Wednesday, June 5, 2013

ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስተያየት ሲሰጡ “ኮሚሽኑ ጥርስ እንዳለው አሳይቷል” ብለው ነበር፡፡

እንግዲህ ለኤልፓና ለቴሌኮም ስንል ጫካ አንገባ?

እናንተ … በገዢው ፓርቲ አባላት የተሞላው ፓርላማ ከመቼ ወዲህ ነው እንዲህ ደፋር የሆነው? (ሰርጐ ገብ ቡድን ገባ እንዴ?) የፓርላማ አባላቱ ስንቱን ቱባ ቱባ የመንግስት ባለስልጣን መሰላችሁ ሲያፋጥጡ የሰነበቱት! አንድ የፓርላማ አባል ስለ ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስተያየት ሲሰጡ “ኮሚሽኑ ጥርስ እንዳለው አሳይቷል” ብለው ነበር፡፡ እኔ ደግሞ “ፓርላማው ጥርስ እንዳለው አስመስከረ!” ብያለሁ – ለራሴ፡፡ ከምሬ ነው … እንደ ድሮ አጨብጭቦና እጅ አውጥቶ መለያየት ቀረ እኮ! (እንኳን ፈጣሪ ገላገለን!) ባለፈው ጊዜ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ ደብረፅዮን ገ/ ሚካኤል ለፓርላማ ሪፖርታቸዉን ካቀረቡ በኋላ ከግራና ከቀኝ እንዴት በጥያቄ እንዳፋጠጧቸው አልነግራችሁም፡፡ አንዱ አባል፤ በተወከለበት አካባቢ የኔትዎርክ መቆራረጥ መኖሩን ሲገልፅ፤ ሌላኛው እሱ በተወከለበት አካባቢ ግን ከእነአካቴው ሞባይል እንደማይሰራ ተናገረ፡፡ (ምን ያድርግ ሃቅ ነዋ!) ሃላፊው ታዲያ ምናቸው ሞኝ ነው፡፡ ጥያቄው እንኳንስ በእሳቸው የስልጣን ዘመን በተተኪው ትውልድም መልስ የሚያገኝ ስላልመሰላቸው ስለ ቴሌኮም ማውራቱን ትተው ስለ አገሪቱ ዕድገት መስበክ ጀመሩ፡፡ (ክሊሼ እኮ ነው!) “ምስቅልቅሎች ይኖራሉ፤ ግን የዕድገት ምስቅልቅሎች ናቸው!” አሉን ሚኒስትሩ፡፡ (አዲስ ነገር ግን አልነገሩንም!) እኔ ግን አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ከሁለቱ “ጉልቤ” የመንግስት ድርጅቶች የሚገላግለን እናገኝ ይሆን? እንግዲህ ለኤልፓና ለቴሌኮም ስንል ጫካ አንገባ? እውነቴን ነው … ኤልፓ የዕለት ተዕለት ኑሮአችንን አመሰቃቀለው እኮ! እሱም እንደባልደረባው “ምስቅልቅሉ የዕድገት ምስቅልቅል ነው!” እንዳይለን እሰጋለሁ፡፡ (ተመሳሳይ ላባ ያላቸው ወፎች አብረው ይበራሉ ይባል የለ!) ይታያችሁ … በአንድ ከሰዓት በኋላ ብቻ ሦስቴ መብራት እየጠፋብን ነው፡፡ ቴሌኮምም ቢሆን እኮ ብሶበታል፡፡ ቅዳሜ ማታ እዚሁ አዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ ለሚኖር ጓደኛዬ የላክሁት ማሴጅ መቼ ቢደርስ ጥሩ ነው? ማክሰኞ ማታ – በአራተኛው ቀን ማለት ነው፡፡ ለዚህ ለዚህማ እኔው ራሴ እቤቱ ሄጄ መልዕክቱን አደርስለት ነበር (ከመንገድ ትራፊክ የቴሌ ትራፊክ ባሰ እኮ!)

No comments:

Post a Comment