Monday, June 24, 2013

የተረጋጋ መንግስት እንዲቆም ከመቼውም ጊዜ በላይ የምትንቀሳቀስበት ወቅት ላይ መሆኗን ለማሳሰብ በነገው እለት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ አቶ ኦባንግ ሜቶ አስታወቁ።

“መኖር አለ፣ መሞት አለና ወደ ህሊናችን እንመለስ"
 June 25, 2013 03:10 am
hebrew-university
እስራኤል ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝብ ፍላጎት የሚመረጥ የተረጋጋ መንግስት እንዲቆም ከመቼውም ጊዜ በላይ የምትንቀሳቀስበት ወቅት ላይ መሆኗን ለማሳሰብ በነገው እለት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ አቶ ኦባንግ ሜቶ አስታወቁ። የሒብሩ ዩኒቨርስቲ ምሁራንና ማህበረሰብ ለአቶ ኦባንግ መልክት ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ንግግር ያደርጋሉ። በእስራኤል የሚኖሩ ስደተኛ ወገኖችን አስመልክቶ ቃል እንደተገባላቸውም አመልክተዋል። አቶ ሳሙኤል አለባቸው “መኖርና መሞት ስላለ ወደ ህሊናችን ልንመለስ ይገባል” አሉ።
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር የአሜሪካ እንደራሴ (ኮንግረንስማን) ክሪስ ስሚዝ በመሩት የምክክር ሸንጎ ላይ ንግግርና ማብራሪያ ካሰሙ በኋላ ወዲያውኑ በቀጥታ ወደ እስራኤል አምርተው ነበር። ለሁለት ጉዳዮች ወደ እስራኤል ያመሩት አቶ ኦባንግ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከእስራኤል ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በነገው ዕለት እንደሚመክሩ ለጎልጉል ሲያስታውቁ ስለሚናገሩበት ጉዳይም ፍንጭ ሰጥተዋል።
የሚያገኟቸውን ባለስልጣናት ሳይዘረዝሩ ስለ ምክክሩ የተናገሩት አቶ ኦባንግ “ዛሬ እስራኤል ኢትዮጵያ ላይ ህዝብ አምኖና መርጦ የሚያቆመው መንግስት እንዲመሰረት ከማንም በላይ መስራት እንዳለበት ወቅታዊ እውነቶችን በማንሳት አሳስባለሁ” ብለዋል። “እስራኤል” አሉ ጥቁሩ ሰው “እስራኤል አሁን ባለው የኢህአዴግ ተጨባጭ ሁኔታ ዝምታን አትመርጥም። ዝም ልበል ካለች የመጀመሪያዋ ተጎጂ አገር ትሆናለች። የምንግባባበት ወቅት ላይ ስለደረስን በማስረጃ እንነጋገራለን። ቀና ምላሽ እንጠብቃለን” በማለት አስረድተዋል፡፡hebrew-university
ምክክሩ እንዴት ሊዘጋጅ እንደቻለ ተጠይቀው “እቅድ ተይዞለት የተሰራ፣ ጊዜው ሲደርስ የተደረገ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። በሒብሩ ዩኒቨርስቲ የሕግ ፋኩልቲ ተገኝተው ለምሁራኖችና ተተኪ ፖለቲከኞችና የአዲሱ ትውልድ አባላቶች ንግግር እንደሚያቀርቡ አቶ ኦባንግ አስገንዝበዋል።
በዩኒቨርስቲው በሚያደርጉት ንግግር የሁሉንም ስሜት የሚነካ፣ ከራሳቸውና ከኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት አንጻር  የወደፊቱን በመተንበይ መንግስታቸው ኢትዮጵያ ላይ ያለውን አቋም በተረጋጋ መሰረት ላይ እንዲተክል የቀረበለትን ጥሪ እንዲቀበል ድጋፍ እንዲያደርጉ እንደሚጠይቁ ታውቋል።
በህንድ አገር ያቀረቡትን የትግል ጥሪ ተቀብለው ካራቱሪ ላይ ዘመቻ የጀመሩ “የመሃትማ ጋንዲ ፍሬዎች“  መገኘታቸውን አቶ ኦባንግ አስታውሰዋል። አሁንም በነጻ አውጪ ሰም አገር እየመራ ያለው ህወሃት እየፈጸመ ያለውን አሰቃቂ ተግባር ናዚ ከፈጸመው ተግባር ጋር እንዲመዝኑት በስፋት በመረጃ የተደገፈ ንግግር እንደሚያደርጉ ከገለጻቸው ለመረዳት ተችሏል። ስራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ዝርዝር ማብራሪያ እንደሚያቀርቡም አመልክተዋል።
አቶ ኦባንግ እስራኤል ስለሄዱበት ሌላው አንገብጋቢ ጉዳይ ሲያስረዱ፣ በመጀመሪያ የገለጹት “በመደራጀት ድል ይገኛል” በሚል መገረማቸውን በመግለጽ ነው። የተደረገላቸው አቀባበል ልባቸውን እንደነካው፣ የተሰራው ስራና የተገኘው ውጤት ደግሞ እንዳረካቸው የገለጹት የኢትዮጵያን እናድን አንድነት ማህበር በእስራኤል አመራር አባላትን በማመስገን ነው።
ከተቋቋመ አስር ወር ያልሞላው ማህበር በእስራኤል የኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ውስጥ እየሰሩ የዜጎችን መረጃ በማበላሸት፣ በማስተርጎም ስራ ወቅት መረጃ በማዛባት፣ በማሳሳትና ዓ.ም. በማሳከር የስደት ማመልከቻቸው እንዲበላሽ ሲያደርጉ የነበሩ የህወሃት አባላት ላይ ማስረጃ በማሰባሰብ ባካሄዱት ትግል ድል ተቀዳጅተዋል። የእስራኤል የኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት የቀረበለትን ማስረጃ ተመልክቶ የወያኔ አባላት የሆኑትን ሰራተኞች እንዲያስወግድ የተደረገው ጥረት አድካሚ እንደነበር ወ/ሮ ጽጌ ማርያም አቤ ለጎልጉል ተናግረዋል።israel israel 1
የማህበሩ የፋይናንስ ሃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ጽጌ ማሪያም አብረዋቸው የሚኖሩ የህወሃት ደጋፊዎች አገር ቤት እንደሚያደርጉት በማስፈራራት፣ በካሜራና በቪዲዮ በመቅረጽ ምስላችንን ለኤምባሲ በመስጠት፣ ወደ አገር ቤት የሚሄዱ እንደሚታሰሩ ወዘተ ተግባራት በመዘርዘር እንደሚያስፈራሩ አመልክተዋል። አገሩ ግን ኢትዮጵያ ባለመሆኑ ከጫጫታ እንደማያልፍ የተናገሩት ጽጌ ማርያም፣ “ስንሰባሰብ፤ ገንዘብ በመሰብሰብ አሸባሪዎችን ሊረዱ ነው። የአክራሪ ደጋፊዎች ናቸው፤ ወዘተ በሚል ለፖሊስ ይከሱናል። አሁን ግን ሁሉም ዝምታውን ሰብሮ ተባብሯል። እነሱም ሟምተዋል” ብለዋል።
የማህበሩ ጸሐፊ አቶ ጥላሁን በሻህ በበኩላቸው ከትናንት በስቲያ አቶ ኦባንግ በተገኙበት በተካሄደው ስብሰባ ላይ የተገኙት የህወሃት ሰዎች ስብሰባውን ለማወክ ጥረት አድርገው አንደነበር አመልክተዋል። አቶ ኦባንግን ጥያቄ እንጠይቃለን በማለት “አንተ ኢትዮጵያዊ አይደለህም” በማለት ለመዛለፍ እንደሞከሩም ተናግረዋል። ስብሰባው ሲጀመር አገር ቤት ህወሃት በበደኖ ያስፈጸመውን ጭፍጨፋ ያካተተ ቀንጭብ ምስል (ቪዲዮ ክሊፕ) መታየቱ ያናደዳቸው የህወሃት ደጋፊዎች “ይህ በኃይለሥላሴ አስተዳደር ወቅት የተፈጸመና እናንተ ቆርጣችሁ ቀጥላችሁ ያዘጋጃችሁት ነው” ማለታቸውን አቶ ጥላሁን ተናግረዋል።
በበደኖ እልቂት ቤተሰቦቿን ያጣች አንድ እህት ባጋጣሚ ስብሰባው ላይ ተገኝታ ስለነበር በሰማቸው ክህደት የተነሳ ራስዋን መቆጣጠር ተስኗት እያነባች መነሳቷን አቶ ጥላሁን ያስታውሳሉ። ጭፋጨፋውን ህወሃት በውክልና አስፈጽሞ ከኦነግ ጋር ሲጣላ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ጭፋጨፋው ከተከናወነ ከሁለት ዓመት በኋላ  ይፋ መሆኑንን “እኔ እማኝ ነኝ” በማለት መናገሯን አመልክተዋል።
በስብሰባው ላይ የተገኙ ወገኖች ቢበሳጩም ራሳቸውን በመቆጣጠርና አስቀድሞ በማህበሩ በተሰጠ መመሪያ መሰረት በሰላም የተፈለገለትን ዓላማ አሳክቶ መጠናቀቁን አቶ ጥላሁን አስረድተዋል። ከአቶ ጥላሁን በሻና ጽጌ ማርያም አቤ ጋር ያደረግነውን ቃለ መጠይቅ ሙሉ ሪፖርት በቀጣይ እናቀርባለን።
በስብሰባው ላይ “ኢትዮጵያዊ አይደለህም” የተባሉት አቶ ኦባንግ ምን ምላሽ እንደሰጡ ተጠይቀው “ምን ምላሽ እሰጠዋለሁ! ከመለስ የሚገኘው ትምህርት ውጤቱ ይህ ነው። የመለስ ፍሬዎች መጠናቸው እዚህ ድረስ ነው። እኔም ሆንኩ መላው ጋምቤላ ህዝብ ስለ ኢትዮጵያዊነታቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ ተሰምቶ አይታወቅም። ለአገራቸው ከመሞት ውጪ በባንዳነት ስማቸው ተነስቶም ሆነ ተከስሰው አያውቅም። እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ጭምር ነጻ ለመውጣት እንደምንሰራ ግን ነግሬያቸዋለሁ። እምነታችን ጥላቻ ስላልሆነ ላይገባቸው ይችላል። እኛ እንደዚህ ነን” ብለዋል።israel meeting
ጉባኤው በእስር ላይ ባሉት የሰላም ታጋይ አቶ አንዷለም አራጌ ስም የተሰየመ ሲሆን ማህበሩ ከጎናቸው መቆሙን ለመግለጽ ውስን አንድ ሺህ ዶላር ለቤተሰብ ለማድረስ መወሰኑን አስታውቋል። በስም የሚታወቁና የማይታወቁትን የህሊና እስረኞች ከልብ ለመደገፍና አለኝታነታቸውን ለመግለጽ ወደፊትም እንሰራለን ብለዋል። አዳዲስ መሪዎችንም እናበረታታለን ብለዋል።
የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ሳሙዔል አለባቸው ጉባኤውን ሲከፍቱ “መኖር አለ፤ መሞት አለ። በጉባኤው ላይ ገለልተኞች፣ ተቃዋሚዎችና አገር ቤት ያለውን አገዛዝ የሚደግፉ አሉ። ሁሉንም መሆን ይቻላል ግን በስርዓት እናድርገው” በማለት ተናግረዋል። አቶ ኦባንግ ከሚመሩት የጋራ ንቅናቄ ጋር በመሆን በጀመሩት ፕሮጀክት በስደት ከለላ ካገኙ በኋላ ወገኖቻቸውን የሚሰልሉትን በማጋለጥና በወንጀል ለማስቀጣት ከፍተኛ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል። ሰማያዊ ፓርቲ ለፈጸመው ታላቅ ተግባርና ህዝብ ለፈጸመው አኩሪ ገድል ክብር እንዳላቸው አመልክተዋል። ለጉባኤው መሳካት ትብብር ላደረጉላቸው ሚዲያዎች ምስጋና አቅርበዋል። የሽግግር ካውንስል ላደረገላቸው ተደጋጋሚ ትብብር ያላቸውን አድናቆት ሰንዝረዋል። የአቶ ኦባንግ በመካከላቸው መገኘት ታላቅ ክብር እንደተሰማቸው አስታውቀዋል።

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

No comments:

Post a Comment