Wednesday, April 24, 2013

“ፍየል ወዲህ…”

ይኸነው አንተሁነኝ
ሚያዚያ 23 2013

“ከእንግዲህ የገበሬው ችግር የርሃብ ችግር ሳይሆን የሚያመርተውን የተትረፈረፈ ምርት በርካሽ እንዳይጥለውና በገንዘብ መልክ የሚኖረው ገቢ እንዳያንስበት ነው፡፡” ባለራዕዩ መለስ ዜናዊ በዘመነ አካለ ስጋው የወሸከተው ደርዝ የሳተ ቃል
የተለያዩ መንግስታት ሕዝባቸውን ለማስተዳደርና ቁሳዊ መንፈሳዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት፣ የሀገራቸውን ጸጥታና ደህንነት አስጠብቆ ለመምራት፣ እንዲሁም ከሌላው ዓለም ጋር ጥቅምን ያገናዘበ ግንኙነት ለመመስረት የሚያግዙ የተለያዩ ፖሊሲዎችን ያጸድቃሉ ይተገብራሉም። አፈጻጸሙንም በተመለከተ የተለያዩ መመዘኛዎችን በማውጣት ይከታተላሉ፤ ተጠቃሚውን ምሕበረሰብ መሰረት ያደረገ የእርምት እርምጃዎችንም መውሰድ ከአንድ መንግስት ነኝ ከሚል አካል የሚጠበቅ ሃቅ ነው። ይህ ሲሆን እንግዲህ የተዘጋጁትን ፖሊሲዎች፣ አተገባበራቸውንና ሊያመጡ የሚችሉትን ውጤት በተመለከተ የሚወጡ መንግስታዊ ቅድሚያ መግለጫዎችም ሆኑ ማብራሪያዎች ከዚያም ሲያልፍ እቅዶችና የተስፋ ቃሎች በሙሉ በባለሙያ የተቃኙና በመሰረታዊ የትንበያ ሳይንስ የተዳሰሱ ሊሆኑ መቻላቸው አያጠያይቅም እጅግ በጣም ቢያንስ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ለሚሰማቸው መንግስታት።
እስከ አሁን ያልነውን ሀቅ ይዘን ወደ ሀገራችን ስንመጣና ከላይ የተጠቀሰውን የባለራዕዩን ንግግር ከዚህ ሀቅ ጋር ስናወዳድር በፓርላማ የጭብጨባ አጀብ ሞቅታ፣ በጉሽ ጠላ ብርታት አልያም በምርቃና መንፈስ የተነገረ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር አይኖረንም። ምክንያቱም ያለ እረፍት ለዘመናት ስትታረስ የኖረችና ለምነቷን ያጣች የበሬ ግንባር የምታክል መሬት ይዞ ዓመት ሙሉ የሚቆዝምን ገበሬ የትኛው የግብርና ፖሊሲ የተትረፈረፈ ምርት ባለቤት ሊያደርገው እንደሚችል ከባለራዕዩ በቀር የሚያውቅ የለምና። ባለፉት ጥቂት ዓመታትም የታየው ገበሬው የተትረፈረፈ ምርቱን የሚሸጥበት ገባያ ሲያጣና እንደተባለውም በርካሽ ሲሸጠው ሳይሆን ልሰው የማያውቁ ልሰው ወይም ቀምሰው የማያውቁ ቀምሰው የእህል ዋጋ ከመቸውም በላይ ሲወደድ ነው። “የግፍ ግፍ…” እንደሚባለው ይራበውም ይጥማው ያችኑ ቁራጭ መሬት ይዞ የሚያዘግመውን ገበሬ ሕወሃት መራሹ ገዥ በልማትና ኢንቨስትመንት ሰበብ እያፈናቀለ ለልመናና ለባሰ ግፍና በደል እየዳረገው መሆኑ ሲታይ የባለራዕዩ ንግግር በሞቅታ እንጅ ጥናትን መሰረት ያደረገ እንዳልነበረ ያሳያል። የሚታየው ያገጠጠ እውነት ያረጋገጠውም ገበሬው ትርፍ አምርቶ ሲደሰት ሳይሆን ከትናንሽ እስከ ትላልቅ ከተሞቻችንን ወረራ በሚመስል መልኩ በስደት ሲያጥለቀልቅ ነው። የቀረውም
ከቀጣሪነት ወደ ተቀጠቀሪነት ደረጃ ወርዶ በገንዛ መሬቱ ላይ ለአረብና ለሕንድ ገበሬዎች አሽከር በመሆን የስቃይ ሂዎት ሲገፋ እንጅ ትርፍ አምርቶ ሲሻሻል አልታየም። ታዲያ ይህ እንግዲህ ከሕወሃት እጅግ ብዙ ደርዝ የሳቱ ቃሎች አንዱ መሆኑ ሲታወስ ወያኔ እውን የማይሆን የተስፋ ዳቦ እያሳየ ይገዛል ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ሕወሃት የስኳር ዋጋ መወደድን አስመልክቶ ባሰራጨው ደርዝ የሳተ መግለጫ ስኳር ቀምሰው የማያውቁ በመቅመሳቸው ለጊዜው አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ሊጣጣምልን አልቻለም ብሎ፤ ነገር ግን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቀመር ችግሩ በቅርብ ጊዜ እንደሚስተካከል ነግሮን ነበር። ዛሬ ታዲያ ከስድስትና ሰባት ዓመታት በሗላ ለኒያ በሻጉራ ለታሙት መከረኛ ያገራችን ገበሬዎች ይቅርና ለከተሜው  ሳይቀር ስኳር ማየት እንደ መስቀል ወፍ ሲናፈቅ ስናይ የህወሃት ባለስልጣናት ንግግር በግምትና በአቦሰጥ እንደነበር ምስክር አያሻንም። አሉ የሚባሉት ስኳር ፋብሪካዎች የሚያመርቱትና በዚሁ ምስኪን ሕዝብ ሰበብ ከውጭ የሚገባው ስኳር ግን ለሕወሃት ባለስልጣናትና ጥቅም ተጋሪዎች ሃብት ማካበቻ ሽልማቶች ሆነዋል።
እንዲሁ ከዓመታት በፊት በቀን ሶስቴ ትበላላችሁ ትጠግባላችሁም ተብሎ በጎጠኛው መለስ ተነግሮን ተንቢቱ ስቶ ጭራሽ በጊዜው ከነበረን ሃቃችን በታች ተምዘግዝገን በመውረድ ላይ እንገኛለን። መናገር የማይሰለቸው ሕወሃት ግን አሁንም ሊመጡ ስለሚችሉ የፍስሃ ዘመናት ደርዝ የሳቱ ቃሎችን ከመግባት አልቦዘነም። እንዲያው ነገር እንዳላበዛ እንጅ ዘመኑ የፌዴራሊዝም ነው ስለዚህም ክልሎች ራሳቸውን ያስተዳድራሉ፤ የፖለቲካውን ምህዳር እናሰፋለን ለዓለምም እንከን የለሽ ምርጫ እናሳያለንስ ተብሎ አልነበር። ደርዝ ከሳቱ አይቀር እንዲህ ነው።
የሃብትና የስልጣን ክፍፍልን በተመለከተም “የኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔረሰቦች ሕዝቦች ለሃብትና ለስልጣን እኩል መብት አላቸው” በሚል ደርዝ በሳተ ቃሉ ያናፋ የነበረው ሕወሃት የሀገራችንን አብዛኛውን የንግድ እንቅስቃሴ የራሱ ንግድ ኤምፓየር በሆነው “ኤፈርት” አማካኝነት ተቆጣጥሮ ሁሉም የብርና የሳንቲም ኖቶች ወደ “ኤፈርት” ይፈሳሉ እያለን ይገኛል። ይህንንም በተሳካና ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማስፈጸም ከኤፈርት የስራ እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት ያላቸውን መስሪያ ቤቶች በዘረኛ አገዛዙና በራሱ ቁርጠኛ ሰዎች ተቆጣጥሮ የሃብትና የስልጣን ክፍፍሉን አንድ አቅጣጫ ብቻ ይዞ እንዲሄድ እያደረገው ነው።
የተመኘውንና የተናገረውን የመናዊነትን ቀርቶ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን የጎጥ አለቃ እንደሆነ የተሰናበተውን ባለራዕዩን ገዥ ጨምሮ ብዙዎቹ የሕወሃት ሰዎች ነባራዊውን ርሃብ በዘነጋ ምኞት፣ ዓለም ያወቀውን ስደታችንን ባላስታወሰ ተስፋ፣ አቅማችንን ባላገናዘበ ጀብደኝነትና የፖለቲካ ጥቅም ፍለጋ ባምስት ዓመት አባይን እናቆማለን እያሉ ደርዝ ያልጠበቀ ቃል ይመግቡናል። ይህን ቃላቸውን ለማስፈጸም በሚልም ድህነት ያደቀቀውን ምስኪን ሕዝባችንን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ሳይቀር በዚሁ የሳተ ቃል ያባብላሉ። በየደረሱበት ከተከራዩት የስብሰባ አዳራሽ ተዋርደው የመባረራቸው የዜና ዘገባ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየደረሰን ቢሆንም። የሆነው ሆኖ ግን በእርግጥ የአባይ ግድብ ወሬ እውነት ከሆነ ምነው ታዲያ ከሀገራችን አልፎ በአፍሪካ ተወዳዳሪ ባለሃብት እየሆነ ከመጣው ኤፈርት ኩባንያ ሀብት ትንሽ ዘገን አልተደረገም? ወይስ ኤፈርት በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ለምለም ሳር እየጋጠች ትግራይ ላይ  እንደምትታለብ ላም የትግራይ ጎጠኞች ብቻ ነው? ግድቡም ከተሰጠው የግንባታ እድሜ ግማሽ የሚሆነውን እየጨረሰ ነው ስራው ግን ባለህበት እርገጥ እንደሆነ ከቃላት በላይ ማረጋገጫዎች አሉ። ታዲያ ይህስ ቢሆን ደርዝ የሳተ ቃል ላለመሆኑ ከዚህ በላይ ማረጋገጫ ማሳየት ያስፈልግ ይሆን።
ከሕወሃት ደርዝ የሳቱ ቃሎች ይልቅ ሀገራችን ብዙ አንገብጋቢና ያገጠጡ ችግሮች አሏት። ሕዝባችን ነጻ አልወጣም በጎጠኝነት የአገዛዝ ቀንበር ስር ይማቅቃል። በየዓመቱ ባስር ሽዎች የሚቆጠሩ ዘለው ያልተገቡ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሕወሃት የተምታታ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት ተስፋ አጥተው በስደት ዓለም እየተንከራተቱ ይገኛሉ። በሕወሃት ውስጠ ተንኮል የተነሳም የሀገር ውስጥ ስደተኛው የትየለሌ ሆኗል። ወደድንም ጠላንም ዛሬ በዓለም ፊት ከውርደት በታች ተዋርደን የዓለም መሳቂያዎች ሆነናል። ሕወሃት ግን በኛ ኪሳራ የንግድ ኢምፓሩን በአፍሪካና በዓለም ደረጃ እያስፋፋ ቀጥሏል። ይህ የሀገራችን ቀውጢ ወቅት እኛን ካላስነሳን፤ ይህ የሕዝባችን ችግር እኛን ካላነቃን፤ ምን በጽናት ሊያቆመንና ሊያስተባብረን ይችላል? ይጠቅማል ባልነው መንገድና ወቅት ሁሉ የሕወሃትን ጎጠኛ አገዛዝ የሚያዳክም  የሀገራችንን ሰላምና ጸጥታ የሚያስጠብቅና የሕዝባችንን ጥንካሬና ስነ ልቦና የሚያጠናክሩ እርምጃዎችን እንውሰድ። የኢትዮጵያዊነታችን ክብርና ኩራቱ ሀገራችን ከሕዝባችን ጋር በሰላም ተጠብቃ አስከኖረች ድረስ ብቻ ነውና።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *
You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <strike> <strong>


No comments:

Post a Comment