Wednesday, August 14, 2013

ወጣቱ(ቄሮ) የነፃነት መግለጫ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙ የኦሮሞ ልጆች ላይ የተላለፈ ኢፍትሀዊ ውሳኔ እና በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተከፈተው ዘመቻ ትግሉን ከግብ እንዳይደርስ አያደርገውም፤


ወጣቱ(ቄሮ) የነፃነት መግለጫ
 
ወጣቱ(ቄሮ) የነፃነት መግለጫ | Hagayya 14, 2013
QEERROO
QEERROO
እ.ኤ.አ ነሐሴ/2013 የወያኔው ፍርድ ቤት ባዋለው ችሎት በእነ ደቻሳ ዊርቱ መዝገብ በተከሰሱ 24 የኦሮሞ ተማሪዎች ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ከእውነት የራቀና ሆን ተብሎ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተከፈተው ዘመቻ አካል ነው፡፡ በመሆኑም ለዚህ ኢፍትሀዊ ውሳኔ የወያኔ መንግስት እና ቅጥረኞቹ በኦሮሞ ህዝብ ላይ እያደረሱ ለሚገኙት ወደር የሌለው ግፍ እና በደል ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡
የወያኔ መንግስት የኦሮሞ ተማሪዎችን ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመሰብሰብ “የኢፌዲሪ መንግስት በአግባቡ እና በፍትሀዊነት የኦሮሞን ህዝብ እያገለገለ አይደለም እያላችሁ ህዝቡ በመንግስት ላይ እንዲያምፅ ለማድርግ አስተባብራችኋል ስለዚህ በአሸባሪነት ወንጀል ተጠያቂ ናችሁ” በማለት የከሰሳቸው ሲሆን ችሎት በማቋቋም በኦሮሞ ልጆች ላይ የረዥም እና የአጭር ጊዜ እስራት ብይን አስተላልፎባቸዋል፡፡ የመብት ጥያቄ ለመጠየቅና ሰልፍ ለመውጣት አስባችኋል በማለት ተማሪዎችን ማሰር እና ከትምህርት ገበታቸው ላይ ማባረር ለረጅም አመታት ሲፈፀም የቆየ ነው፡፡ “የኦሮሞ ህዝብ ሰልፍ ሊወጣ ነው ብላችኋል” በማለት ተማሪዎችን በህዝባዊ አመፅ አስተባባሪነት በመፈረጅ አሰቃቂ ድርጊት ከመፈፀሙም በላይ ኢ-ፍትሀዊ ውሳኔ ስለተላለፈባቸው ብሄራዊ የኦሮሞ ወጣቶች ንቅናቄ ይህን ድርጊት በጥብቅ ያወግዘዋል፡፡ የወያኔ መንግስት የኦሮሞ ተማሪዎችን በማሰር እና የኦሮሞን ህዝብ ከመኖሪያ አካባቢው በማፈናቀል የፖለቲካ ችግሩን ለመፍታት መሞከሩ የህዝቡን የፀረ ባርነት ትግል መቀልበስ እንደማይችል እንገነዘባለን፡፡
የኦሮሞ ተማሪዎች በአንድ በኩል የፀረ ባርነት ትግሉን ለማቀናጀት አስባችኋል እየተባሉ እየተወነጀሉና እየታሰሩ የሚገኙ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ባልፈፀሙት ድርጊት አሸባሪ ተብሎ በመፈረጅ ትርጉም የሌለው ክስ ቀርቦባቸው የእስር ውሳኔ ከተሰጠባቸው መካከል፡-
1. ተማሪ ደቻሳ ዊርቱ፡- ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ከ 8 ዓመት፣
2. ተማሪ ኤቢሳ ራቴሳ፡- ከኦምቦ ዩኒቨርሲቲ 8 ዓመት፣
3. ተማሪ አዳሙ ሽፈራው፡- ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 8 ዓመት፣
4. አቶ በርሲሳ ለሚ፡- የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆን 4 ዓመት፣
5. መምህር ብርሃኑ እምሩ፡- የኮተቤ ኮሌጅ መምህር ሲሆን 4 ዓመት፣
6. ተማሪ ጌቱ ሳቃታ፡- ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 3 ዓመት፣
7. ተማሪ ሴና መረራ፡- ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 3 ዓመት፣
8. ጋዜጠኛ አለሙ ተሾመ፡- የአዲስ አበባ ነዋሪ ሲሆን 3 ዓመት፣
9. ተማሪ ዲሪብሳ ዳምጤ፡- ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 3 ዓመት፣
10. ተማሪ ስለሺ ሶሪ፡- ከሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ 3 ዓመት፣
11. ተማሪ አብዲሳ ጉደታ፡- ከመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ 3 ዓመት፣
12. ተማሪ መሬሳ ኃ/ኢየሱስ፡- ከአዲስ አበባ የግል ኮሌጅ 3 ዓመት፣
13. ተማሪ ደሜ ዘሪሁን፡- ከአዲስ አበባ የግል ኮሌጅ 3 ዓመት፣
14. ተማሪ አብዲ ደረጀ፡- ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ 4 ዓመት፣
15. ተማሪ አለማየሁ ራጋሳ፡- ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ 3 ዓመት፣
16. ተማሪ ደረጀ ጌቱ፡- 3 ዓመት፣
17. ተማሪ ዳግም በቀለ፡- ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ 3 ዓመት፣
18. ተማሪ ጌታቸው አበራ፡- ከሻምቡ 3 ዓመት፣
19. ተማሪ ሻፊ ሰኢድ፡- ከጅማ ዩኒቨርሲቲ 3 ዓመት፣
20. ጅሬኛ ደሳለኝ፡- 3 ዓመት ከ3 ወር፣
21. አለማየሁ ረጋሳ፡- 3 ዓመት፣
22. ሻሼ ሰኢድ፡- 3 ዓመት፣
23. መምህር ለሚ፡- 4 ዓመት፣ እንዲሁም
24. አለሙ ተሾመ፡- 3 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡
ከላይ ስማቸው የተገለጹት የኦሮሞ ተማሪዎች ያለምንም ጥፋት ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ከትምህርት ገበታቸው በመያዝ የታሰሩ ሲሆን ይህ መንግስት በኦሮሞ ተወላጆች ላይ እየወሰደ ያለው የጠላትነት ውሳኔ የተጨቋኙን ህዝብ ቁስል የበለጠ ያደማል እንጂ ትግሉ እንደማያቆም መታወቅ አለበት፡፡
ብሄራዊ የኦሮሞ ወጣቶች ንቅናቄ የኢፌዲሪ መንግስት በኦሮሞ ላይ የሚፈፅመውን አረመኔያዊ ድርጊት እንዲያቆም በጥብቅ ያሳስባል፡፡
ትግሉ ይቀጥላል! የባርነት አገዛዝ ይወድቃል!
ድል ለኦሮሞ ህዝብ!
ብሄራዊ የኦሮሞ ወጣቶች ንቅናቄ
ነሀሴ 2013 አዲስ አበባ

1 comment:

  1. woyane esk mech endezik ychekunenal yhen worada mengist beandenet hunen masewoged alebin enji oromo amhara eytebabalu menakor mekom alebet dill 4 ETHIOPIA

    ReplyDelete