Monday, May 13, 2013

የቋንቋን ነገር! መግባቢያም መደናቆሪያም ሊሆን ይችላል፡፡

ኢህአዴግና መንግስት የራሳቸው ቋንቋ አላቸው የፓርቲ ኮድ የሚባል፡፡


ወዳጆቼ — በቀጥታ ወደ ቁምነገሩ ከመግባታችን በፊት በቀልድ ዘና ብንል ምን ይላችኋል? (አይዟችሁ አለመሳቅ መብታችሁ ነው!) አያችሁ — ለጊዜው ዋጋው ያልተወደደ ቀልድ ብቻ ስለሆነ እሱም ድንገት ሳይንር ብንዝናናበት ነው የሚሻለን – በኋላ ቀልድ ድሮ ቀረ እያሉ መቆዘም እንዳይመጣ (እንደእነ ጥሬ ሥጋና ክትፎ ማለቴ እኮ ነው!) አሁን ቀልዱን እነሆ – በነፃ፡፡ አንድ ሴናተር ጠበቃው ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ አዲስ ዜና ለመስማት በጉጉት ይጠብቃል። ጠበቃውም “ክቡር ሴናተር፤ መጀመርያ የትኛውን ዜና ልንገርዎ— መጥፎውን ወይስ የከፋውን?” ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡ ሴናተሩ ትንሽ ያስቡና “መጀመርያ መጥፎውን ልስማ—” ይላሉ፤ደግሞ ምን አመጣህብኝ በሚል ስሜት፡፡ ጠበቃም “ሚስትዎ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምስል እንዳገኘች ሰምቻለሁ” ይላቸዋል ሴናተሩ ተገርመው “ይሄን ነው መጥፎ ዜና ያልከው?እስቲ ደግሞ የከፋውን ያልከውን ንገረኝ ” ይሉታል በጥርጣሬ ዓይን እያዩት፡፡ ጠበቃውም “ምስሉ እኮ የእርስዎና የፀሃፊዎ ነው” አላቸውና እጢያቸውን ዱብ አደረገው፡፡
አያችሁልኝ —- የቋንቋን ነገር! መግባቢያም መደናቆሪያም ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዴማ ቋንቋውን የምናውቀው እየመሰለን ሁሉ የምንሸወድበት ጊዜ አለ፡፡ አሁን ለምሳሌ ከኢህአዴግና ከመንግስት ጋር በአንድ ቋንቋ የምናወራ ነው የሚመስላችሁ አይደል? እኔም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ እንደዚያ ይመስለኝ ነበር፤ እውነቱ ግን ሌላ ነው፡፡ ኢህአዴግና መንግስት በአማርኛ ቋንቋ የሚያወሩ ቢመስሉም ፍቺው እኛ ከምንረዳው ፍፁም የተለየ ነው፡፡ ይሄኔ እኮ እያፌዝኩ ይመስላችሁ ይሆናል፡፡ ግን ከምሬ ነው፡፡ ኢህአዴግና መንግስት የራሳቸው ቋንቋ አላቸው ፡፡ የፓርቲ ኮድ የሚባል፡፡ ለዚያ እኮ ነው መግባባት ያቃተን፡፡ ያመናችሁኝ ስላልመሰለኝ አንዳንድ ማሳያዎች ማቅረብ ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ ለናንተ ብቻ ሳይሆን ለራሱ ለኢህአዴግም ጭምር፡፡
እሱም ራሱ እኮ በኛ ቋንቋ የሚያወራ አድርጎ ነው የሚያስበው፡፡ በነገራችሁ ላይ ከዚህ የተገነዘብኩት አንድ ትልቅ ቁምነገር አለ፡፡ ምን መሰላችሁ? በአማርኛ ቋንቋ ስላወራን ብቻ እንግባባለን ማለት አይደለም፡፡ ሁለት ግለሰቦች በአንድ ቋንቋ እያወሩ ላይግባቡ ይችላሉ፡፡ እኛና ኢህአዴግ ምርጥ ምሳሌዎች ነን፡፡ (“እኛን ነው ማየት” ይሏል ይሄኔ ነው) ይኸውላችሁ —- መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ እጁን ሲያስገባ እኔና እናንተ በስጋት ልንሞት እንችላለን – ያ የምንጠላው ሶሻሊዝም ተመልሶ ነፍስ ሊዘራ ነው ብለን፡፡ አንዳንዶቻችን ደግሞ መንግስት የዘበኝነት ሚና ብቻ ሊኖረው ይገባል በሚል ለመቃወም ሁሉ ይዳዳን ይሆናል (አለማወቅ ደጉ አሉ!) ለዚህ ሁሉ የዳረግን ግን ሌላ ሳይሆን የቋንቋ ችግር ነው፡፡ የኢህአዴግን ቋንቋ አለማወቃችን! አያችሁ —- በኢህአዴግኛ መንግስት ኢኮኖሚ ውስጥ እጁን አስገባ ማለት ገበያውን አረጋጋ ማለት ነው (ቀላል ተሸወድን!) ትዝ ይላችኋል…ከፍተኛ የስኳር እጥረት የተከሰተ ጊዜ …”አሁንስ ክፉ ጊዜ መጣ!” ብለን ተስፋ ቆርጠን ነበር እኮ! ኢህአዴግ ነፍሴ ግን ከትከት ብሎ ሳቀብን (መሳቅ ሲያንሰው እኮ ነው!) የፓርቲ ቋንቋ ባለማወቃችን! ለካስ አገር ያተራመሰው የስኳር እጥረት ያን ያህል ጉድ የሚያሰኝ አልነበረም፡፡ ለምን መሰላችሁ? የስኳር እጥረት በኢህአዴግኛ የስኳር እጥረት አይደለም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ ገበሬ የስኳር ተጠቃሚ ሆኗል ማለት ነው፡፡
(ቋንቋ አለማወቅ እንዴት ያበሽቃል!) አሁን ተላመድነው እንጂ የኑሮ ውድነቱ መናር የጀመረ ጊዜ አበሻ “እግዚኦታ” ሊጀምር ምንም አልቀረውም ነበር፡፡ አውራው ፓርቲ ግን “ኧረ ለበጐ ነው!” እያለ ይማጠነን ጀመር፡፡ መቼም ኢህአዴግ ተዓምር አያልቅበትም አይደል (The Incredible የሚለውን ፊልም አይታችሁታል?) የኑሮ ውድነቱ እድገት ማለት ነው ብሎን ቁጭ አለ፡፡ ያኔ ተረጋጋን፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ባለሁለት ዲጂት ዕድገት በማሳየቱ የመጣ መሆኑን ስንሰማ ሃዘናችን ወደ ደስታ ተቀየረልን (ወይ ነዶ! የፓርቲ ቋንቋ አለማወቅ!) አያችሁ… ለእኛ የኑሮ ውድነት፣ በኢህአዴግ ቋንቋ ዕድገት ማለት ነው (ቀላል ተሸወድን!) ይኸውላችሁ…የእኛና የልማታዊ መንግስታችን ልዩነት ሌሎች እንደሚያስወሩብን ያን ያህል የተጋነነ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ እንኳንስ ከእኛ ከመረጥነው ህዝቦቹ (ድምፆቹ ማለት እኮ ነን) ጋር ቀርቶ ለሥልጣን ከሚፎካከሩት ተቃዋሚዎችም ጋር የከፋ ጠላትነት የለውም፡፡
ችግሩ የቋንቋ ብቻ ነው፡፡ የፓርቲውን የኮድ ቋንቋ የሚያውቁት ቁንጮ የኢህአዴግ አመራሮች ብቻ ናቸው (ቁንጮ አመራሩ አድርባይ ሆኗል ነው የተባለው?) ለዚህ እኮ ነው ኢህአዴግና ህዝቡ ለሁለት አስርት ዓመታት መግባባት ያቃተው፡፡ ለምሳሌ ኢህአዴግ የበቆሎ ምርት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ኤክስፖርት ማድረግ እንጀምራለን ሲል ልታፌዙበት ትችላላችሁ፡፡ እናንተማ —- በቆሎ ከአገር ውስጥ ፍጆታ ተርፎ በምን ተዓምር ለውጭ አገር ገበያ ይቀርባል ብላችሁ ነው። እሱ ግን እንደዚያ ዓይነት ነገር አልወጣውም – እሱ ሊል የፈለገው በጥቂት ዓመታት ውስጥ “የበቆሎ ምርት እጥረት ጠብቁ ነው!” (የባቢሎን ቋንቋ ሆነባችሁ አይደል?) የኢትዮጵያ መብራት ሃይል ኮርፖሬሽን ከሁለት ዓመት በፊት ምን ነበር ያለን? የኤሌክትሪክ ሃይል ለጐረቤት አገራት ኤክስፖርት ማድረግ እንጀምራለን ሲለን ተገርመን አልነበር (በአማርኛ የሚያወራ መስሎን ነዋ!) ጊዜው ሲደርስ ግን የገጠመን ተደጋጋሚ የሃይል መቆራረጥ ሆነ፡፡ ኮርፖሬሽኑ ዋሽቶናል እያልኩ ግን እንዳይመስላችሁ፡፡ ችግሩ የእኛ ነው – ቋንቋ አለማወቃችን! ግን አንድ ነገር ልንክድ አንችልም፡፡
ኤልፓ ባይዋሸንም እኛ ግን በደንብ ተሸውደናል (በቋንቋ ዕውቀት ማነስ!) “ፓወር ኤክስፖርት አድርገን በፎርየን ከረንሲ እንንበሸበሻለን” ስንል በሻማና በፋኖስ ማዕድ መቅረብ ጀመርን! (ፈረንጅ ይሄ ነው “ዲዛስተር” የሚለው) ባለፈው ሚያዝያ ወር በተካሄደው የአዲስ አበባና የአካባቢ ምርጫም ተሸውደናል ልበል? (በደንብ ነዋ!) ምርጫ ቦርድ፤ “ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ይካሄዳል” ሲለን እውነት መስሎን በደስታ ጮቤ ረግጠን ነበር! ለካስ የቋንቋ ክፍተት የፈጠረው ችግር ነው፤ እንጂማ ቦርዱ “ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ይካሄዳል” ሲል ኢህአዴግ ያለተፎካካሪ ለምርጫው ይወዳደራል ማለቱ ነበር፡፡ መቼም በእኛ ቋንቋ አለማወቅ ቦርዱን መውቀስ “ፌር” አይደለም አይደል? በነገራችሁ ላይ በቅርቡ “የኢህአዴግና የህዝቡ ቋንቋ” የሚል ሳይንሳዊ መጽሐፍ ለማሳተም አስቤአለሁ (ኢህአዴግ ስፖንሰር ካደረገኝ) የአዲስ አበባ መስተዳድር በመዲናዋ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ከደርግ በተኮረጀ የታክሲ ስምሪት (ቀጣና) እፈታለሁ ሲለን በጄ ብለን የተቀበልነው ቋንቋው ቀጥተኛ መስሎን እኮ ነው፡፡
ለካስ መስተዳድሩም በገዢው ፓርቲ የኮድ ቋንቋ ነው የሚግባባው፡፡ እናም “ታክሲ በቀጣና” የሚለው በኢህአዴግኛ “ታክሲ በወረፋ” አንደማለት ነው (የውጫሌ ውል ትዝ አላችሁ?) በዚህም የተነሳ ዛሬ ድረስ ጠዋትና ማታ ለታክሲ እንሰለፋለን (ቋንቋ አለማወቃችንን እያማረርን) በ2002 ምርጫ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን በዝረራ ካሸነፈ በኋላ ምን ብሎ ነበር ያጽናናቸው? “ተቃዋሚዎች በፓርላማ መቀመጫ ባይኖራቸውም በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉበት መድረክ ይመቻቻል” አላለም (ከዋሸሁ እታረማለሁ!) ያኔ ታዲያ ሁላችንም ደስ ብሎን ነበር – የጦቢያ ፖለቲካ ሊሻሻል ነው በሚል፡፡ ግን አሁንም ችግሩ የኛ ነበር፡፡ ኢህአዴግ በፓርቲው የኮድ ቋንቋ መናገሩን አልተገነዘብንም፡፡ ለካስ ተቃዋሚዎች በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ይሳተፋሉ ሲል ከእነ አካቴው ይገለላሉ ማለቱ ነበር (እውነትም የባቢሎን ቋንቋ!) በነገራችሁ ላይ ያለፉ ሁነቶችን እየነቀስኩ የኢህአዴግኛ ትርጉማቸውን ሰንግራችሁ —- የፓርቲ ቋንቋ የምችል መስሏችሁ እንዳትሸወዱ! ሁሉንም ያወቅሁት ከህይወት ተመክሮ ነው፡፡ ነገርዬው ከሆነ በኋላ ማለት ነው፡፡ እንጂማ እኔን ለፓርቲ ቋንቋ ማን ያደርሰኛል (ካድሬ መሆንን ይጠይቃላ!) በቅርቡ አንዳንድ የመንግስት መ/ቤት አመራሮች በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ እያሉ የሚናገሩትን ሰምታችሁልኛል? ለምሳሌ ያቀዱትን በወቅቱ ማጠናቀቅ ያልቻሉበትን ምክንያት ሲጠየቁ ምን እንደሚሉ ታውቃላችሁ? “የአቅም ማነስ እንዳለብን አንክድም!” ይላሉ – አፋቸውን ሞልተው፡፡ ለምን እውነቱን ተናገሩ የሚል ነገር አልወጣኝም (እውነት ከሆነ አይደለ!) እኔን ያስገረመኝ ይሄን ሲናገሩ በጥፋተኝነት ስሜት አለመሆኑ ነው፡፡
በቃ የአቅም ማነስን ከአቅም በላይ እንደሆነ ችግር አድርገው ነው የሚያቀርቡት፡፡ ኢህአዴግ አንዳንድ ከቁጥጥሩ በላይ የሆኑ ችግሮች ሲገጥመው “ከደርግ የወረስነው ችግር ነው!” እንደሚለው፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ…ካለፈው መንግስት በግድ የተላለፉ አንዳንድ ችግሮች እንደሚኖሩ መካድ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ድህነት፣ ደካማ የሥራና ኋላቀር የፖለቲካ ባህል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እንግዲህ ሳንወድ በግድ ከንጉሱም ሆነ ከደርጉ የወረስናቸውን ችግሮች እንደምንም ታግለን ከመፍታት በቀር አማራጭ የለንም፡፡ እኔን የሚገርመኝ ግን ካለፈው የደርግ ወታደራዊ መንግስት ወደንና ፈቅደን የወረስናቸው አንዳንድ አሰራሮችና ችግሮች ናቸው! ከወረስናቸው ችግሮች አንዱ ሶሻሊዝም ነው (ሶሻሊዝም ችግር እንጂ ምን ሊባል ይችላል!) ሌላው የታክሲ ቀጣና ነው – ወደንና ፈቅደን ከደርግ የወረስነው፡፡ ተሞክሮ የቀረውም የዋጋ ቁጥጥር ወደን የወረስነው ነበር፡፡ (ኢህአዴግ ሳያውቀው “ደርግ ናፋቂ” ሆነ እንዴ?) ወደንና ፈቅደን ችግር ከመውረስ ያውጣን እንጂ ሌላ ምን ይባላል!! በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎችን እንዳይዘግቡ ከአገር ሲያስወጣ የፕሬስ ነፃነትን ያፈነ ከመሰላችሁ የቋንቋ ስህተት ፈፅማችኋል፡፡ በኢህአዴግኛ የአገር ገጽ ግንባታ ነው፡፡ ካፒታሊዝምን ሲያብጠለጥልና የደረሰባቸውን የኢኮኖሚ ድቀት ደጋግሞ ሲያነሳ ደግሞ “ፊቴን ወደ ቻይና አዙሬአለሁ” ማለቱ ነው፡፡ (በፓርቲው ቋንቋ ማለቴ እኮ ነው!) መልካም የዳግማይ ትንሳኤ በዓል እመኝላችኋለሁ!
source: addis admas.com

No comments:

Post a Comment