Wednesday, June 12, 2013

በዘር ላይ የተመሰረተ አገዛዝ ዛሬም ሆነ ነገ እልቂትን ይጋብዛል፤ እየታየ ያለውም እልቂት ነው።

June 11, 2013
ከታክሎ ተሾመ
ወያኔ / ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረበት ቀን ጀምሮ በአገርና በሕዝብ ላይ የሚደርሰው እልቂት ከፍተኛ ስለመሆኑ ነጋሪ የሚያስፈልግ አይመስለኝም።  የከፋፍለህ ግዛውን ይትባህል ለማስወገድም ሆነ እድሜውን ለማስቀጠል  በደጋፊና  በተቃዋሚ  መካከል ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ትግል ተካሂዷል።  በዘር ላይ የተመሰረተ አገዛዝ ዛሬም ሆነ  ነገ  እልቂትን ይጋብዛል፤ እየታየ ያለውም እልቂት ነው።The long youth march to freedom and dignity has begun in Ethiopia. It is beautiful.
ውጭም ሆነ አገር ውስጥ ድርጅት መሰረትን ያሉት  የትግል ስልታቸውም ሆነ ጥንካሬያቸው አንድነትን የተላበሰ ባለመሆኑ ከራሳቸው ፍጆታ ውጭ ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ  እየሰሩ አለመሆናቸው  በየጊዜው እየታየ ነው። በየጊዜው ሥማቸውንና መልካቸውን እየቀየሩ የሚወለዱ ድርጅቶችና ስቪክ ማኅበር ስብስቦች የሕዝቡ ትግል እንዲወሳሰብና አንድ ወጥ እንዳይሆን  አድርጐታል።
በቅርቡ ወጣቱን ማዕከል ያደረገ ሰማያዊ ፓርቲ የተባለው ወጣቱን በማደራጀት ሥር-ነቀል ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። በመሆኑም  ሰማያዊ ፓርቲ ከዚህ ቀደም እንደ አሸን ከፈሉ ድርጅቶች በተሻለ ሁኔታ የትግል ስልት የተከተለ ይመስላል።
ለዚህ ማስረጃ ግንቦት 2 ቀን 2013 አዲስ አበባ ውስጥ የጠራው ሰላማዊ ሕዝባዊ የተቃውሞ  ሰልፍ ወደፊት  ተስፋ ሰጭ ብቻ ሳይሆን የአንድነት ተምሳሌነቱን አሳይቷል ማለት ይቻላል። አገር ቤት እንዳገኘሁት መረጃ  ከሆነ የሰልፉ መንፈስ ብሄር፤ እስላም፤ ክርስቲያን ሳይይል የብዙዎችን የትግል ወኔ የቀሰቀሰና  ወደፊት  ትግሉ  ቀጣይ እንደሚሆን  ያመላከተና የለውጡን አይቀሬነት ተስፋ ሰጭ  እንደሆነ ነው።
በወጣቱ የሚጀመር ትግል ለውጤት እንደሚበቃ የካቲትን 1966 አብዮት ተመልሶ መቃኘት የሚቻል ይመስለኛል። ከታሪክ አመጣጥ መረዳት እንደሚቻለው ወጣቱ አዲስ ሃሳብ አፍላቂ  ብቻ ሳይሆን ከዘመኑ ፖለቲካ ጋር የመጓዝ  እድሉ  የተመቻቸ  ነው። ሕዝብ ከቀዩው እየተፈናቀለ፤ አገር  እየተደፈረች  መሆኑ  እውነት ነው።  ዛሬ ወጣቱ  የቆየች  አገሩን የመንከባከብ  ኃላፊነት  እንዳለበት ከተገነዘበበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብሎ መናገር ይቻላል።  እስከ ዛሬ የወያኔ  እድሜ  የተራዘመው  የወጣቱ አለመደራጀትና በጋራ አለመቆም፤ እድሜ ጠገብ  ፖለቲከኞች እኔ አውቃለሁ ባይነት፤ ጧት ተፈጥረው እንደጤዛ የሚበኑ፤ ስቪል ማኅበራት ነን የሚሉ ስብስቦች  ወጣቱን  ለማደራጀት ያላቸው ቁርጠኝነት አለመኖር  ነው።
ይሁን እንጅ ዛሬ ወጣቱ አገሩን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት በመረዳት የአያቶቹን ገድል ለመሥራት ቆርጦ የተነሳ መሆኑን ግንቦት 2 2013  ያደረገውን የተቃውሞ ሕዝባዊ ሰልፍ ልብ ይሏል። በመሆንም ወጣቱ ለዴሞክራሲ፤ ለመልካም አስተዳደር ለዘላቂ ነፃነት ቆርጦ የተነሳ ስለመሆኑ ማንነቱንና አይበገሬነቱን ለወያኔ ለመንግሥት አሳይቷል።
አገራችን ቀደምትና የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌ ብትሆንም ዴሞክራሲያዊ የሆነ አስተዳደር ባለመኖሩ የሕዝቦች ሰባዊ መብት የተገደበ  ነው። ከመሳፍንቱ፤ ከቀዳማዊ  ኃ/ሥላሴ እስከ ደርግ የግዛት  ዘመን ድረስ ለዴሞክራሲና ለመልካም አስተዳደር ሲባል አገር ውስጥ የተለያዩ የተቃውሞ  ትግሎች  ተካሂደዋል።  ነገር ግን  ደርግ ወድቆ ወያኔ ኢሕአዴግ  አዲስ አበባ  እንደገባ  አገር  ውስጥ  ይደረጉ የነበሩ የተቃውሞ ትግሎች ጠቅልለው ውጭ ወጥተዋል።
በውጭ የሚደረጉ የተቃውሞ ትግሎች ያለውጤት 22 ዓመታትን እያስቆጠሩ ይገኛሉ።  በእርስ በርስ መናቆር ምክንያት ያለው መንግሥት ያለተቃዋሚ እንዳሻው አገሪቱን የመዘወር እድል እንዳገኘ አይካድም። በ1966 የተካሄደው ሕዝባዊ አብዮት እንደ ዛሬው  ውጭ ሆነው በታገሉ ድርጅቶች አማካኝነት ሳይሆን የተገኘው ድል አገር ውስጥ በተደረገው ሕዝባዊ ተቃውሞ ነው።
የነፃነት ትግሉ ውጭ ሳይሆን አገር ቤት መሆን እንዳለበት በተለያዩ መጣጥፎቼ ገልጨ ነበር። ዛሬም አበክሬ የማምንበት አገር ቤት የሚደረገውን ትግል ነው። እንዳልኩትም በቅርቡ በሰማዊ ፓርቲ አማካኝነት የተደራጀው  ወጣት 22 ዓመት የተራዘመውን ትግል ከሕዝቡ ጋር ለማቀናጀት እየሞከረ ያለው አገር ቤት በመሆኑ ነው።
የውጩ ትግል ከዲፕሎማሲና ከገንዘብ እርዳታ ያለፈ ዘልቆ እንደማይሄድ ከአገሪቱም ሆነ ከዓለም ተጨባጭ ሁኔታ መረዳት ይቻላል። ስለዚህ በውጭ እንደ አሸን የፈሉ ድርጅቶች ዲሲና አውሮፓ ሆነው በአገር ቤት መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጡ እንዳልቻሉ ልብ ሊሉት ይገባል።  እውነታው ይህ ሆኖ እያለ አንዳንዶች በውጩ ትግል መኩራራትን ስለሚፈልጉ እውንቱን አምኖ ከመቀበል ይልቅ ለምን ተደፈርን በሚል አካኪ ዘራፍ  የሚሉ መኖራቸው ሃቅ ነው። ቢሆንም ከዚህ አጉል ዝና የሚወጡበትን አእምሮ እግዚአብሄር ይስጣቸው ከማለት ያለፈ ሌላ የምለው  አይኖርም።
የአገር ቤት ጠላት ሊንበረከክና ሥልጣን ለሕዝብ እንዲያስረክብ ከተፈለገ አገር  ውስጥ ሆኖ  እየታገሉ መስዋዕት መክፈል የሚያስፈልግ መሆኑ እርግጥ ነው። ወደፊት ትግሉ ቀጣይነት እንዲኖረውና ውጤት ለማምጣት ከተፈለገ የተለያዩ ፖለቲካ ድርጅቶች ከወጣቱ ጐን በመሰለፍ፤ በማደራጀት፤ የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ መስጠ ይጠበቅባቸዋል። በውጩ የሚኖረው ትውልደ ኢትዮጵያዊ/ ማኅበረሰብ  የአገር ቤቱ ትግል እንዲጐለብትና ለውጤት እንዲበቃ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ሁሉ ዛሬም ይበልጥ ተጠናክሮ ለአገር ቤቱ ትግል የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ማድረግ የሚጠበቅበት ይመስለኛል።
በመጨረሻም ሰሞኑን አባይን አስመልቶ የግብጽ መንግስት የሚያስተላልፋቸው ቱልቱላዎች እየተሰሙ ቢሆንም ለኢትዮጵያ አዲሲ  ነገር አይደለም። ስለዚህ ድርጅቶችም ሆኑ አገር ወዳድ ወገኖች  የመቻኮል ባሕሪ ሳያሳዩ ጉዳዩን በጥሞና ቢከታተሉት የሚሻል ይመስለኛል።  ነገር ግን  የምሁራን ጥናት በደንብ ሳይታከልበት በመጣደፍ በየድህረ-ገጾችም ሆነ በሬዲዮ ሊወጡ የሚችሉ መጣጥፎች ለትግሉም ሆነ ለአገራችን አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል እገምታለሁ። ይህን በተመለከተ ወደፊት የምለው ይኖረኛል።
ሁሉም ፊቱን ወደ ሀገሩ!

No comments:

Post a Comment