Saturday, September 27, 2014

ወያኔ በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው በደል በቃ ብለን አሁኑኑ ለትግል እንነሳ!

በዳንኤል በቀለ* (ከኖርዌ)
ወያኔ የጥቂት ባለሃብቶችን እና የታማኝ ካድሬዎችን ጥቅም ብቻ ለማስከበር ብሎም የስልጣን ላይ ቆይታቸውን ለማርዘም የዋሁን እና ምስኪኑን የኦሮሞ ገበሬ ያለምንም ተተኪ ቦታ እና ያለምንም የካሳ ክፍያ ከመሬቱ ላይ እያፈናቀሉ ለረሃብ እና ለስደት እንዲሁም ኩሩው የኦሮሞ ህዝብ በታሪኩ አይቶት ለማያውቀው ለልመናና ለተለያዩ ችግሮች እየዳረጉት ይገኛሉ። በኦሮሞነታቸው በሚያነሱት የነፃነት ጥያቄ በወያኔ እስር ቤት በግፍ የታጎሩ የኦሮሞ ልጆች ቁጥራቸው እጅግ ከፍተኛ ነው – በብዙ ሺዎች እንደሚቆጠር ይታወቃል። በየቦታው ባሉ የወያኔ እስር ቤቶች ዋናው የመግባቢያ ቋንቋ ኦሮሚኛ እስከ መሆን የደረሰበት ሁኔታ እንዳለ ብዙ ጥናት ያደረጉ የአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አመላክተዋል። የአንድ ብሄር ዝርያዎች ብቻ በስልጣን ላይ መቀመጥና መግዛት የሌሎች ብሄሮች በህይወትና በሞት መሃል ተገዝቶ መኖር የኦሮሞ ህዝቦች ደግሞ እያጣጣሩ እንኴን እንዳይኖሩ በሚደረግበትና የወያኔ የእስር ቤት ቋንቌ ኦሮምኛ በሆነበት በዚህ ወቅት ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር አለን ብለው በውሸት ህዝብንና አለምን ለማታለል መሞከር ገዢው ወያኔ በፍፁም ዲሞክራሲን በስም እንጂ በተግባር የማያውቅ መሆኑን ለተመለከተው ሰው ሁሉ ግልፅ ነው። በየትኛው ዲሞክራሲ በሰፈነበት አገር ነው አንድ መንግስት ራሴን እችላለሁ፤ አስተዳድራለሁ፤ በቅኝ ግዛት መተዳደር በቃኝ ያለን ህዝብ እኔ አውቅልሃለው በማለት በግፍ የሚገዛው። በፍጹም! ይህ አምባገነናዊ የቀኝ ግዛት የወያኔ መንግስት ለኦሮሞ ህዝብ ያለውን ንቀት ያሳያል።
በርግጥ የኦሮሞ ህዝብ ባለፉት የኢትዮጵያ አምባገነን ነገስታት ጭምር ያለማቋረጠ እጅግ አስከፊ ጭቆናና የመብት ረገጣ እንዲሁም የተለያዩ ኢ-ዲሞክራሳዊ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸሙበት ተጉዞ ዛሬ ላይ ደርሷል። ባለፉት ረጅም ዘመናት በፈጣሪ የተሰጠን ስልጣን ነው እያሉ የኦሮሞ ልጆችን በግፍ እንደ በግ ሲያርዱ፣ ሲያስሩ፣ ሲገርፉና ከሰው በታች እንደ ቆሻሻ ተመልክተው ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ማንነታችንን ሲያንቌሽሹ በነበሩት ሰው በላ አፄዎች ተገዝተናል። ያ ሁሉ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆች ላይ ያደረሱት የዘር ማጥፋት ወንጀል ጭራሽ እንደ ፅድቅና ቅድስና ተቆጥሮላቸው የአረመኔዎቹ ነገስታት ሙት አመት ሲከበር እያየን እንዳልሰማንና እንዳላየን በዝምታ እኛ ኦሮሞች መመልከታችን ሁሌም የሚከነክነኝ ጉዳይ ነው። ይባስ ብሎ የብዙ ሺ የኦሮሞ ልጆችን ደም ሲያፈስ የነበረው የወያኔው ክፉ መሪ ሟቹ መለስ ዜናዊ ዛሬም እንደ ቀደምት ነገስታቶች ሁሉ ትልቅ ጀብዱ እንደሰራ ታላቅ መሪ ነበር ተብሎ ሲወደስ ሳይ ኢትዮጵያውያን ነን የሚሉት ቀኝ ገዥዎቻችን ክፉነታቸው ገደብ እንደሌለው ያሳየኛል። ይሄንን ሁሉ ግፍ ከኦሮሞ ህዝብ የዋህነት ጋር ሳነፃፅረው በጣም ያሳዝነኛል። ወገኖቼ ልናውቀው እና በጥሞና ልናስተውለው የሚገባን ጉዳይ ግን የዋህነታችን አልጠቀመንም በጣም ጐድቶናል፣ እጅግም በድሎናል።
ጨካኙ የወያኔ መንግስት በኛ በኦሮሞች ዘንድ እያደረሰ ያለውን ግድያ፤ እስርና ማሰደድ አጠናክሮ ቀጥሏል። በቅርቡ እንኳ በፊንፊኔ አጎራባች የኦሮሚያ ከተሞች ላይ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆችን ለማፈናቀል በማሰብ አዲስ ማስተር ፕላን ነደፍኩኝ በማለት ለማታለል ያደረገውን ሙከራን የተቃወሙ የኦሮሞ ወጣቶችና ተማሪዎች ስለምን ተቃወማችሁኝ በሚል ትዕቢት ተወጥሮ ወገኖቻችንን በጥይት አስደብድቦ አሰገደለ። በአምቦ፤ ወለጋ፤ መዳዎላቡና ሃሮማያ ኦሮሞዎች በየመንገዱ በወያኔ ፖሊሶች ሲገደሉ ተመልክተናል፤ የሟቾቹን ስም ለማጉደፍም ከኦነግ ጋር በመያያዝ እንዲሁም የተለያዩ ተቀጽላ ስሞችን እየሰጠ ሊደርስበት ከሚችለው የዘር ማጥፋት ውንጀል ለመሸሽ ሲውተረተር አይተናል። ግን ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ የኛ የኦሮሞዎች ዝምታ ለምንድን ይሆን? ያደረግናቸው የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችስ ከደረሰብን በደል ጋር ተመጣጣኝ ናቸውን? ወገኖቻችን በአደባባይ ሲገደሉ እያየን ምንስ እየሰራን እንዳለ በፍጹም ሊገባኝ አልቻለም።
አምባገነኑ የወያኔ ስርአት ርህራሄ ከሌለው እስራቱም አልፎ የኦሮሞን ልጆች እያደነ ይገኛል፡፡ ወያኔ ካድሬዎቹን ተጠቅሞ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚያደርገውን ኢሰብአዊ ድርጊት ኦሮሞዎች ተሰደው በሚኖሩበት የጎረቤት አገሮች ጭምር ደርሷል፡፡ የኦሮሞ ወጣቶችን ከጎረቤት አገሮች አሳፍኖ በመውሰድ የኦነግ አባል ወይም ደጋፊዎች ናችሁ እያለ የሚፈፅመውን ግድያ እና እስራትም እጅግ ከፍቷል፡፡ በወጣቶች ላይ የወያኔ መንግስት የግድያ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ጀምሮ አስከፊ ድርጊቱን በእስር ቤት እየፈፀመባቸው ይገኛል፡፡ ስለዚህ የወያኔ መንግስት እየፈፀመ ያለውን ግድያ፣ እስራት፣ ከትምህርት ገበታ ማፈናቀል እና ኢፍትሀዊ ውሳኔውን ለመጋፈጥና ነፃነቱን ለማወጅ የኦሮሞ ህዝብ በጋራ መነሳት ያለበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ የወያኔ መንግስት ከመቼውም ጊዜ የከፋ ጫና በኦሮሞ ወጣቶች ላይ እያደረሰ መሆኑ ለኦሮሞ ህዝብ ነፃነት መጎናፀፊያው ወቅት እየቀረበ መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ የኦሮሞ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ እጅ ለእጅ ተያይዞ መብቱን መጠየቅ አለበት፡፡
በመጨረሻም ያለምንም ወገናዊ እና ሰብአዊ ስሜት ህዝባችንን እየገደለ፤ እያሰረና እያሰደደ እንዲሁም ታሪካችንን፤ ባህላዊ እሴታችንን እና ሃይማኖታችንን ጭምር ጥላሸት እየቀባ፤ የተፈጥሮ ሃብታችንን በመመዝበር ለግል ጥቅም እያዋለ ያለውን አምባገነኑን የወያኔ መንግስት ማስወገድ የምንችለው እራሳችንን አደራጅተን በቆራጥነት ተነስተን በጋራ እርምጃዎችን መውሰድ ስንጀምር ነው። ስለዚህ እኛ ኦሮሞዎች ዛሬ ነገ ሳንል በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘን ወያኔ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን ትጥቅ በማስፈታት ህዝባችንን እየደረሰበት ካለው የመከራ ህይዎት ልንታደገውና ነፃነቱን ልናጎናፅፈው ይገባል። ፍርሃት በቃ ብለን ልንነሳ የሚገባበት ሰአት አሁን ነው። ከፍርሃት ቆፈን የተላቀቀ ህዝብ ደግሞ መሳሪያ ሳይገታው እራሱን በማደራጀት ነፃነቱን ለማወጅ ጊዜ አይወስድበትም። ወገኔ የኦሮሞ ህዝብ ሆይ ህዝባችን ከታሠረበት የመከራ ሰንሠለት በጣጥሰን ለማውጣት ያሉንን አማራጮች ሁሉ አሟጠን መጠቀም እንዳለብንም መዘንጋት የለበትም። በተለይ ጠላታችን የሆነውን የወያኔ መንግስ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ ጐን በመሰለፍ በትጥቅ ትግል ገርስሶ ለመጣል መነሳት ይኖርበታል ስልም ወገናዊ ምክሬን በዚህ አጋጣሚ ማስተላለፍ እሻለሁ! በኦሮሞ ሕዝብ እና መሬት ላይ ጥገኛ ሆኖ የኖረውን አምባገነኑን የወያኔ መንግስት ገርስሰን ህዝባችንን እና መሬታችንን ነጻ የሚወጣበት ጊዜ ቅርብ ነው!
ድል ለሰፊው የኦሮሞ ህዝብ!

No comments:

Post a Comment