Wednesday, April 10, 2013

የነፃነት ዋጋ በምን ይተመን?

እነሆ ዛሬ የምንጓዘው ከሳሪስ አቦ ወደ ቃሊቲ መናኽሪያ ነው። የሰው ልጅ ለኑሮ የሚደረግ ትርምስ ጎዳናው ላይ ይንቀለቀላል።
እንደወትሮው የኑሮ ንረት እያፍገመገመን ይኼው ዛሬ ላይ ደርሰናል። ‘ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል’ ያስብላል የአብዛኞቻችን አኗኗር ሲታይ። መኖርን መኖር ሊያስብሉ የሚችሉት መሠረታዊ ነገሮቻችን እስካሁን በጥያቄ ሰገነት ላይ እንደተሰቀሉ ናቸው። አንዳች ትንፋሽ እስኪያጠፋቸው እንደ ሻማ ውስጣችንን ያቀልጣሉ።

‹‹የዚህ ሁሉ ሰው ትዕግስት እንደ ሰም ቀልጦ ያለቀ ቀን ምን ልንሆን ነው?›› ይባባላል አንዳንዱ መንገደኛ እርስ በእርሱ እየተንሾካሾከ። ‹‹አይ እናት አገሬ! እስካሁን እኮ ለመኖር የተመኘ እንጂ የኖረ ትውልድ የለሽም። ይኼው እኛስ መቼ ከሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎት (መጠለያ፣ ምግብ፣ ልብስ) ጥያቄ ተሻገርን?›› ይላል ታክሲ ጥበቃ አብሮኝ የቆመ ወጣት። ‘ወጣት ተስፋ ፍለጋ የባከነበት ዘመን’ ይላል ውስጤ የአዕምሮዬን የሐሳብ ልጓም ጥሶ። በዚያው ልክ ደግሞ ጥቂት የሚባሉት ኑሯቸውን ለሌሎች ኑሮ መቃናት ሰውተው ሲንገላቱ ጎዳናው ያሳየናል። አዎ፣ ግን ጥቂቶች ናቸው። እነርሱም አሸናፊ መሆን የሚችሉት የብዙኃንን ጥቅም ለግላቸው ተድላ ለማዋል የሚተጉ ተንኮለኞችን ሴራ መግታት ከቻሉ ብቻ ነው። ለመልካም ነገር የመተባበር ቅስም በተሰበረበት በዚህ ዘመን የበጎ ነገር አሸናፊዎችን ማየት ቀላል ነገር አልሆን ብሏልና። ‹‹የጎመን ድስት ይውጣ የገንፎ ድስት ይግባ›› ሲባል እንደሰማነው የግለሰቦች ዘመን ወጥቶ የሕዝብ ዘመን (በተግባር) ሲገባ የምናየው መቼ ይሆን? ‹‹ሊነጋ ሲል ይጨልማል›› ብለን ለጊዜው እንለፈው፡፡

በራሪ ታክሲ አግኝተን ተሳፍረናል። የቻለችንን ችላ የተረፉዋትን እንደበተነች ልትከንፍ በሾፌሯ አማካይነት ታክሲዋ ትጣደፋለች። በራሪ ነቻ! በበራሪ ዕድሜ በራሪ ታክሲ ማግኘት የሚቻለው ሲታደሉ ብቻ ነው። ሆኖም ወያላው እየጫነ የነበረው የአንዲት ተሳፋሪ ዕቃ ተጭኖ አላልቅ በማለቱ እየታገለ ቆመናል። ‹‹አቦ ምንድን ነው ይኼ? ከነገርኩሽ ብር ላይ ሦስት ብር መጨመርሽ ነው፤›› አላት ተማሮባት። ‹‹በእናትህ የለኝም። ሰው አገር ሲለቅ እንዲህ ነው የሚሸኘው?›› አለቸው የልምምጥ የውሸት ፈገግታ ገጿ ላይ ዘርግታ። ‹‹ታዲያ ይኼን ሁሉ ዕቃ በሰባት ብር? ደግሞ ሰው አጣብቤልሽ?›› አላት ሙግት በለመደ አንደበቱ። ‹‹ይኼን ጊዜማ እኛ ነን ሰበባችሁ? እኛን እንደ ዕቃ ቆጥራችሁ እንዳሻችሁ ወትፋችሁ ስትጭኑን ግን ምንም አይመስላችሁም?›› አለው አንድ ቁጡ ተሳፋሪ። ወያላው መልስ አልመለሰለትም። ወደ አንድ ጥቅስ ጠቆመውና ኮተቷ ወደአስቸገረው እንስት ዞሮ ‹‹እሺ በቃ ሁለተ ብር ትጨምሪያለሽ፤›› አላት። ‹‹አንተ በእናትህ? ምን ነው ምንም ቢሆን እኮ የኖርኩበት ከተማ ነው።

ዛሬ ብለቀው ጠብቀህ . . . ተው በእናትህ ገና ለትራንስፖርት ብዙ ነው የምከፍለው፤›› ትለዋለች። ጥቅስ የተጋበዘው ተሳፋሪ፣ ‹‹እኔን ነው በማያገባህ አትግባ? (ጥቅሱን እያነበበ) እንኳን አንተ መንግሥትም አላለኝ። የመናገር መብት አለኝ እሺ፤›› እያለ ይጦፋል፤ ቁጣ ቁጣ እያለው። ‹‹ወዴት ነው ስደቱ?›› ትላታለች ወፈር ያለችው ወጣት ተሳፋሪ በወያላው ካልከፈልሽ የምትባለዋን ምስኪን። ‹‹ወደ መተሃራ፤›› ትመልሳለች። ‹‹አገርሽ እዚያ ነው?›› ትጠይቃታለች። የወያላውና የንዴታሙ ንትርክ በመሀል ጎላ። ‹‹መንግሥት? አላለም እንዴ? ግለሰብ ከሕግ በላይ በሆነበት አገር፣ ጎሳ ከአገር ይበልጥ ይሰፋብናል በሚባልበት ጊዜ መንግሥት ይለኛል እንዴ!›› ወያላው ያመራል። ‹‹. . . አገሬስ እዚሁ ነበር። ምን ላድርግ ኑሮን አልቻልኩትም። ዘመዶቼ መተሃራ ናቸው። ኧረ ተይኝ እንግዲህስ ሁለተኛ ወደ እዚህ እግሬን የማነሳም አይመስለኝ፤›› ትላታለች ከሁላችንም ይልቅ ረጅም መንገድ ያቀደችዋ ምስኪን ተሳፋሪያችን። ለነገሩ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ሁሉም በመሰለው አቅጣጫ ለመሰደድ ያቆበቆ ነው። ግን ሽሽት ከምን? ከዘመን ወይስ ከአገር?

የወያላውና የደም ፍላታሙ ጎልማሳ አንድ ሁለት እየተካረረ ሄዶ ለቡጢ ከመጋበዛቸው በፊት እንዲረጋጉ አንድ ነገር ማድረግ ነበረብን። ወዲያውኑ ታክሲያችን መክነፍ ጀመረች። አንድ ቀልደኛ ‹‹አደራ ‘ኮብልስቶን’ አጠገባችሁ ካለ ገለል በማድረግ ተባበሯቸው፤›› ሲል ይቀልዳል። ‹‹አሁንማ ‘ከኤድስና ከኮብልስቶን ራሳችንን እንጠብቅ’ የሚል ‘ቢልቦርድ’ ሳያጥለቀልቀን ይቀራል?›› ይላል አጠገቡ የተቀመጠ የዚሁ ቀልደኛ ወጣት ብጤ። ‹‹ምን ነው ሰሞኑን ‘ኮብልስቶን’ ላይ ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነው ቀልዱ?›› አለች ከኋላ መቀመጫ አራት ሆነን ከተቀመጥነው አንዷ። ‹‹አልሰማሽም (ጓደኛዋ ሳይሆን አይቀርም) ሰሞኑን በሥራ አለመግባባት በኮብልስቶን የተጨፋጨፉትን? አሁን መንግሥት ምን ይል ይሆን? ‘በአጎረስኩ እጄን ተነከስኩ’ ነው የሚለው መቼም፤›› አላት ለማሾፍ ድምፁን እያቀጠነና እያወፈረ።

‹‹ምን ይኼን ያህል ሞት ብርቅ ሆኖ ነው? እዳው የቤተሰብ ነው አይምሰልህ!›› አለችው። በዕድሜ ተለቅ ያሉ ተሳፋሪዎች በወያላውና በቁጡው ሰው መሀል ገብተው ነገሩን በማለዘብ ላይ ናቸው። ወፈር የምትለዋ እንስት ወያላው ሁኔታውን አይቶ ዕዳውን ያበዛባትን ምስኪን ሒሳብ ‹‹እኔ እከፍልሃለሁ፤›› ስትል እንሰማለን። አንዱ ሲገነባ አንደኛው ያፈርሳል። አንደኛው ሲሸሽ ሌላው ይሸኛል። የአንዱ መልካም ምላስ ቁጣን እያበረደ ይኖራል። የአንዱ ጦስ ለአንዱ የመኖር ትርጉም መሠረትነቱ እነሆ እንዲህ ይቀጥላል።

ወያላው በዕቃ በተጨናነቀው ሒሳብ መቀበያ መድረኩ ላይ እንደቆመ የመንገዱን ታሪፍ ሰብስቦ ጨርሷል። መሀል አካባቢ የተቀመጠ ተሳፋሪ ስልክ ጠራ። አነሳው፣ ‹‹ሃሎ፣ አቤት? ሃሎ . . . ሃሎ? አይሰማም፤›› ተዘጋ። ‹‹ወይ ‘ኔትወርክ’ እንዲህ በእንቁልልጭ ይጫወትብን ጎበዝ?›› ይላል ብሽቅ ብሎ። ‹‹የኑሯችን ባህሪ ነው። መልመድ ነው ያለን አማራጭ፤›› ትላለች ቀጭኗ መሀላችን የተቀመጠችው። ጓደኛዋ ይስቃል። (ደስ ይበላት ብሎ ይመስላል፣ ይሉኝታ!) ተደውሎለት የነበረው ተሳፋሪ ራሱ መልሶ ደውሎ ማናገር ጀምሯል። ‹‹ሄሎ አቤት አቤት! የት ደርሳችኋል? ምን? እናንተ ሰዎች ዓላማችሁ የሰውን እንጀራ መዝጋት ነው ልበል? አንዲት ‘ዋየር’ ለመቀጠል ይኼን ያህል መለመን አለብኝ? ያውም በራሳችሁ ጥፋት?›› እያለ ቀጠለ። የመብራት ኃይል ጣጣ መሆኑ ነው። ‹‹የፈረደበት፣ ባለፈው እኔም ዘንድ መብራት እልም ሲል አንዲት ገመድ ተቃጥላ መጥቶ ቆጣሪ ለማስተካከል ያየሁት አበሳ?›› በማለት አንድ አዛውንት ሮሮ ጀመሩ። መብራትና መብራት ኃይል ወዲያውኑ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆነው እርፍ።

‹‹እኔን የገረመኝ ኑና ሥሩልኝ ብላቸው የተመደቡት ሠራተኞች አራት ብቻ ናቸው ብለው የሰጡኝ መልስ ነው። አዲስ አበባን ለሚያህል ከተማ አራት ሰው ብቻ? ጉድ እኮ ነው የምንሰማው?›› ሲል አንድ ብርቱ መሳይ ጎልማሳ፣ ‹‹አሁንማ በተለይ ዝናብ ሲጥል ከመብረቅ ይልቅ የትራንስፎርመር ፍንዳታ መፍራት ጀመርን እኮ፤›› አለ ለመኮመክ ወጣቱ። ‹‹ኧረ ተው በፈጠራችሁ። አሁን ደሃን ማማት ደግ ነው? ምናለ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽ ዕቅዱ መሳካት ላይ ብናተኩር?›› ይላል አዲስ ድምፅ። ‹‹አይዞን ‘አሁን ዓባይ ሲገደብ መብራት መጥፋት የለ፣ ትራንስፎርመር መፈንዳት የለ፣ ሙስና የለ፣ የቤት ችግርና የመልካም አስተዳደር እጦት የለ፤ በቃ ሁሉንም ድራሹን ነው የምናጠፋው’ ይል ነበር ኢቲቪ መሀላችን ቢኖር ኖሮ!›› ብሎ ለመሳለቅ ሞከረ ወያላው። በሚኮረፈው ስንስቅ በሚሳቀው ስናኮርፍ ዕድሜና ጊዜ እንደሁ ላፍታም አልቆሙ። መጨረሻችን ግን ምን ይሆን?

ይልቅ ወደ ታክሲያችን መጨረሻ እየተጠጋን ነው። ቃል የሰለቸውን ዝምታ እየገለጸው ጥቂት እንደተጓዝን ወራጅ ባዩ እየተበራከተ ሄደ። ሳናውቀው በጨዋታ የፈጠርነው ዝምድና ለስንብት ሲጣደፍ ይታያል። ቀድመውን የሚወርዱት ተሳፋሪዎች እጅ ነስተውን ይሰናበታሉ። ‹‹አቤት! እውነት እኮ ሁሌ እንዲህ ብንዋደድ እኛን የመሰለ ጠንካራ፣ እንደኛ ሥልጡን የሚሆን ሕዝብ አልነበረም፤›› ይላሉ አዛውንቱ ታክሲ ውስጥ በአጭር ጊዜ የገነባነው የአንድነት መንፈስ ደስ አሰኝቷቸው። አጠገባቸው የተቀመጠ ጎልማሳ፣ ‹‹መዋደድ ማን ይጠላል ብለው ነው አባት? እንደሚያውቁት ግን እየመራ የሚያስጀምረን ከሌለ ከባድ ሕዝቦች ነን፤›› አላቸው። አልገባቸውም። ‹‹እንዴት?›› አሉት በከፊል ወደእሱ በመዞር። ‹‹ፍቅርን ከአንደበት ባለፈ በተግባር የሚያስተምረን አካል እንፈልጋለና። አዩ ሁሌም ሕዝብ ያለ መሪ፣ መንጋ ሁሌም ያለ እረኛ ዋጋ ኖሮት አያውቅም። ሆኖ የሚያሳየውና አርዓያ የሚሆንለት አካል ይፈልጋል ሕዝብ። ያኔ በዕድገት፣ በሥልጣኔና በልማት የሚያቆመው ምንም ነገር አይኖርም፤›› ሲላቸው ራሳቸውን ነቅንቀው ‹‹ትልቅ ነገር ተናገርክ።

በተለኝ እኛ በአሁኑ ጊዜ ከፖለቲካ ዲስኩር ይልቅ ተግባራዊ ዕርምጃ ነው ማየት የምንናፍቀው። ለሕዝብ ቆሜያለሁ ከሚል መንግሥት ሕዝባዊ ሥራ ማየት ናፍቆናል። ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና ጥልፍልፍ የቢሮክራሲ አሠራር አቅለሽልሾናል። እንኳን እሬት ማርም ሲበዛ ይመርም አይደል? እናም የምንፈልገው በነፃነት ኖረን በነፃነት መሞት ነው፡፡ ከነፃነት በተቃራኒ ያለው ባርነት ነው፤›› ብለውት ‹‹እኔን እዚህ ጋ ጣለኝ›› ሲሉ ታክሲዋ ቆመች። የነፃነት ዋጋ በምን ይተመናል እያልኩ ሳሰላስል ወያላው ‹‹እዚህ ነው መጨረሻው!›› ሲል መውረድ ግድ ሆነብን። መልካም ጉዞ!

No comments:

Post a Comment