Wednesday, May 22, 2013

በጥቁር ገበያ የዶላር ዋጋ በሰላሳ ሳንቲም መቀነሱ አነጋጋሪ እየሆነ ነው

በጥቁር ገበያ የዶላር ዋጋ በሰላሳ ሳንቲም መቀነሱ አነጋጋሪ እየሆነ ነው

dollar1
በአዲስ አበባ የሚገኙ የጥቁር ገበያ ባለድርሻዎች በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ታዋቂ ነጋዴዎች ከሙስና ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በመታሰራቸው በተፈጠረ መደናገጥ መነሻ ከፍተኛ የሆነ ኪሳራ እያጋጠማቸው መሆኑን ገልፀው፣ የዶላር ምንዛሪ በታሪኩ የሰላሳ ሳንቲም ቅናሽ አሳይቷል።
የከፍተኛ ባለስልጣናቱ በወንጀል የመጠርጠር ዜና ከመሰማቱ በፊት ሃያ ብር ከአርባ ሳንቲም የነበረው የዶላር ምንዛሪ ወደ ሃያ ብር ከአስር ሳንቲም በሳምንት ውስጥ ቀንሷል። በዚህ ቅናሽ ውስጥ አስደንጋጭ የሆነው ክስተት በማንኛውም አይነት ምንዛሪ መጠን ዶላር ወደላይ ሲጨምር ሆነ ሲቀንስ በሰላሳ ሳንቲም የልዩነት ምንዛሪ ውስጥ ወድቆ አለማወቁ መሆኑን ከስፍራው ያገኘነው መረጃዎች ያሳያሉ። በሙስና ከተጠረጠሩ ባለስልጣናት እና ነጋዴዎች ጋር በተያያዘ ይህ ልዩነት መፈጠሩ አብዛኛው የጥቁር ገበያ የዶላር ምንዛሪ ባለድርሻ አካላትን ማስደንገጡን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ጠቁመዋል።
ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ከፍተኛ የዶላር እጥረት በሀገሪቷ ሲከሰት የጥቁር ገበያ ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆናቸውን ቢገለጽም፣ ከመንግስት እና ከግል ባንኮች ሰራተኞች የገጠማቸው ችግር ግን እጅግ ፈታኝ እንደነበር አስረድተዋል። ይህም ሲባል፣ ለአንድ የአሜሪካን ዶላር ከአንድ ብር እስከ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም የባንኩ ደንበኞች ክፍያ እየፈጸሙ ከፍተኛ መጠን ያለው የዶላር ምንዛሪ ከባንኮቹ ማግኘትን በአማራጭነት በመውሰዳቸው ወደ እኛ ከመምጣት ባንኮንችን ተመራጭ ያደርጉ ነበር። ሆኖም ከፍተኛ መጠን ዶላር የማይፈልጉ ደንበኞች በወቅቱ ስለነበሯቸው ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አልሸሸጉም።
በአሁን ሰዓት ከመንግስት ኪራይ ሰብሳቢ የተለያዩ ባለስልጣናት እና ነጋዴዎች ወደ እነሱ ይፈስ የነበረው የኢትዮጵያ ብር ለዶላር ምንዛሪ ከፍተኛ ጠቀሜታ የነበረው ከመሆኑ አንፃር አሁን የተፈጠረው ድንጋጤ በከፍተኛ ሁኔታ የጥቁር ገበያውን የዶላር ምንዛሪ ይጐዳዋል። የተፈጠረው ድንጋጤ ግለሰቦችን ሳይቀሩ ማሸማቀቁን ያነጋገርናቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች አረጋግጠዋል። በስፍራው የተገኙት መረጃዎችም የሚያሳዩት ከመንግስት ከፍተኛ ኪራይ ሰብሳቢ ባለስልጣናት ሰንሰለት ይፈስ የነበረው የኢትዮጵያ ብር ለጊዜ ተቀዛቅዟል። ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ የጥቁር ገበያው አደጋ ውስጥ መውደቁ አይቀርም የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልፀዋል።
ለምን የኢትዮጵያ ብር ወደ ጥቁር ገበያ ይላካል?
በሙስና ውስጥ የተዘፈቁ የመንግስት ባለስልጣናት እና ተባባሪ የንግዱ ማሕበረሰብ አባላት ከሕግ አግባብ ውጪ የሚያገኙትን የኢትዮጵያ ብር በአዲስ አበባ ጥቁር ገበያ ውስጥ በዘረጉት ሰንሰለት ወደ አሜሪካ ዶላር ለውጠው ወደ ውጭ ሀገር እንዲወጣ በማድረግ ተጠቃሚ በመሆናቸው መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በተለይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በዚህ መልኩ የሰበሰቡትን የአሜሪካ ዶላር በተሰጣቸው ያለመፈተሸ መብት በመጠቀም እና በገቢዎችና ጉምሩክ በዘረጉት የኪራይ ሰብሳቢ ሰንሰለቶች አማካይ ወደ ውጭ ይዘውት የሚወጡበት አሰራር ሊኖር እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል። የሰበሰቡትን የአሜሪካ ዶላር በሳምሶናዊት ቦርሳቸው ውስጥ በመጨመር እና ቦርሳውን ላይ ያለመፈተሽ መብት የሚያጎናጽፋቸውን ልጣፍ በመለጠፍ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በቀጥታ ዶላሩን ይዘው የሚወጡበት ዕድል ከፍተኛ በመሆኑ ሊጠቀሙበት ይችላሉ ሲሉ ግምታቸውን ተናግረዋል።
በአስረጅነት ግምታቸውን ሲያስቀምጡ የገቢዎችና ጉምሩክ ምክትል ዋና ዳሬክተር የነበሩት አቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ መኖሪያ ቤት የተገኘው 26ሺ የአሜሪካ ዶላር እና 19ሺ ዩሮ የአውሮፓ ሕብረት የመገበያያ ገንዘብ በዚህ መልኩ የተሰበሰቡ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ግምት ገልፀዋል። አያይዘውም አንድ ግለሰብ ከ200 የአሜሪካ ዶለር ምንዛሪ ውጪ ይዞ መገኘት እንደማይችል በኢትዮጵያ ሕግ መስፈሩንም አስታውሰዋል። እንዲሁም በአቶ አስመላሽ ወ/ማሪያም መኖሪያ ቤት የተገኘውም አንድ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ወደ ዶላር ለመቀየር የተቀመጠ ገንዘብ ሊሆን እንደሚችል ከጥቁር ገበያ ያገኘነው ግምታዊ መረጃ ያሳያል።
ይህን መሰል ተግባር መፈጸም ትርጉሙ ብዙ ሊሆን ይችላል። በተለይ አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን በሀገር ውስጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መኖሩ እያወቀ የኢትዮጵያን ብር በዶላር እየመነዘረ ወደ ውጭ ሀገር በማስወጣት ተግባር ላይ ከተሰማራ እንደሀገር ትልቅ በደል መሆኑን መገንዘብ ሮኬት ሳይንስ አይሆንም። በዚህ መልኩ የተሰማሩ የመንግስት ባለስልጣናት በወፍ በረር ሲታይ፣ ዶላር ማሸሽ ቢመስልም በተግባር ግን ሲመነዘር የኢትዮጵያ መንግስትን እና ሥርዓቱን ቀስ በቀስ እየሸራረፉ ሊጨርሱት መዘጋጀታቸውን የሚያሳይ ነው። የፓርቲ ሹመኞቹን የመንግስትን ስርዓት ለዘረጋው ገዥ ፓርቲ ቢተውም፣ ተግባራቸው ግን ሕገ መንግስቱን በጠራራ ፀሐይ እየበጣጠሱት ስለመሆኑ አስረጂ አያስፈልገውም።
የገንዘብ ምንጩ ስትራቴጂ
እ.ኤ.አ. የሴፕቴምበር 11 ቀን 2001 የአሜሪካኑን የሽብር ጥቃት ተከትሎ ትንሹ ቡሽ ሴፕቴምበር 20 ቀን 2001 “WAR ON TERROR” በሚል መጠሪያ ዓለም ውስጥ የሚገኙ አሸባሪዎችን ለመደምሰስ ያስችላል በሚል አዲስ ስትራቴጂ ይዘው ብቅ አሉ። ቡሽ ቀጠል አድርገው በአሸባሪዎች ላይ የምንከፍተው ዘመቻ ‘የመስቀል ጦርነት’ ነው በማለት ለዓለም ሕዝብ በይፋ ተናገሩ።
ቡሽ ብዙም ሩቅ ሳይጓዙ በአደባባይ “የመስቀል ጦርነት” የሚለውን ቃል ተገቢ አይደለም፤ ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር አወዛጋቢ ፍቺ ያመጣል በማለት በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል። ጦርነቱን የምንጀምረው በአልቃይዳ እና በእሱ የሽብር መረብ ከተያያዙ አሸባሪዎች ጋር ነው ሲሉ አቋማቸውን በግልፅ አስቀመጡ። ዓለም ከአሜሪካ ጎን ቆመ። ቡሽም፣ ‘ወይ ከእኛ ወይም ከእነሱ’ ጋር መሆንን ምረጡ ብለው ለዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብ ጥሪ አቀረቡ። ዓለምም በወቅቱ በጐ ምላሽ ሰጣቸው። ጦርነቱ እንደቀጠለ ነው። ኦሳማ ቢላደን ግን ከአስር ዓመት በኋላ ተገድሏል።
እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ቁምነገር፤ እንደቡሽ የመጀመሪያ አቀራረብ ቢሆን የተቀደሰውን የእስልምና እምነት ከሽብር ተግባር ጋር ጨፍልቆ ለማየት ያለመ ነበር። ሆኖም ቡሽ ፈጥነው አባባላቸው ስህተት መሆኑን አርመው በይፋ ይቅርታ ጠየቁ። ስለዚህም ነገሮች ለያይቶ ማየት እንጂ በአንድ ቅርጫት ውስጥ ወርውሮ አንድ መለያ መስጠት ተገቢ አለመሆኑ ከዚህ መረዳት ይቻላል።
በተነፃፃሪነት ሲታይ ደግሞ ገቢዎችና ጉምሩክ በቀድሞ ከፍተኛ አመራሮቹ በኩል የኢትዮጵያ ነጋዴዎችን በተለይ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙትን ነጋዴዎች በግብር ስም ሁሉም ነጋዴ ግብር አጭበርባሪ ኪራይ ሰብሳቢ በማድረግ ሽብር “TERROR ON TAX” በነጋዴው ላይ ረጩ። ነጋዴውም ግብር መክፈሉን ሳይሆን ለኪራይ ሰብሳቢ ወይም ለግብር አጭበርባሪ ታፔላን ላለመጋለጥ በሚል ብቻ የገቢዎችና ጉምሩክ ከፍተኛ ሃላፊዎች ተገዢ መሆኑ አረጋገጠ። በመጨረሻም በተፈበረከው የሽበር ማዕቀፍ ውስጥ ነጋዴው ወደቀ። ፍርሃት፣ ስጋት መለያው ሆነ።
ከዚህ በኋላ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮቹ ጋር ተባብሮ መስራት የኪራይ ሰብሳቢዎች የህግ የበላይነትን ማረጋገጫ አድርጎ ተቀበለው። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው መንግስት ከፍተኛውን የሙስና ወንጀል በራሱ መንገድ ደረሰበት እንጂ በአደባባይ በመውጣጥ ለማጋለጥ የደፈረ ታዋቂ ባለሃብት አንድም አልነበረም። በሕግ የማይነኩ በሚመስሉ የገቢዎችና የጉምሩክ ባለስልጣናት ጋር ሲራኮቱ የነበሩ ታዋቂ የከተማችን ባለሃብቶች ሕግ በራቸው ደጃፍ ሲመጣ ሌላ የፖለቲካ ዓላማ ያለው ተግባር እንጂ ሙስና አይመስለንም ሲሉ በአደባባይ በዘረጉት የኪራይ ሰብሳቢዎች የሙስና ሰንሰለት በመጠቀም ከተማውን እያሟሟቁ ይገኛሉ። እውነቱ ግን ሌላ ሆኖ ነው እየታየ ያለው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በባሕርዳር በተደረገ የኢሕአዴግ 9ኛው ጉባኤ ላይ ከተጋበዙ ባለሃብቶች መካከል አንዱ የከተማችን ባለሃብት ለጉባኤው ያቀረበው ጥያቄ አጠቃላይ መንፈሱ ሲታይ “የኪራይ ሰብሳቢ” መሰረታዊ ይዘት በመቀየር ወደ ‘ሽብር’ መለወጡን አመላካች ነው። ባለሃብቱ ጉባኤውን የጠየቀው እንዲህ ሲል ነበር፣ “የኪራይ ሰብሳቢ ፍቺው በጣም የተለጠጠ ነው። በትክክልም ምን እንደሆነ እንኳን ለመረዳት አዳጋች ነው። በጅምላ ሁሉም ነጋዴ በገባበት ቢሮ ውስጥ ኪራይ ሰብሳቢ እየተባለ ይሸማቀቃል። እኔ እራሴ አሁን ኪራይ ሰብሳቢ በሚባለው ፍቺ ኪራይ ሰብሳቢ ልሁን፣ አልሁን ማረጋገጥ እንኳን አልችልም” ሲል በነጋዴው ላይ የተለቀቀውን ሽብር ለጉባኤው አስረድቷል።
ቡሽም በጅምላ የሚካሄደው ጦርነት የመስቀል ጦርነት ነበር ያሉት። እሳቸው ግን በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስትም ከንግዱ ማሕበረሰብ ጋር የበለጠ በመቀራረብ ለኪራይ ሰብሳቢዎች የተጋለጠውን የንግዱን ሕብረተሰብ ከሌላው ጤነኛ የንግዱ ሕብረተሰብ መለየት አለበት። ሁሉም ነጋዴ የኪራይ ሰብሳቢዎች መጠቀሚያም ተባባሪም ሊሆን ስለማይችል ነው። ንግድም ዓለምን የለወጠ የተከበረ ተግባር ከመሆኑ አንፃር መንግስት ከዚህ በፊትም ሲያደርገው እንደነበረው አሁንም አጋርነቱን ማሳየት ይጠበቅበታል። ስለዚህም መሰረታዊ የመንግስትን የገቢዎችና ጉምሩክ ፖሊሲን “በሽብር”፣ “በፍርሃት” ቆፈን ቀይረው ለራሳቸው ጥቅም ያደሩ የመንግስት ባለስልጣናት በፈጠሩት የተሳሳተ የኪራይ ሰብሳቢ ፍቺም በተቻለ ፍጥነት ለንግዱ ማሕበረሰብ መሰረታዊ ዕሳቤውን ማቅረብ ያስፈልጋል። በአንድ ቅርጫት ውስጥ የተቀመጠው የንግዱ ማሕበረሰብ ስምም ተገቢውን ስፍራ ሊያገኝ ይገባል። በመንግስትም በበኩሉ ኪራይ ሰብሳቢዎችን መያዙ ምርጫው ሳይሆን ግዴታው መሆኑን ግንዛቤ መውሰዱም ይጠቅማል። በተረፈ መንግስትና ጤናማው የንግዱ ማሕበረሰብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጸች መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር በመሆኑ ብዙ ማለት አይቻልም። (ፎቶ: Euroradio)
(ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 402 ረቡዕ ግንቦት 14/2005)

No comments:

Post a Comment