Saturday, October 5, 2013

The late prime minister of Ethiopia "funny" response to Homosexuals የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የግብረሰዶም አራማጆች “የመደራጀት መብታችን ይከበር” የሰጡት አስቂኝ ምላሽ


Written by  ወልደመድህን ብርሃነመስቀል
በቅርቡ አንድ የመዲናችን የግል ኮሌጅ በሥራ አመራር የትምህርት ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ሲያስመርቅ፤ ግብረ ሰዶማዊነት በአገራችን እያስከተለ ስላለው አደጋ የሚያስቃኝ በጥናት የተደገፈ ጽሑፍ ቀርቦ ነበር፡፡ ፅሁፍ አቅራቢው፤ የግብረሰዶም አራማጆች ለኢትዮጵያ መንግስት “የመደራጀት መብታችን ይከበር” በሚል ያቀረቡትን ጥያቄና የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር የሰጡት ምላሽ በሚል ያቀረቡት ቀልድ ለአንባቢያን የሚያስተላልፈው ቁም ነገር አያጣምና ልጥቀሰው። ጠ/ሚኒስትሩ የመብት ጠያቂዎቹን ተወካዮች አስጠርተው እንዲህ አሏቸው፡-
“እንድትደራጁ ከመፍቀዳችን በፊት ጥያቄያችሁ ከሕግ፣ ከሞራል፣ ከባህል፣ ከሥነ ምግባር…አንፃር ተቀባይነት ይኖረው አይኖረው እንደሆነ ማጣራት አለብን፡፡ ይሄን ለማጣራት ደግሞ የእናንተም ትብብር ያስፈልገናል፡፡ የመጀመርያው ተግባራችሁ የሚሆነው የድጋፍ መጠየቂያ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ነው፡፡ የሰልፉ መነሻ መሐል መርካቶ ይሆናል፡፡ ድምፃችሁን እያሰማችሁ፣ መፈክሮቻችሁን በጽሑፍ ይዛችሁ በመጀመሪያ የምታልፉት በራጉኤል ቤተክርስቲያን በኩል ይሆናል፡፡ በመቀጠል አንዋር መስጊድን ታቋርጣላችሁ፡፡ ከዚያ ወደ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ትዘልቃላችሁ፡፡ በአፍንጮ በር በኩል በ6 ኪሎ ዩኒቨርስቲና የሰማዕታት ሐውልትን ካለፋችሁ በኋላ፣ በ4 ኪሎ ዩኒቨርስቲ በኩል የነፃነት ሐውልትን አቋርጣችሁ፣ በሁለቱ ቤተመንግስቶች መሐል በመጓዝ መስቀል አደባባይ መድረስ ከቻላችሁ፣ የመደራጀት ጥያቄያችሁ ምላሽ ያገኝ ይሆናል”
ቀልድ ነው ተብሎ የተነገረው የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ምላሽ በውስጡ ለውይይት የሚጋብዙ ሃሳቦችን ይዟል፡፡ በአገራችን ግብረሰዶም እንዳሁኑ የተስፋፋ አይሁን እንጂ ከግማሽ ክ/ዘመን በፊት ብቅ ብቅ ማለት መጀመሩን የሚጠቁሙ የአማርኛ ልቦለድ ሥራዎች አሉ፡፡
የአማርኛ አጭር ልቦለድ ጀማሪ ተብለው ከሚጠቀሱት ደራስያን አንዱ የሆነው ታደሰ ሊበን በ1949 ዓ.ም “መስከረም”፣ በ1952 ዓ.ም “ሌላው መንገድ” የተሰኙ ሁለት የአጫጭር ልቦለድ መድበሎች ያሳተመ ሲሆን ደራሲው በኢትዮጵያ ውስጥ የግብረ ሰዶማውያንን ሁኔታ የሚያመለክት ጭብጥ በማንሳት ፈር ቀዳጅ እንደሆነ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በ2000 ዓ.ም ያሳተመው ደራሲያንን የሚያስተዋውቅ አውደ እለት (አጀንዳ) ይጠቁማል፡፡
“ሌላው መንገድ” ስድስት አጫጭር ልቦለድ ታሪኮችን ያካተተ ሲሆን፤ በመጽሐፉ ከገጽ 55 እከ 74 የሚዘልቀው ታሪክ ዋና ገፀባሕሪ፣ ብርሃኑ የሚባል የ22 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ታሪኩን “እኔ” እያለ በአንደኛ መደብ የሚተርከው ገፀባህሪ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞች ቼክ ክፍል ውስጥ ነው የሚሰራው፡፡
ከቁመቴ ማጠር በስተቀር ደም ግባቴ በጣም ቆንጆ ነበር፡፡ ይህንንም በየዕለቱ የተለያዩ ሰዎች በተለይ ሴቶች የሚያረጋግጡልኝ እውነት ነበር የሚለው ብርሃኑ፤ መልከመልካምነቱን ሲገልፅ፤ “ቀጥ ያለ አፍንጫ፣ ትክክል የሆኑና ንጣታቸው በረዶ የመሰሉ ጥርሶች፣ እጅግም ያልወፈሩ እጅግ በጣም ያልሳሱ መካከለኛ ከንፈሮች፣ ቅንድቦቼ የተኳሉና የተቀነደቡ የሚመስሉ፣ ፀጉሬ፣ ግንባሬ፣ ጉንጮቼ፣ ጆሮዎቼ፣ እምንም ዘንድ ያልተዛቡ፤ በጠቅላላው የሰራኝን እጅ ረቂቅነት አጉልተው የሚያወሱ ነበሩ። ለሴቶችም የማይችሉት ፈተና ነበርኩ…ሲያዩኝ መተርከክ፣ ማተኮር፣ መገላመጥ ግዴታቸው ነበር፡፡”
ጥሩ መልበስ ውበቴን ስለሚያጐላው አልባሌ ነገር መልበስ አዘወትር ነበር የሚለው ዋና ገፀ ባሕሪ፤ በ1942 ዓ.ም እለተ ሰኞ የገጠመውን ይተርካል። በቼክ ክፍል ለመገልገል የመጡ አንድ ደንበኛው ካስተናገዳቸው በኋላ፣ ለአንድ ጉዳይ እንደሚፈልጉት በመግለፅ እቤታቸው እንዲመጣ ይቀጥሩታል፡፡
ሰውየው በትልቅ ቪላ ቤት ውስጥ ነዋሪ ናቸው፡፡ የግቢ ጠባቂ ዘበኛ፣ የእልፍኝ አስከልካይ ወንድና ሴት አገልጋዮችም አሏቸው፡፡ መኖሪያ ቤታቸው ዘመናዊና በውድ ዕቃዎች የተሞላ ነው። ቀጠሮ የሰጡት ወጣት ሲመጣ፣ ውስኪ እየጋበዙ ያጫውቱት ጀመር። የእጅ ሰዓት ከኤደን (የመን) እንደሚያመጡለት ቃል ገቡለት፡፡ ሁለት ሙሉ ልብስ የሚያሰፋበትን ጨርቅ በአቅራቢያው ካለው ሱቅ እንዲወስድም ነገሩት፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ጉዱ የመጣው፡፡ “ሁሉ ሰው፣ መቼም ተፈጥሮ ሆኖ አንዳንድ አመል አለው” በማለት ፍላጐታቸውን በግልጽ ነገሩት፡፡
በቀረበለት ጥያቄ ግራ የተጋባው ብርሃኑ፤ “ምንም አልመለስኩለትም፤ ብቻ… አመዴ ቡን ብሎ ኩምሽሽ አልኩኝ” ይላል - የገጠመውን ሲተርክ። ከዚያም በብልሃት ከሰውየው ወጥመድ አምልጦ መውጣቱን ይተርካል፡፡
ነገሩ ከተከሰተ ከስድስት ወር በኋላም ሰውየው ተመሳሳይ ጥያቄ ለጓደኛው እንዳቀረቡለት ነግሮን ነው ታሪኩ የሚጠናቀቀው፡፡
“እሳት በሌለበት ጭስ አይኖርም” እንደሚባለው፣ በሕብረተሰቡ ውስጥ ካየውና ከሰማው በመነሳት ከ50 ዓመት በፊት በአገራችን ግብረሰዶም ማቆጥቆጥ መጀመሩን በድርሰት ሥራው የጠቆመን ሌላኛው ደራሲ ኃይለሥላሴ ደስታ ነው፡፡ “የሚያቃጥል ፍቅር” በሚል ርዕስ በ1963 ዓ.ም ባሳተመው ለቦለድ መጽሐፉ፤ የዚህ ችግር ተጠቂ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ በጨረፍታ ያሳየናል፡፡
የመጽሐፉ ዋና ገፀ ባሕሪ ከትላልቅ ቤተሰቦች የተወለደች፣ ትምህርቷን ባሕር ማዶ ጭምር የተከታተለችና በህክምና ሙያ የሰራች ሲሆን የሕይወት ውጣ ውረድና መከራው በዝቶባት ከሐረር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ በውቤ በረሃ የሴተኛ አዳሪነት ህይወቷ ከገጠሟት ያልተለመዱ ድርጊቶች አንዱን ትነግረናለች፡፡
የድርጊቱ ፈፃሚ በአየር መንገድ የሚሰራ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ የግሉ ቪላ ቤትና የቤት አገልጋይ ሠራተኞች አሉት፡፡ ሴተኛ አዳሪዋን ከቡና ቤት አግኝቷት ነው ወደ ቤቱ የሚወስዳት፡፡ “ልብስሽን ሙሉ ለሙሉ አውልቀሽ ካልተኛሽ” በሚል ነው ያልተለመዱ ጥያቄዎችን ለዋና ገፀ ባሕሪዋ ማቅረብ የሚጀምረው፡፡
“ውስጥ ልብሴን እንኳን ልልበስ” ስትለው ሰውየው አይፈቀድላትም፡፡ “መጨረሻ ከሰው ቤት ነበርኩና ሳልወድ በግድ አወላልቄ ተኛሁ፡፡ ጥቂት ጊዜ እንደቆየን መብራቱ ጠፋና ‘ዙሪ’ አለኝ፡፡ በለሰለሰ አንደበት ‘ወዴት’ አልኩት፡፡ ‘ይህ ለሊት የእኔ ሥልጣን ነውና እንዳስፈለገኝ ላዝሽና ልጠቀምብሽ እችላለሁ’ አለ” እያለች የደረሰባትን ያልተለመደ እንግልትና በደል ትተርካለች፡፡
የአገር ውስጥ ገጠመኙ አይሁን እንጂ ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔርም የግብረ ሰዶማዊያን ባህሪና አቀራረብ ምን እንደሚመስል “ማስታወሻ” በሚል ርዕስ በደራሲ ዘነበ ወላ በተዘጋጀው መጽሐፍ ውስጥ አንድ ገጠመኙን በመጥቀስ ይነግረናል፡፡
ጉዳዩ በእንግሊዝ ለንደን የተከሰተ ነው። ስብሐት በወቅቱ ተማሪ ነው፡፡
ሃና የተባለች ፍቅረኛውን የሚያስተናግድበት እርካሽ የሆቴል መኝታ በመከራ ያገኛል፡፡ የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ ለስብሐት “እዚህ ሴት ይዞ መምጣት ክልክል ነው፡፡ ግን እኔ ሳላይህ ይዘህ መግባት ትችላለህ፡፡ እኔም እያየሁ አላይህም” እንዳለው ስብሃት ይነግረናል፡፡
“ሃና መጣችና ገና ከሩቅ እንዳየችው በእንግሊዝኛ ‘ያንን ሰው አልወደውም’ አለችኝ፤ ‘ምን ማለትሽ ነው’ አልኳት፡፡ ‘አንተን የሚያይበት አስተያየት ደስ አላለኝም’ አለችኝ፡፡ ‘ዝም ብለሽ ነው’ ብዬአት ባለውለታችን መሆኑን እያጫወትኳት ገባን፡፡ ተመላልሳ እዛ ሆቴል ትመጣለች፡፡ ሰውየውም አይቶ እንዳላየ ያሳልፈናል፡፡”
አንድ ቀን ሚስተር ዋትሰን ‘እንዲያው ፈገግታህ በጣም ደስ ይለኛል’ አለኝ፡፡
የሃና ዕይታ ተገለፀልኝ። የፍቅር ጨዋታን ከተቃራኒ ፆታ ጋር ሳይሆን ከተመሳሳዩ ጋር መደሰት የሚፈልግ ሰው ነው፡፡ በጨዋ ቋንቋ ልተባበረው እንደማልችል ነገርኩትና በሁኔታው እያዘንኩ ተለያየን፡፡”
በሦስቱ መፃሕፍት ውስጥ የቀረቡት መረጃዎች ሁለት ቁም ነገሮችን ያስጨብጡናል፡፡ አንደኛው አሁን ለአገራችን አደጋ ሆኖ የቀረበው ግብረ ሰዶማዊነት፤ መነሻው የባሕር ማዶ ልማድ መሆኑን ነው፡፡ ደራሲ ታደሰ ሊበን፤ በልቦለድ ስራው የዚህ ሰለባ መሆኑን የሚያሳየን ገፀባህሪ፤ ለንግድ ሥራ ወደ ውጭ አገራት የሚመላለስ ኢትዮጵያዊ ነጋዴ ነው፡፡
ደራሲ ኃይለሥላሴ ደስታም የቀረፀው ገፀባህሪ፤ ለውጭ የባህል ተጽእኖ በቀላሉ ሊጋለጥ የሚችል የአየር መንገድ ሠራተኛ ነው፡፡ ስብሐትና ፍቅረኛው ተግባሩን የተፀየፉት ሰውም እንዲሁ የውጭ አገር ዜጋ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን፤ ለትምህርት፣ ለሥራና ለተለያዩ ጉዳዮች ወደተለያዩ የዓለም አገራት ሲመላለሱ ብዙ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ወደ አገራቸው የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ይዘዋቸው የሚመጡት አዳዲስ አፈንጋጭ ልማዶች ሕብረተሰቡ ሲፈቅድ ይስፋፋሉ። በተቃራኒው የማደግና የመስፋፋት ዕድል ያጡ ደግሞ አሉ፡፡
ከእነዚህም አንዱ ግብረ ሰዶም ነው፡፡ አሁን ግን ይሄ አፈንጋጭ ልማድ በአገራችን እየተስፋፋ መምጣቱና ለማህበረሰቡ አደጋ ሆኖ መጋረጡ እየተነገረ ነው፡፡
የቀድሞ ትውልድ የተቆጣጠረውን የማህበረሰብ ችግርና አደጋ፤ የአሁኑ ለምን መቆጣጠርና መከላከል አቃተው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ለውይይትም ይጋብዛል። ውይይቱ ከውጭ አገራት የሚገቡ ሌሎች መሰል አፈንጋጭ ልማዶችን ለመከላከል የሚያስችል ሥነ ልቦናዊ ዝግጅት የሚሰጠን ይመስለኛል፡፡
AddisAdmassNews.com

No comments:

Post a Comment