Tuesday, May 14, 2013

አምስት:- ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ፤ ነገረኛነትን እንዴት እንገራዋለን?

ፕ/ሮ መስፍን ወልደማርያም
ሳይንሳዊ ውይይትም ወይም ክርክር የሚመራው በሕገ-ኀልዮት ወይም በእንግሊዝኛ ‹‹ሎጂክ›› በሚባለው የአስተሳሰብ መመሪያ ነው፤ ይህንን አዚህ ለመዘርዘር ከባድ ነው፤ ግን ሁለት መሠረታዊ ቁም-ነገሮችን ማንሣት እንችላለን፤ አንደኛው የሕገ-ኀልዮት መንገድ ከዝርዝር ተነሥቶ ወደማጠቃለል የሚሄድ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከአጠቃላይ ወደዝርዝር የሚወርድ ነው፤ (የትና መቼ እንደሆነ አላስታውስም እንጂ ከዚህ በፊት በጻፍሁት ከታች-ወደላይና ከላይ-ወደታች በማለት እነዚሁኑ መንገዶች ለማስረዳት ሞክሬ ነበር፤ከታች ወደላይ ከዝርዝር መነሣቱን ሲሆን፣ ከላይ ወደታች ያልሁት ከአጠቃላይ የሚነሣውን ነው፤) በቀላል ምሳሌ ላስረዳ፤ ከበደ ሁለት ዓይኖች አሉት፤ ወርዶፋ ሁለት ዓይኖች አሉት፤ ዘነበች ሁለት ዓይኖች አሏት፤ …. እንዲህ እያልን በአካባቢያችን ያሉትን ሰዎች ሁሉ አንድ በአንድ (በዝርዝር) ከገለጽን በኋላ ሰዎች ሁሉ ሁለት ዓይኖች አሏቸው ወደሚል ትክክለኛ መደምደሚያ (ማጠቃለያ) እንደርሳለን፤ በዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ማዳረስ አንችልም፤ ከምናገኛቸው ሰዎች ዘጠና አምስት ከመቶው ሁለት ዓይኖች ያሏቸው ከሆኑ አልፎ አልፎ ያጋጠሙንን ዓይን የሌላቸውን ሰዎች በመጥቀስ ማጠቃለያው አይፈርስም ወይም አይሻርም፤ ከተጠኑት ሰዎች ውስጥ ቢያንስ ዘጠና አምስት ከመቶ የሚሆኑት ሁለት ዓይኖች እንዳሏቸው ከተረጋገጠ ሰዎች ሁሉ ሁለት ዓይኖች አሏቸው የሚለውን ማጠቃለያ እንደእውነት ተቀብለነው እያንዳንዱን ሰው በተናጠል ሁለት ዓይኖች አሉት ለማለት እንችላለን፤ ይህ ሳይንስ እውቀትን ለማስፋፋት የሚጠቀምበት መንገድ ነው።Prof. Mesfin Woldemariam
ማጠቃለያው ተረጋግጦ ከተቀመጠ በኋላ ከአጠቃላይ ወደዝርዝር በሚወርደው መንገድም መጠቀም አንችላለን፤ ስለዚህም ሰዎች ሁሉ ሁለት ዓይኖች አሏቸው ከሚል ከደረስንበት ማጠቃለያ እንነሣና ከበደም፣ ዘነበችም፣ ወርዶፋም ሰዎች በመሆናቸው ሁለት ሁለት ዓይኖች አሏቸው፤ እያልን ከማጠቃለያው ወደዝርዝሩ እንደርሳለን፤ ልብ በሉ ማጠቃለያው የቆመው እያንዳንዱን እውነት በማስተዋል ላይ ነው፤ ከማጠቃለያው የምንነሣው ግን ከሀሳብ ነው፤ ሰዎች ሁሉ ሁለት ዓይኖች አሏቸው ከሚል ሀሳብ ተነሥተን ከበደ ሰው ነውና ሁለት ዓይኖች አሉት … እያልን ስለእያንዳንዱ ሰው እንናገራለን።
በሁለቱም የአስተሳሰብ መንገዶች ብዙ ጊዜ አስከፊ ስሐተቶች ይፈጸማሉ፤ አንድ ወይም ሁለት ምሳሌዎችን በመያዝ ቶሎ ወደማጠቃለያ አንዘላለን፤ ሁለት ወንዶች ያታለሏት ሴት ወንዶች ሁሉ አታላዮች ናቸው ወደሚል ማጠቃለያ ትደርሳለች፤ ወይም ሁለት ሴቶች ያታለሉት ወንድ ሴቶች ሁሉ አታላዮች ናቸው ወደሚል ማጠቃለያ ይደርሳል፤ በዓለም በሙሉ ያሉ ስንትና ስንት ሚልዮን ሴቶችን በሁለት በሚያውቃቸው ሴቶች ወክሎ መናገር የማሰብ ውጤት ሊሆን አይችልም፤ ማጠቃለያው ከስሜት የመነጨ እንጂ ትክክለኛ አስተሳሰብን ተከትሎ የተገኘ አይደለም፤ በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ ሰው የራሱን ስሜት ብቻ እየተናገረ ወደስምምነት ለመድረስ በፍጹም አይቻልም፤ እንዲሁም እውነተኛነቱ ከአልተረጋገጠ ማጠቃለያ ተነሥቶ እያንዳንዱን እዚያ ውስጥ መክተት ወደፍጹም ስሕተት የሚያገባ ነው፤ በለጠና ዘለቀ ያታለሏት ሴት ወንዶች ሁሉ አታላዮች ናቸው ወደሚል የተሳሳተ ማጠቃለያ ደረሰች፤ ያንን የተሳሳተ ማጠቃለያ ይዞ ሌሎችም ወንዶች ሁሉ አታላዮች ናቸው ማለት አለማሰብ ነው፤ ቀደም ሲል እንደተባለው ወደትክክለኛ ማጠቃለያ ለመድረስ ሰፊ ጥናት ተደርጎ ቢያንስ ዘጠና አምስት ከመቶው የሚሆኑት ወንዶች አታላዮች መሆናቸው ሲረጋገጥ ነው፤ በለጠና ዘለቀ ብቻ ወንዶችን ሁሉ አይወክሉም።
ብዙ ጊዜ በችኮላና በጅምላ የሚነገሩ ነገሮች ስሕተት አለባቸው፤ በቶሎ ካልታረሙ ክርክር ሲገጥማቸው እየጠነከሩ ይሄዳሉ፤ ለምሳሌ ቀሚስ የሚለብስ ሁሉ ሴት ነው፤ ወይም ሴቶች ሱሪ አይታጠቁም፤ እነዚህ ዓረፍተ ነገሮች በእውነት ላይ የተፈናጠጠ ሐሰትን የያዙ ናቸው፤ ይህንን ለማፍታታት አልሞክርም፤ ለአንባቢው እተወዋለሁ፤ አብዛኛውን ጊዜም ንግግራችን የጅምላ ነው፤ ከጅምላ አነጋገር ፈጽሞ ለመውጣት አንችልም፤ ግን አእምሮአችን ማበጠርና ማጣራት እንዲችል፣ ቀጥሎም ተቃውሞ ሲመጣ ለመታረም እንዲዘጋጅ ማስለመድ ይጠቅመናል።
አእምሮው በአንድ ዓይነት ጥላቻ የተመረዘ ሰው ከሱ ዘር፣ ወይም ከሱ ጎሣ፣ ወይም ከሱ ቋንቋ፣ ወይም ከሱ ሃይማኖት … የተለየውን ሰው ሁሉ በስሜት ብቻ እያጠቃለለ በጅምላ ይጠላል፤ ይንቃል፤ ይሰድባል፤ ያዋርዳል፤ እያንዳንዱንም ሲያገኝ በአእምሮው ውስጥ ያስቀመጠውን ምስል እያየ ሰውዬውን ይገምተዋል፤ ሰውዬውን የሚገምተው እሱ ራሱ አእምሮው ውስጥ ባስቀመጠው ምስል ነው እንጂ ሰውዬው በሚናገረው ወይም በሚሠራው አይደለም፤ አንዳንድ ወንዶችም አንዲት ሴት ክፉኛ ስላቃጠለቻቸው ሴትን በሙሉ ይጠላሉ፤ ከአንድ ተነሥቶ ወደጅምላ መዝለል በጣም ከባድ ስሕተት ነው።
ሳይንስ በአብዛኛው የሚጠቀምበት በመጀመሪያው፣ ከዝርዝር ወደማጠቃለያው በሚወስደው የአስተሳሰብ መንገድ ነው፤ የሳይንስ ሕጎች ሁሉ የተገነቡት በዚህ ከዝርዝር ወደአጠቃላይ በሚወስደው አስተሳሰብ ነው፤ እያንዳንዱ ካልታወቀ ሁሉም በአጠቃላይ ሊታወቅ አይችልም፤ የተረጋገጠ እውቀት የሚጀምረው ከእያንዳንዱ ነገር ነው አንጂ ከጅምላ አይደለም።
በኢትዮጵያ የፖሊቲካ ንግግር ዋናው ጅምላው ነው፤ ለሰነፍ አእምሮ በጅምላ ማሰቡ በጣም ይቀላል፤ አንዳንዱን እያገላበጡ ከማጣራት ጅምላውን በሩቁና በግርድፉ መፈረጅ ቀላል ቢመስልም ስሕተት ነው፤ ከለመደም አእምሮን ያባልጋል፤ በፖሊቲካ በተለይ የተሳሳተ የጅምላ አስተሳሰብና አነጋገር አገርንና ሕዝብን ወደከፋ አደጋ ውስጥ የሚጨምር ይሆናል፤ ለዚህ ነው የተሳሳተ የጅምላ አስተሳሰብን በጥንቃቄ ማገላበጥ የሚያስፈልገን፤ ኢሳት በዚህ በኩል ትክክልና በጎ አስተሳሰብን ለማበረታታት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

No comments:

Post a Comment