Monday, June 24, 2013

ዛሬ ጠዋት ቤቲ የተባለችው ኢትዮጵያዊት ወጣት ከደቡብ አፍሪካው ቢግ ብራዘር አፍሪካ ውድድር መባረሯ ሌላ “ሰበር ዜና” ሆኗል –


ኢትዮጵያዊት ወጣት ከደቡብ አፍሪካው ቢግ ብራዘር አፍሪካ ውድድር መባረሯ ሌላ “ሰበር ዜና” ሆኗል – ፌስ ቡክ ላይ !!
በራሱ ልክ በቪዲዮ የታየው ድርጊቷ የቀሰቀሰውን የብዕር ጦር ያህል ቀስቅሷል። አብዛኛው አስተያየትም “እሰይ .. እንኳን ተባረረች ፣ አሁን የት እንደምትገባ እናያለን” የሚል ከመምሰሉም ሌላ አንዳንዶች ዱላ ሁሉ ይዘው ኤርፖርት የሚጠብቋት ነው የሚመስለው።
ስሜታዊነት ላይ ጭካኔ ሲጨመርበት መጨረሻው አስከፊ ነው። አንዳንዴ ጨካኝ ሰው ከስሜታዊነት ከወጣ ጨካኝነቱን ሊገታው ይችላል። ስሜታዊ ሰውም በስሜት ቢገፋፋም የሚጨክንበት ወኔ ላይኖረው ይችላል። ሁለቱ ሲደባለቁ ግን አያድርስ ነው .. አሁን ፌስ ቡክ ላይ የታዘብኩት ይህንኑ ነው።
ልጅቷ ተሳስታለች። 24 ሰአት ካሜራ ላይዋ ላይ እንዳለ እያወቀች ይህን በማድረጓ በጣም በጣም ተሳስታለች። ለዚህ ስህተቷ ግን ካልተገደለች፣ ካልተሰቀለች የምንል ካለን ደግሞ ከሷ የበለጠ ተሳስተናል። ለመሆኑ በሰሜትም ይሁን በሌላ ተገፋፍቶ ስህተት የሰራ ሰው እንዲህ እንዲረገም፣ እንዲወገዝና፣ እንትን የነካው እንጨት እንዲሆን በሰማይ የትኛው ሃይማኖት ፣ በምድርስ የትኛው ህግ ይፈቅዳል? የአንዳንዱ ሰው ፍርድ እዚህ ፌስ ቡክ ላይ ሲነበብ .. ያ ሰው እንኳን እግዚአብሔር አልሆነ ያሰኛል። በዚህ ጭካኔው እግዜር ቢሆን ኖሮ ዓለም ሁሉ በጠፋ ነበር። ምክንያቱም ቤቲ የተሳሳተችውን ስህተት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ያልተሳሳተ የለምና !!
ቤቲ በቤት ውስጥ ወሲብ ስትፈጽም በአደባባይ ታየች። ትልቅ ስህተት! .. ግን እኛስ በአደባባይ የሰረቅን የለንምን? በአደባባይ ሰው የገደለን፣ በአደባባይ ሰው ያዋረድን፣ በአደባባይ ሰው በተንኮል ጩቤ የምንወጋ የለምን? በአገራችን ከታች በየግሮሰሪው፣ ከላይ በየትላልቁ ሆቴል ራሳቸውን “ለገበያ” ያቀረቡ እህቶቻችን የሉምን? እያየናቸው አንዱ ይዟቸው ክፍል ሲገባ እኮ ምን ሊያደርጉ እንደሆነ እናውቃለን። የሌላውን ጥፋት እንዲህ ስንረባረብበት በርግጥ እኛ ንጹህ ሆነን ነው ወይስ ከሷ ጥፋት፣ የኛ ጥፋት ይሻላል ብለን ነው?
ብዙዎች “አዋረደችን” ሲሉ አንብቤያለሁ – ኽረ ባካችሁ!! የተዋረደ ሰው እኮ አንገቱን ቀና ማድረግ ፣ በሙሉ አይኑ ሌላውን ማየት፣ በሙሉ አፉ ሌላውን መናገር አይችልም። እስቲ እኛ የቤቲ ድርጊት ከተሰማ ጀምሮ ህይወታችንን እንይ ? አንዋሽ! እውነት ተዋርደናል? ምን ሆንን? ምን የተቀነሰብን ነገር አለ? በሷ የተነሳ ምን ጎደለብን? ምናልባት ቤተሰቦቿ አንዳንድ ቦታ ሲሄዱ መጠቋቆሚያ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል፣ እነሱ አቀርቅረው ሊሆን ይችላል.. .. “አዋረደችን” ቢሉ በነሱ ያምራል! .. እስቲ እኛ ምን ሆንን? ክርስቲያንም እንሁን እስላም .. እንድንዋሽ አልተፈቀደልንም !!
ቤቲ አጥፍታለች። ማንም አይክድም። የውድድሩ አዘጋጆች – ዛሬ ለወጣ አንድ የአዲስ አበባ ጋዜጣ እንደተናገሩት .. ማንም ሰው የሚወዳደረው በግሉ እንጂ ፣ አገሩን ወክሎ አይደለም። ይህ የአወዳዳሪዎቹ ህግ ነው። ተወዳዳሪዎቹ ቢወድቁም ቢነሱም፣ ቢያጠፉም ቢያለሙም፣ ቢያለቅሱም ቢስቁም፣ ቢደሰቱም ቢያዝኑም፣ ጥሩ ቢሰሩም ጥሩ ባይሰሩም የግላቸው እንጂ የአገር ጉዳይ አይደለም። ቤቲ በግሏ አመልክታ ፣ በግሏ ተመርጣ ሄደች። ያረገችውን አረገች .. ጥሩ ሰርታ ብታሸንፍ ገንዘቡ ለግሏ ምናልባትም ለቤተሰቧ ነው .. ሄዳም መጥፎ ብትሰራና ብትከስር በግሏ ቀጥሎም ኪሳራው ለቤተሰቧ ነው።
ትኬት ገዝቶ፣ ልብስ ገዝቶ፣ ወጪዋን ችሎ የላካት ቤተሰቧ ነው። እኛ ምኑም ውስጥ የለንበትም .. አሁን ጥፋት ሲገኝባት እኛን እዚያ ውስጥ ለምን እንከታለን? ከዚህ በፊት አንድ ጸሃፊ እንዳሉት የአገር ጉዳይ ማድረጉን ትተን ….፣ ድርጊቱ በራሱ ትክክል ነው አይደለም በሚለው ላይ በሰለጠነ መንገድ እንወያይ። በውግዘት ማንንም አናስተምርም – በውይይት ግን ለመማር የሚፈልግን ሁሉ እናስተምራለን።
ማንም ሰው ከሰራው ስህተት በላይ አይቀጣም። ይህ ሁሉ የፌስ ቡክ ውርጅብኝ በቂ ነው፣ እሷም በድጋሚ .. ሌላም ሰው ወደፊት እንዲህ ዓይነት ነገር ስህተት የሚፈጽም አይመስለኝም። አሁን አገሯ ስትመለስ ይኸው የስድብ ውርጅብኝ የሚቀጥል ከሆነ በርግጥ የመጨረሻ ጨካኞች መሆናችንን እንረዳ። እንኳን ራሷን የበደለችን ልጅ ቀርቶ እኛን እንኳን የበደሉን ቢኖሩ ፣ መጽሃፉ የሚለው “የበደላችሁን ይቅር በሉ” ነው።
አዎ ቤቲ ተሳሳተች። በዓለማችን ላይ የሷን ሃያ እጥፍ ስህተት የሰሩ ሰዎች፣ ለሰሩት ስህተት ይቅርታ ጠይቀውም ሆነ ይቅር ተብላችኋል ሌላ ጊዜ እንዲህ ባታድርጉ ጥሩ ነው .. ተብለው ህይወት፣ ኑሮ ቀጥሏል ። ከነ ስህተቷ ፣ ከነ ጥፋቷ፣ ከነ ድርጊቷ .. ለቤቲ ሊታዘንላት ይገባል። እስከዛሬ የተጻፈባትን የምታየው፣ የተባለችውን የምትሰማው ከዛሬ በኋላ ነው። ምን እንደሚሰማት መገመት አያዳግትም። ከዚህ በላይ ምን ትሁን?
ወደፊት እንዴት በጥሩ መንገድ ተጉዛ የተሻለ ቦታ እንደምትደርስ ማሳየት እንጂ፣ ከግራና ከቀኝ እያጣደፍን ወደ ገደል የምንገፋት ልንሆን አይገባም። በተለይ “ሚዲያ” ያላቸው፣ የአዲስ አበባ ኤፍ ኤሞችም ሆነ ጋዜጦች የበለጠ ሃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል።

1 comment: