የአካባቢው ተወላጆች በመሸፈታቸውና ጊዜ እየጠበቁ ጥቃት በመፈጸማቸው ከፍተኛ ውጥረት መንገሡን መታዘብ ተችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከሚዛን ተፈሪ ወደ ቴፒ፣ ከሽሽንዳ ከተማ ወደ ቴፒ፣ ከማሻ ከተማ ወደ ቴፒ የሚወስዱ መንገዶች በሙሉ በደቡብ ክልል ልዩ ኃይል፣ በፌደራል ፖሊስና በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር እየተደረገባቸው ይገኛሉ፡፡

ቁጥጥሩ ማንኛውም መንገደኛ ላይ ጥብቅ ፍተሻን የሚያካትት ሲሆን፣ የፀጥታ ኃይሎች አካባቢውን በመቆጣጠር ላይ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት ሁሉም ነዋሪዎች ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በከተማ ውስጥ እንዲዘዋወሩ አይፈቀድም፡፡ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ግድያ ባይፈጸምም ከዚያ በፊት በነበሩት ጊዜያት በየምሽቱ የሰው ሕይወት መጥፋቱ የተለመደ እንደነበር ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የከተማው ነዋሪ እንደገለጹት በየምሽቱ የሰው ሕይወት መጥፋቱ የተለመደ ነው፡፡

“የፀጥታ ችግሩን ለመቅረፍ በተጠሩ መድረኮች አስተያየት የሰጡ ሰዎች ላይ ዕርምጃ የተወሰደ በመሆኑ፣ በአደባባይ ሐሳብን መግለጽ በራስ ላይ እንደመፍረድ ይቆጠራል፤” በማለትም የችግሩን ጥልቀት አስረድተዋል፡፡

የሸኮ ተዋላጆች የሚያነሱት ጥያቄ መሠረቱ በቤንች ማጂ ዞን የሚገኘው ሸኮ ወረዳ፣ በሸካ ዞን የሚገኘው የኪ ወረዳና በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን የሚገኘው ሜጢ ወረዳ፣ አንድ ላይ ተዋህዶ ዞን እንዲሆንና ዞኑንም የማስተዳደር ሥልጣንም እንዲሰጣቸው ነው፡፡

የማጃንግ ብሔርን ማጠቃለል የፈለጉበትን ምክንያት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሸካ ዞን ተወላጅ እንደገለጹት፣ የማጃንግና የሸኮ ብሔረሰብ አባላት ለዘመናት አብረው የኖሩና ባህላቸውም ተመሳሳይ በመሆኑ ነው፡፡

በቴፒ ከተማ የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር ብዛት ከ35 ሺሕ በላይ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment